Saturday, 12 October 2019 12:10

ድምፃዊው ሻምበል ብርቅነህ ኡርጋ አረፈ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በ1941 ዓ.ም ከአባቱ ከአቶ ዑርጋ ጂጆና ከእናቱ ከወ/ሮ አበበች ካሳ በቀድሞው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዲላ ከተማ የተወለደው ሻምበል ብርቀነህ ዑርጋ፣ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በዲላ አፄ ዳዊት ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በናዝሬት አፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት ከተከታተለ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የቀድሞ የምድር ጦር ኦርኬስትራ ሻለቃ ውስጥ በድምፃዊነት ተቀጠረ:: በኋላም በነበረው ብሩህ አዕምሮና ታታሪነት ባሳየው ውጤት የመኮንንነት ኮርስ ዕድል አግኝቶ፣ በሆለታ ጦር አካዳሚ በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ተረመቀ፡፡
በሙዚቃው ዓለም በዜማና በግጥም ደራሲነቱ በ1975 ዓ.ም በፊሊፕስ አሣታሚነት የተሠራው “አትሸኟትም ወይ” የሚል የሙዚቃ ካሴት አሳትሞ ለህዝብ አቅርቧል፡፡ ከዚሁ ካሴቱ ውስጥ ‹‹ፍቅር አገርሽቶ አሞኛል አሞኛል፣ ገና ልጅ ናት ጋሜ፣ አትሸኟትም ወይ›› የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚያም ባሻገር ከያኔው ሻምበል የተለያዩ ግጥምና ዜማዎችን ለተለያዩ ከያንያን የሰጠ ሲሆን፤ በሬዲዮ በቴሌቪዥንና በመድረክ ላይ ሥራዎቹን በማቅረብ ይታወቃል፡፡ በተለይም የሀገር አንድነት አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት በየጦር ግንባሩ በመሄድ ከመሰሎቹ ታምራት ሞላ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ጥላዬ ጨዋቃና ሌሎች ጋር በመሆን ለአገሩና ለወገኑ የሚገባውን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከግራ ከቀኝ ሀገሪቱ በጠላት በተከበበችበት ወቅት…
ሴራው ይከሽፋል ይከሽፋል ዛሬ
ኢትዮጵያ ሀገሬ
አድማው ይከሽፋል ዛሬ›› እያለ አዚሟል፡፡
በ1970ዎቹ መጨረሻ ወደ ቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን ተጉዞ ትምህርቱን የተከታተለው ሻምበል ብርቅነህ ዑርጋ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጀርመንኛን ማቀላጠፉ ብዙ ባልንጀሮቹን ያስደነቀ እንደነበር ከሥራ ባልረደቦቹ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል:: በምድር ጦር ኦርኬስትራ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገለው ሻምበል ወርቅነህ፤ ሲሆን ኮሎኔል ለማ ደምሰውን ተክቶ በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ የኦርኬስትራው ሃላፊ በመሆን አገልግሏል፡፡
ሻምበል ብርቅነህ በተለይ ጦርነቱ ከግራና ከቀኝ ተፋፍሞ፣ ሀገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ለሀገሩ አንድነትና ልዕልና በየምሽጉ ውስጥ ኑሮውን ባደረገበት ዘመን ያቀነቀነው ዜማ፤ በሣምንቱ ይካሄድ በነበረው የዘፈን ምርጫ ወቅት ያለማቋረጥ ይመረጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡
‹‹በረሃ ነው ቤቴ፣ የቀበሮ ጉድጓድ
ቤተሰቤን ሳላይ ሳይናፍቀኝ ዘመድ
ትጥቄንም አልፈታ ወገቤን አሥሬ
ለሀገሬ ልሰዋ ለሀገሬ ልሰዋ አለብኝ አደራ››
የሚለው ከአድማጮች ልብ ፈጽሞ የማይጠፋ ነው፡፡
ሻምበል ብርቅነህ በ1983 ዓ.ም የሻለቅነት ማዕረግ የሚያስገኘውን ኮርስ ካጠናቀቀ በኋላ ከስርዓቱ ጋር በተፈጠረበት ችግር፣ እሥራትና ቅጣት ገጥሞት ወደ ሰሜን ጦር ግንባር እንደ ቅጣት የተላከ ቢሆንም መንግሥትና ሀገር የገቡበት ችግር አስገድዶ በነበረ ወቅት ሻምበል ብርቅነህም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ፤ ከቤተሰቦቹ ጋር በመቀላቀል በመንፈሳዊ አገልግሎትና ህይወት ኑሮውን ቀጥሏል፡፡
በሕይወት ዘመኑ ዘጠኝ ልጆችን ያፈራው ሻምበል ብርቅነህ ዑርጋ ባለፉት ጥቂት ወራት ባደረበት ህመም፣ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡  

Read 6904 times