Saturday, 12 October 2019 12:00

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት ኢትዮጵያውያንን አስደስቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 ‹‹ክብሩ የአገር ነው፤ እንኳን ደስ ያለሽ እናት አገር ኢትዮጵያ›› - ፕ/ት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

             ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፋቸው በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስደስቷል፡፡ ከ302 የኖቤል የሰላም እጩዎች ጋር ተወዳድረው ያሸነፉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ ለሚሰሩት ሥራ ትልቅ ብርታት እንደሚሆናቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሽልማት ውጤት ለማወቅ ከተፈጠረብኝ ጉጉት የተነሳ እንቅልፍ እንኳን ሳልተኛ ነበር ስጠባበቅ የነበረው ያለው ጦማሪና መምህር ስዩም ተሾመ፤ ጠ/ሚኒስትሩ በማሸነፋቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሸነፈው ብሏል፡፡ 70 ሺህ ሰው የተገበረበትን የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት፣ ወደ ሥልጣን በመጡ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ መፍታታቸው ጥቅሙ ከኛ ይልቅ ለውጭ አገር ሰዎች ነው የተገለጠው የሚለው ስዩም፤ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤታማ ስራ እኛ ኢትዮጵያውያን ሳይገባን፣ የአለም ሕዝብ ገብቶታል፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ዋጋ ሳንሰጠው የአለም ሕዝብ ዋጋ ሰጥቶታል፤ የኖቤል የሰላም ሽልማቱ እኛም ወደ ቀልባችን እንድንመለስና አይናችንን ገልጠን እንድንመለከት ያደርገናል›› ብሏል፡፡ የቀድሞው የፓርላማ አባልና የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማን አህመድ በበኩላቸው፤ ዜናውን ስሰማ ሽልማቱን ራሴ ያገኘሁት ያህል ነው የተሰማኝ ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ አለም ዋጋ የሰጠውን የሰላም ስራ የሰሩ እንዲሁም ሞት የተፈረደባቸውን ሰዎች ሳይቀር ከእስር ቤት አውጥተው ብሩህ ተስፋ እንዲኖራቸው ያደረጉ የሰላም አርበኛ ናቸው ሲል አድናቆቱን ገልጿል -  አብዱራህማን፡፡
ይሄንኑ ሀሳብ የሚጋራው አክቲቪስትና ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬ ደግሞ በአገር እንድንኮራ የሚያደርግ ሽልማት ነው ብሏል። ‹‹አገራችን አሁንም ድረስ በተለያዩ የዜና አውታሮች ስሟ በጦርነት፣ በግጭትና በረሃብ እየተነሳ ባለበት ወቅት የአገሪቷ መሪ ለሰላም ያበረከቱት አስተዋጽኦ በአለም ፊት ሚዛን መድፋቱ፣ ለኢትዮጵያውያንና ለጠ/ሚኒስትሩ ትልቅ ድል ነው፡፡ ሽልማቱም ከዚህ ቀደም ለሰሩት እውቅና፣ ወደፊት ለሚሰሩት ደግሞ ማበረታቻ ነው›› ብሏል - ፖለቲከኛው፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከእስር ቤት ከተለቀቁ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆነው ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በበኩሉ፤ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ግልጽ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ያለኝ ቢሆንም በመሸለማቸው በእጅጉ ደስተኛ ሆኛለሁ›› ብሏል፡፡ ‹‹ብንወዳቸውም ባንወዳቸውም፣ ብንመርጣቸውም ባንመርጣቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸው ለአገር ክብር ነው፤ ደግሞሞ ይገባቸዋል›› ያለው ፖለቲከኛው፤ በዴሞክራሲ ገና ብዙ ቢቀረንም ጠ/ሚኒስትሩ ዴሞክራሲን የበለጠ ለማስፋት እንዲሰሩ ያበረታታቸዋል የሚል ተስፋ እንዳለው ገልጿል፡፡
በንግግሩ አወዛጋቢነት የሚታወቀው አክስቲቪስት ጃዋር መሀመድ በፌስቡክ ገፁ ባሰፈረው መልዕክት፣ ‹‹ጠ/ሚኒስትሩ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላም እንዲወርድ ለማድረጋቸው የተሰጠ ተገቢ እውቅና ነው›› ብሏል -  በአገር ውስጥ በርካታ የሰላም ስራዎች ገና እንደሚቀሩ በመግለጽ።
ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለጠ/ሚኒስትሩ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት፤ ‹‹ክብሩ የአገር ነው፤ እንኳን ደስ ያለሽ እናት አገር ኢትዮጵያ›› ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ታከለ ኩማ በበኩላቸው፤ ‹‹ሽልማቱ የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የሰላም፣ የይቅርታና የእርቅ ፍሬ ነው›› ብለዋል።
የደስታ መልዕክት ካስተላለፉት የአለም መሪዎች አንዱ የሆኑት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ለአፍሪካና ለሌሎች አገራት ምሳሌ ነው›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት መሀመድ ቡሃሪ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሱዳኑ ጠ/ሚር አብደላ ሃሞዶክ፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ዛይድ ፈጥነው ለጠ/ሚኒስትሩ የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት ካስተላለፉ መሪዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
‹‹የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ሽልማቱን በተመለከተ በፌስቡክ ገፁ ባሰራጨው መግለጫ፤ ‹‹ይህ እውቅና የተሰጠው ጠ/ሚኒስትሩ በዋናነት ለሚያራምዱት የመደመር እሳቤ ነው›› ብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሰላም፣ ይቅርታና እርቅን የፖሊሲያቸው ቁልፍ አቅጣጫ ማድረጋቸውን የጠቆመው ጽ/ቤቱ፤ በሺህ የሚቆጠሩ እስረኞች መለቀቃቸው፣ በውጭ አገር በፀረ ሽብር ሕጉ ተከሰው የነበሩ የሚዲያ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በምህረትና በይቅርታ ወደ አገራቸው መመለሳቸው፣ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱ፣ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ በተፃራሪ ሃይሎች መካከል እርቅ መመቻቸቱ እንዲሁም የእርቅና ሰላም ኮሚሽን መቋቋሙ… ዋነኛ ስኬቶች ናቸው›› ብሏል
በክፍለ አህጉሩ ሁለት አስርት አመታት ያስቆጠረውን የኢትዮ - ኤርትራ ጠብ በእርቅ መፍታታቸውና በአገራቱ መካከል አዲስ የትብብር እድሎችን መክፈታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር እሳቤ ለቀጠናው መረጋጋትና ውህደት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ›› ያለው ጽ/ቤቱ፤ ለዚህም በሱዳን በተካሄደው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተጫወቱትን ሚና በመጥቀስ፤ በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል የሚታዩ ልዩነቶችን ለማስታረቅ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑንም አክሎ ገልጿል፡፡
‹‹አለም እነዚህንና ሌሎች ስኬቶቻቸውን ተገንዝቦ፣ የኖቤል ሽልማትን በመስጠት አክብሯቸዋል፤ ሽልማቱ ለሰላም የተሰጠ በመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከሰላም ጎን እንዲቆሙ ጥሪ እናቀርባለን›› ያለው የጠ/ሚኒስትሩ፣ ጽ/ቤት፤ ‹‹ድሉ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ነው›› ብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸነፉ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ሲሆኑ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከዛሬ 81 ዓመት በፊት በ1938 (እ.ኤ.አ) በእጩነት ቀርበው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአፍሪካ በስልጣን ላይ እያሉ የኖቤል ሽልማት ካገኙ መሪዎች መካከል የደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ በ1993 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያሸነፉ ሲሆን ከሳቸው ጋር በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓትን ለማስቆም ቁርጠኛ አቋም የወሰዱት ዴ ክለርክም የሽልማቱ ተቋዳሽ ነበሩ፡፡ የግብጹ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት በበኩላቸው፤ ግብጽ ከእስራኤል ጋር ለዘመናት የነበረባትን ውዝግብ በሰላም በመፍታታቸው ከወቅቱ የእስራኤል ጠ/ሚኒስትር ማንቻም ቤጊን ጋር በ1978 ዓ.ም የሰላም የኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸው ተዘግቧል::
በ2011 እ.ኤ.አ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የሽልማቱ አሸናፊ ነበሩ፡፡
በአለም ቀዳሚውና ከፍተኛ ክብር ያለው የኖቤል ሽልማት፤ እ.ኤ.አ ከ1901  ጀምሮ እስከ ዛሬ ለ133 ግለሰቦችና ተቋማት ሽልማቱ ተሰጥቷል፡፡

Read 7557 times