Saturday, 12 October 2019 12:13

ጉዞህ የዓመት ዕቅድ ከሆነ፣ ጤፍ ዝራ ጉዞህ የአምስት ዓመት ከሆነ፣ ባህር ዛፍ ትከል ጉዞህ የዘለዓለም ከሆነ፣ ልጅህን አስተምር

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አህያና ውሻ አንድ ቀን ተገናኝተው፣ ስለ አሳለፉት ሕይወት ይወያያሉ፡፡
አህያው - ‹‹የእኔ ሕይወት፣ ዘለዓለም ዓለሙን ጀርባን የሚያጎብጥ የሸክምና የልፋት መከራ ነበር›› አለ፡፡
ውሻም -  “የእኔ ሕይወት ደግሞ ሁሌ ሌሊቱን ያለ እንቅልፍ መጮህ ነው፡፡ ባለቤቶቹ ተኝተው፣ ‘ይሄ ውሻ እኮ ተኝቶ ያዘርፈኛል’ እያሉ እያሙኝ መሳቀቅ፣ እጣ ፈንታዬ ነበር፡፡ የት እሄዳለሁ ብዬ በጭንቀት ተጎሳቁዬ ነበር የምኖረው፡፡`
አህያ - “አሁን ግን አረጀንና አባረሩን፡፡”
ውሻ - “ታዲያ፣… አሁን ለምን አንድ አዲስ ሥራ አንጀምርም?”
አህያ - ‹‹ይሻለናል፡፡ የራስን ሥራ የመሰለ ነገር የለም፡፡ ግን፣ የዚህን አገር ነገር እንተውና ወደ ሌላ አገር እንሂድ፡፡ አንተም ዘበኝነትህን እኔም ሸክሜን በነፃነትና በምቾት እንሥራ አለው፡፡
በዚህ ውይይት መሰረት፣ ውሻና አህያ፣ ተይይዘው ወደ ሌላ አገር ተሰደዱ፡፡
እዚያ አገር እንደ ደረሱ፣ ጊዜ ሳያጠፉ፣ ብዙ ቦታ ሥራ ጠየቁ፡፡ ያገኙት ምላሽ ግን፣ እንደ ቀድሞው ነው፡፡ ያው ዘበኝነትና ያው ሸክም ነው፡፡ አዘኑ፡፡ ‹‹ወደ ዱሮ ጌቶቻችን ሄደን፣ ወደ ሥራችን እንዲመልሱን እንጠይቃቸው›› አለ አንዱ፡፡
‹‹መልካም ሀሳብ ነው፤ ወደነሱ ብንመለስ ይበጀናል›› አለ ሌላኛው፡፡
ተያይዘው ወደ ዱሮ ጌቶቻቸው ሄዱ፡፡
የዱሮ ጌቶቻቸው ግን፣ እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፡- ‹‹አይ ዘገያችሁ፡፡ ሌሎች ሥራ የራባቸው እንስሳት፣ በቦታችሁ ገቡባችሁ፡፡ እናም ሌላ ቦታ ሄዳችሁ ሞክሩ›› በሚል ምላሽ ተሰናበቱ፡፡ አዝነው ጎዳና ወጡ፡፡
* * *
አገርክን አትልቀቅ፡፡ የባሰ አገር አለ፡፡ ጠላ አለ ቢሉህ - ውሃ ረግጠህ አትሂድ፡፡ ይህ እውነት፣ ባህል ያጠመቀው፣ ታሪክ ያቆየው ሀቅ ነው፡፡ የምንጊዜም ችግራችን፣ የቆየውን አጠንክሮ አለመያዝና አዲሱን በአግባቡ መርምሮ አለመያዝ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ሁለቱንም አጣጥሞ መጓዝ፣ ወድደን የምንዳክርበት ግዴታችን ነው፡፡ ግን እጣፈንታ አይደለም፡፡ አማራጭ መንገዶችን ማጤን ወግ ነው፡፡ ወደፊት ለመሄድ፣ የኋላችንን ማስተዋል ግድ ይለናል፡፡ አገራችን፣ አሁንም በስደትና በመፈናቀል የተያዘች ናት፡፡ በሚገርም ሁኔታ፣ አገራችን መስቀለኛ መንገዷ ላይ፣ አበሳዋን እያየች ናት፡፡
በክፉ ዘመን ደግሞ፣ የሰው ሁሉ ስሙ አበስኩ ገበርኩ ነው፡፡
‹‹እውነትን ፍለጋ በቆፈርነው ምድር፣
እህል ዘራንበት በልተን እንድናድር››
ዞሮ ዞሮ፤
‹‹በእንጉሥ ፍርፋሪ የፋፋን ትል፣
አሳ አገኘችና፣ ቅርጥፍ!
አሳ አጥማጆች እሷን ቅርጥፍ!
ሆድን ሞልቶ እንደ ስልቻ፣
በልቶ ለመበላት ብቻ››
ይለናል ሐምሌት፡፡
ጉዞህ ለከርሞ ከሆነ፣ ጤፍ ዝራ፡፡
ጉዞህ የአምስት ዓመት ከሆነ፣ ባህር ዛፍ ትከል፡፡
ጉዞህ የዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር!

Read 9808 times