Saturday, 12 October 2019 12:19

የቤተ መንግስቱ አንድነት ፓርክ በወፍ በረር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 ስድስት የምስራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች በተገኙበት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ተመርቆ የተከፈተው “አንድነት ፓርክ”፤ የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ የሚገልጥ፣ በአፍሪካም የመጀመሪያው ታሪክን ከተፈጥሮ ያቀናጀ ፓርክ ነው ተብሏል፡፡ በፓርኩ ምርቃት ላይ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒ፣ የኬንያው ኡጅሩ ኬንያታ፣ የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር፣ የሶማሊያው መሐመድ አብዱል መሐመድ፣ የሱዳን ጠ/ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እና የጅቡቲው የህዝብ ለህዝብ ልዑክ መሪ ናቤል መሐመድ ተገኝተዋል፡፡
በምረቃ ስነሥስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ጠንካራ ጥረት በሁሉም አካላት መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይም በአዲስ አበባ ከአፍሪካ ትልቁን ፓርክ ከየካ እስከ አስኮ ባለው ሰንሰለታማ ተራራ ላይ ለመስራት መታቀዱን በመግለጽ ይህንንም ፕሮጀክት ከማሳካት የሚያቆመን አንዳችም ሃይል የለም ብለዋል፡፡
ታሪክን ከዛሬ ጋር ለነገ በሚበጅ መልኩ የማስተሳሰር ስራን አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ስራችን ውስጥ የቻሉ ያግዙናል ያልቻሉ ይተወናል፣ ያልገባቸው ይተቹናል፣ ያልፈለጉት ይቃወሙናል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “እኛ ግን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን የጀመርነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪክ የማይሽረውና የማይዘነጋው ትውልዱ የሚዘክረው ተግባር ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል:: በእለቱ በክብር እንግድነት የተገኙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተግባር አድንቀዋል የኢትዮጵያንም ክብር በንግግራቸው ዘክረዋል፡፡
ይህ አንድነት ፓርክ ተብሎ የተሰየመው በአፍሪካ ወደር የለውም የተባለው የታሪክና የተፈጥሮ መዘክር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወዳጆቻቸው ባገኙት ገንዘብ የተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ፕሮጀክቱም በጠቅላላው 5 ቢሊዮን ብር ገደማ ፈጅቷል ተብሏል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ መሪዎች አጀብ የተመረቀውና ላለፈው 1 ዓመት ያህል ቀን ተሌት ስራው ሲከናወን የቆየውን ‹‹አንድነት ፓርክ›› ከሃሳቡ ጥንስስ ጀምሮ የሚያውቁት አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን እንደሚከተለው ለአዲስ አድማስ በሰፊው አብራርተዋል፡፡
የአንድነት ፓርክን ሀሳብ አመነጭው ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳቡን ካመነጩ በኋላ የገቡት ለስራው የሚሆን ባጀትና ባለሙያዎችን ወደ ማፈላለጉ ሥራ ነበር፡፡ አርክቴክት ዮሐንስ እንዳሉት ለዚህ ትልቅ ፕሮጀክት በርካታ የውጭ ባለሙያዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች፣ መሐንዲሶች ተመልምለዋል፡፡ የሚሠራው ስራ ሀገራዊ መልክ እንዲኖረውም ያለሰላሰ ጥረት መደረጉን አርክቴክቱ ይመሰክራሉ፡፡ ሲከናወን የቆየውን ሥራ በሁለት በመክፈልም አንደኛ ነባሩን ለጉብኝት በሚመጥን መልኩ የቅርስ እንክብካቤ ስራ መስራት፤ ሁለተኛው ደግሞ ተጨማሪ አዳዲስ የውበት ስራዎችን ማከናወን እንደሆነም - አርክቴክት ዮሐንስ ይናገራሉ፡፡
የቤተ መንግስቱ የፓርክ ስራ ተጠናቆ ከትናንት በስቲያ ለጉብኝት ክፍት ሲደረግ ጐብኚዎች ምን ይመለከታሉ የሚለውን አርክቴክቱ እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡
በመጀመሪያ ጐብኚዎች የሚያገኙት የክፍያና የመግቢያ ቦታውን ነው፡፡ በዚህ ቦታም በፓርኩ ስለሚጐበኙ ነገሮች በምስልና በድምጽ ቅንብር (ዲስፕሌይ) ገለፃ ይደረግላቸዋል፡፡ ይሄን እንዳለፉ የድንኳን ጥላ የሚመስል ነገር አለ፤ ለጐብኚዎች አጠቃላይ ገለፃ የሚደረግበት የመጀመሪያ ክፍል ነው፡፡ ይሄን እንዳለፉ የህፃናትና ልጆች የመዝናኛና መጫወቻ ሥፍራ አለ፡፡ አዋቂዎች ህፃናትን በዚያ ቦታ እንዲዝናኑ ትተው ለጉብኝት ወደ ውስጥ መዝለቅ ይችላሉ::
የህፃናት መጫወቻ ቦታውን እንዳለፉ የሚያገኙት ዋናውን መናፈሻና አረንጓዴ ቦታ ይሆናል፡፡ ይሄን መፈናሻ እንዳለፉ በስተቀኝ በኩል የዱር እንስሳት ማቆያ ቦታ ይገኛል፡፡ በዚህ የእንስሳት ማቆያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ጥቁር አንበሳ የሚገኝ ሲሆን ጦጣዎችና ወደ 20 የሚደርሱ የዱር እንስሳ አይነቶች ወደ ፓርኩ ይገባሉ ተብሏል፡፡
ከእንስሳት ፓርኩ ብዙም ሳይርቅ የኢትዮጲስ ጋርደን ይገኛል፡፡ በዚህ ጋርደን ውስጥ እንደ ጤናዳም፣ አሪቲ የመሳሰሉ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የመድሃኒትና የምግብ ዕፅዋት ይገኛሉ፡፡ ይሄን ጋርደን አልፈው ትንሽ እንደተጓዙ የሚያገኙት የልኡላን መኖሪያ ቤትን ሲሆን ይህ አፄ ኃይለሥላሴ፣ ንግስት ነገስታት ዘውዲቱና ልጅ ኢያሱ… ከመንገሳቸው በፊት ይኖሩበት የነበረ ህንፃ ነው፡፡ ከፊት ለፊቱ ሰፊ አደባባይ ይገኛል:: “ህልሜ ለሀገሬ” የሚል ጽሑፍ ባለበት በዚህ ሥፍራ ፎቶ በመነሳት ማስታወሻ ማስቀረት ይቻላል፡፡  
ይሄን ታሪካዊ ስፍራ እንዳለፉ ዋናውን የአፄ ምኒልክ የቤተ መንግስት ህንፃ ያገኛሉ::  ከቤተ መንግስቱ አቅራቢያም የፊት አውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ መኖሪያ ቤት ይታያል:: የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግስት ባለ አንድ ፎቅ ግዙፍ ህንፃ ሲሆን ወለሉ በእንጨት፣ ግድግዳው በድንጋይ የተሠራ ጥንታዊ ህንፃ ነው፡፡ ከጀርባው በድልድይ የሚገናኝ ሌላ ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ የእቴጌ ጣይቱ ህንፃ ነው፡፡ በተለምዶ ‹‹እንቁላል ቤት›› በመባል የሚታወቀው - የአፄ ምኒልክ ጽሕፈት ቤት ሆኖ ያገለግል የነበረው ነው፡፡ የሕንጻው ምድር ቤት ጽ/ቤታቸው ሲሆን አንደኛ ፎቅ ላይ የፀሎት ቤታቸው ይገኛል፡፡ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው ቴሌስኮፕ የተገጠመለት የቅኝት ማማ ሲሆን አዲስ አበባን በ360 ዲግሪ ማስቃኘት ይችላል፡፡
ከእነዚሁ ህንፃዎች ጋር የተያያዘ የአፄ ምኒልክና ቤተሰቦቻቸው አነስተኛ ግብር ቤትም አለች፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በጽሕፈት ሚኒስቴር ስር የነበረና ጥንታዊ መዛግብትን የያዘ ቤት ይገኛል:: ይህ ቤተመዛግብት በአፍሪካ ጥንታዊው የመዛግብት ቤት ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ ጥንታዊ ሰነዶች በከፍተኛ ጥበቃ የሚቀመጡበት ቤት ሲሆን የሀገረ መንግስቱ ትልቁ የታሪክ ሰነዶች ማከማቻም ነው፡፡ እስከ ዛሬ በዚህ ቤተመዛግብት በልዩ ፍቃድ ገብቶ የተጠቀመው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ብቻ ሲሆን፤ ‹‹አጤ ምኒልክ›› የሚለውን መጽሐፍ የፃፈው ከዚህ ቤተመዛግብት ባገኘው ሰነድ መነሻ ነው፡፡ ይህ ቤተመዛግብት ለጊዜው ለጐብኚዎች ክፍት አልተደረገም፡፡ ሌላው ለጉብኝት ገና ክፍት ያልሆነው የአፄ ኃይለስላሴ ዙፋን ችሎትና ጽ/ቤት ሲሆን ኋላም የኮ/ል መንግስቱ ጽ/ቤት ሆኖ ያገለገለ፣ ደርግ አፄ ኃይለሥላሴን ቀብሯቸዋል ተብሎ የሚታሠብበትም ሥፍራ ነው፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ለቢሮ የተጠቀሙበት ሲሆን ኋላም መኖሪያ ቤታቸውም ሆኗል፡፡ አስከሬናቸውም የወጣው ከዚህ ቤት ነው፡፡ ሌላው ቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ማሞም በዚሁ ቤት ነበር የሚኖሩት፡፡ ቀደም ሲል እዚሁ ህንፃ አካባቢ  የአንበሶች መኖሪያም ነበር፡፡
ጐብኚዎች ሌላው የሚመለከቱት የአፄ ምኒልክ ዙፋን ችሎት ነው፡፡ እዚህ አዳራሽ ውስጥ የአፄ ኃይለሥላሴ ቅርጽ ስነ ዙፋኑ ይገኛል፡፡ አፄ ኃይለስላሴ የእንግሊዟን ንግስት ኤልሣቤጥ፣ የፈረንሳዩን ጀነራል ደጐል፣ የዩጐዝላቪያውን ቲቶን በዚህ አዳራሽ ነበረ የተቀበሏቸው:: ለዚህ ማስታወሻም የአገራቱ መሪዎች ምስል ተቀምጧል፡፡ አዳራሹ የደርግ ም/ቤት ሆኖም አገልግሏል፡፡ 60ዎቹ የአፄ ኃይለሥላሴ ሹማምንት ላይ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው በዚህ አዳራሽ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህ ቦታ አሁን ለጉብኝት ክፍት ሆኗል፡፡
ይሄ ህንፃ 3 ግዙፍ ክፍሎች ያሉት በመሆኑም አሳራሾቹ ለሶስት አላማዎች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በግራ በኩል ያለው የኢትዮጵያን ሃይማኖቶች በዲስፕሌይ የሚተርክ ክፍል ነው - ከአይሁድ ጀምሮ እስከ ባህላዊ እምነቱ ኢሬቻ ድረስ፡፡ ኢትዮጵያ በቅዱስ ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችባቸው ቦታዎችም በዲስፕሌዩ ተለይተው በጥሩ ሁኔታ ተቀምጠዋል፡፡
በዋናው አዳራሽ ጀርባ በኩል ባለው ክፍል ደግሞ የ3ሺህ ዘመን የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታን በዲስፕሌይ የሚተርክ ክፍል ነው፡፡
በስተቀኝ ባለው ሶስተኛው አዳራሽ ደግሞ ከአፄ ሚኒሊክ ጀምሮ እስካሁን ያለውን በተመሳሳይ የሚተርክ ዲስፕሌይ ያለበት ክፍል ነው፡፡
ይህን ቦታ ጨርሰው እንደወጡና ጥቂት እንደተራመዱ ግዙፉ የአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ያገኛሉ፡፡ በዚህ አዳራሽ ደግሞ የአፄ ምኒልክ ምስለ ቅርጽ በዙፋን ሆኖ ይታያል:: ይሄን አዳራሽ እንዳለፉ ዘጠኙን የኢትዮጵያ ክልሎች የሚወክሉ እልፍኞች ተዘጋጅተው የየክልሎቹ ባህል ትውፊትና ቅርስ በቅምሻ መልክ ቀርቦበታል፡፡
ይህ ቤተ መንግስትን ከእንስሳት ማቆያና መናፈሻዎች ጋር አጣምሮ የያዘው አንድነት ፓርክ፤ በአፍሪካ ወደር እንደሌለው ተረጋግጧል ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ ምናልባት ቀጣዩ ፕሮጀክት ደግሞ ኢዮቤልዩ ቤተመንግስትን በተመሳሳይ ወደ ፓርክነት የመቀየር ስራ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ እሳቸውም በዚህ ፕሮጀክት ከሚሳተፉ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው::
አንድ ሰው ወደዚህ ፓርክ ለጉብኝት ሲመጣ የሙሉ ቀን ፕሮግራም መያዝ እንዳለበት ባለሙያው ይመክራሉ፡፡ ይሄ የቤተ መንግስት ፓርክ ዕድሳትና ግንባታ በአጠቃላይ 5 ቢሊዮን ብር መፍጀቱ ተነግሯል፡፡


Read 3768 times