Saturday, 12 October 2019 11:59

ኢትዮጵያ ‹‹የተስፋ አገር››፣ ኖቤልም ‹‹የተስፋ ሽልማት››!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያ፣ ብርቅና ትልቅ አገር ናት፡፡ ትንሽ ሰው አንሁን፡፡


             የኖቤል ሽልማት፣ እንደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ሁለት መልክ አለው፡፡ በአንድ ፊት፣ ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ደረጃ የተመዘገበ፣ የድንቅና ብርቅ ታሪክ ባለቤት ናት፡፡ የኖቤል ሽልማትም፣ እንደ ልብ የማይገኝ ብርቅ ሽልማት ነው፡፡ በልባም ጥረት ግሩም ውጤቶችን በማስመዝገብ፣ በዓለማቀፍ መድረክ ጐልቶ የሚታይ ታሪክ በመስራት የሚመጣ ነው፡፡
በሌላ ፊት ግን፣ ኢትዮጵያ የተስፋ አገር ናት፡፡ ኖቤልም፣ የተስፋ ሽልማት፡፡ ኢትዮጵያ ከቀድሞ ታላቅነቷ የሚበልጥ ሌላ አዲስ ታሪክ ለመስራት፣ ወደ ላቀ ከፍታ ለመመንደግ፣ ልዩና እምቅ አቅም እንዳላት የሚታመንባት አገር ናት፡፡ ከግሪክ የጥንት ታሪክ ፀሐፊ ከሄሮዶትስ ጀምሮ እስከ ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎች ድረስ፣ ከእስራኤል ከግብጽና ከሮም ነገስታት፣ የአይሁድና የክርስትና መሪዎች እንዲሁም ከነብዩ መሐመድ መልእክተኞች ጀምሮ፣ እስከ መካከለኛው ዘመን ሰባኪያንና አሳሾች ድረስ፣ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የስልጣኔ፣ የብልጽግና ምንጭ እንድትሆን፣ በብዙዎች ዘንድ የምትጠበቅ፣ የሚመኙላትና የሚተነብዩላት አገር ነበረች:: ይህ ልዩ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በአስደናቂው የአድዋ ድል ታድሶ ነው፣ ወደ 20ኛው ክፍለ ዘመን የተሻገረው፡፡
የአፍሪካ የነፃነት አርአያና ፋና እንድትሆን ብቻ ሳይሆን፣ በዓለማቀፍ ደረጃ - በሊግ ኦፍ ኔሽንስና በዩኤን በኩል ጭምር፣ ለዓለም ሰላም አለኝታ እንድትሆን ተስፋ የተጣለባት አገር ናት:: ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የኖቤል ሽልማት እጩ ሆነው መቅረባቸውም፣ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ተስፋ ይመሰክራል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ መቁረጥ የለም፡፡ ከቀድሞ ታሪኳ በተጨማሪ፣ አዲስ የላቀ ታሪክ እንደምታስመዘግብ፣ ለእልፍና እልፍ አመታት፣ በየዘመኑ የሚነገርላት የተስፋ አገር ናት - ኢትዮጵያ፡፡
የኖቤል ሽልማትም፣ የተስፋ ሽልማት ነው፡፡ በጥረት ለተመዘገበ ውጤትና በጽናት ለተሰራ ታሪክ፣ በአክብሮት የሚቀርብ ሽልማት እንደመሆኑ መጠን፣ በዚያው ልክ ‹‹የተስፋ እዳም›› ነው - የኖቤል ሽልማት፡፡ አድናቆትም፣ ማበረታቻም ነው፡፡
ድንቅ ውጤትን እያሞገሰ፣ ለላቀ አዲስ ውጤት፣ ከባድ የኃላፊነት ስሜትን ያሸክማል - ወደፊት የላቀ አዲስ ታሪክ የመስራት ኃላፊነትን በአደራ እየሰጠ፣ ለትጋት እምነት ይጥልብሃል፣ ስኬትን ተስፋ በማድረግ፡፡
- “በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ” እየተናቀ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ፀጋ ናት፡፡ ሰርተን  የፈጠርናት ሳትሆን፣ በመታደል ያገኘናት ድንቅ ስጦታ መሆኗን አለመገንዘባችን ጐዳን፡፡
- በዓለም ዙሪያ፣ በየዘመኑ፣ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች፣ “አገር” ለመፍጠር መከራ ያያሉ፡፡ የፈጠሯት አገር ገና በእግሯ ሳትቆም እየፈረሰች፣ በወረራና በጦርነት፣ በስርዓት አልበኝነትና በትርምስ - ሚሊዮኖች ያልቃሉ፡፡ ይሰደዳሉ:: ኑሮ አልባ ከርታታ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ አይነት አገር - አጦች ናቸው “ሚስኪን” የሚል ስያሜ የነበራቸው (ከኢትዮጵያ እስከ ፐርሺያ፣ ከአስራኤል እስከ ባቢሎን፣ ሚስኪን የሚለው ቃል ተመሳሳይ ትርጉም ነበረው - መጠለያ ያጣ አድራሻ ቢስ፣ መድረሻ ቢስ ማለት ነው፡፡)
በአለም ዙሪያ፣ ከጥቂት ጀግኖችና እድለኞች በስተቀር፣ አብዛኛው የሰው ልጅ፣ አገር የለሽ ነበር፡፡ አንድም በስርዓት አልበኝነት ኑሮው ተመሳቅሎ በአጭር እየተቀጨ ይረግፋል:: አንድም፣ ከስርዓት አልበኞችና ወረበሎች እየሸሸ፣ የተራራ እናት ላይ፣ ገደል ጫፍ ላይ ተንጠልጥሎ፣ ጐስቋላ አጭር እድሜውን ይገፋል፡፡ ጨለማ ዱር ውስጥ የአራዊት መጫወቻ ሆኖ ይቀራል፣ በሚያጥወለውል በረሃ በውሃ ጥም እየደረቀ፣ በየዋሻው በእልፍ የበሽታ ዓይነት እየወደቀ ያልቃል፡፡
አልያም፣ መጠጊያና መጠልያ ፍለጋ፣ “አገር እና ስርዓት ተፈጥሯል” ወደተባለበት አቅጣጫ ይሰደዳል፡፡ ነገር ግን፣ “አገርና ስርዓት” እንደልብ አይገኝም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡ ብርቅዬ ነበር::
አገር ሆኖ ለረዥም ዓመታት መዝለቅ፣ እንደልብ አይገኝም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ:: ብርቅዬ ነበር፡፡ አገር ሆኖ ለረዥም ዓመታት መዝለቅ፣ እንደ ተዓምር ነው ተፈልጐ የማይገኝ አይነት፡፡
ለሺ ዓመታት በህልውና የሚቀጥል አገርማ፣ ምናለፋችሁ፣ በጣት የሚቆጠሩ ስሞች ብቻ ናቸው የሚጠቀሱት፡፡ ብዙዎቹ አንጋፋና አውራ አገራት ፈራርሰዋል፡፡ ስማቸው ጭምር ተረስቷል፡፡ አንዳንዶቹም፣ በአሸዋ ስር ተቀብረው፣ ምልክታቸው እንኳ ጠፍቶ፣ እንደ ተረት ብቻ የሚወራላቸው ሆነው ቆይተዋል - እንደነባቢሎን፡፡
በህልውና ከዘለቁት ጥቂት አገራት መካከል ናት ኢትዮጵያ፡፡  ከሞላ ጐደል፣ በወረራ ስትንበረከክ፣ በነፃነት፣ ሺ ዓመታትን ያስቆጠረች እስከዛሬም የዘለቀች አገር ማን ነው ቢባል፣ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሌላ አገር የለም - ኢትዮጵያ ናት፡፡   
ይሄ፣ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ፣ አገር ለመፍጠር፣ በህልውና ለማቆየት ሲሉ ብዙዎች ተሰቃይተዋል፡፡
ለተወሰነ ጊዜ ሲሳካላቸው፣ የዚያኑ ያህል ተደስተዋል ሲፈርስ እንደገና ሀ ብለው እየገነቡ:: ከዘመን ዘመን፣ ለህልውና መከራ ያያሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን፣ አገር ለመፍጠር ሳይሰቃዩ፣ ገና ድሮ ተፈጥራ በህልውና የቆየች ትልቅ አገር ይዘው፣ አገርን ይበልጥ በማሻሻል ላይ የማተኮር ሰፊ እድል አግኝተዋል፡፡ ወደተሻለ ከፍታ፤ በስልጣኔ ጐዳና እየተሻሻለች እንድትገሰግስ የማድረግ በቂ ጊዜና አቅም ይኖራቸዋል (ሌላው ዓለም፣ አቅምና ጊዜውን ሁሉ የሚያውለው አገርን በመመስረት ላይ በነበረበት ወቅት ማለት ነው)
ታዲያ፣ ኢትዮጵያ ትልቅና ብርቅ ፀጋ አይደለችምን? የከበረች ስጦታ ናት፡፡ አንደኛው ስህተት፣ የከበረች ድንቅ ፀጋ መሆኗ አለመገንዘብ ነው፡፡ የአላዋቂነት ነገር ከዚያም የባሰ የማጣጣልና የማጥላላት ክፋት አለ፡፡
ሁለተኛው ስህተት፣ ትልቅና ብርቅ ፀጋነቷን ከማክበርና ከማድነቅ ይልቅ፣ ስጦታነቷን በምስጋናና በፍቅር ተቀብሎ፣ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገር ለመስራትና ለመጨመር ኃላፊነት ከመውሰድና በትጋት ከመጣር ይልቅ፣ ዛሬ አገሪቱን የፈጠሯት ያቆሟት ይመስል፣ የኩራት ባለቤት ለመሆን፣ የክብር መንፈስ ለማግኘት፣ ይራኮታል - ያልነበረበትንና የማያውቀውን ታሪክ በሽሚያ የራሱ ማድረግ የሚችል ይመስለዋል - “እኛ” የሚል ቃል በመደጋገም ብቻ ወይም በሃይማኖት ተከታይነትና በዘር ቆጠራ አማካኝነት ተጠግቶ “ብጋራ” ለማለት፣ የጥንት ሰዎች የሰሩትን ታሪክ፣ “በርቀት ለመውረስ”፣ “በጊዜ መዘውር” የኋሊት ተመልሶ፣ ስሙን በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለማስገባት ያምረዋል፡፡
ከመቶ እና ከሺ ዓመታት በፊት በሕይወት ከነበሩ ሰዎች እንኳ፣ “በአውቶማቲክ” የታሪክ ባለቤት አይሆኑም፡፡ ከወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል፤ አንዱ አዋቂ፣ ሌላኛው አላዋቂ፣ አንዲ ጥበበኛ፣ ሌላኛዋ ነገረኛ፣ ታላቅየው ሃኬተኛ፣ ታናሽየዋ ሰነፍና ገልቱ ትሆናለች፡፡
በቤተሰብ ውስጥ እንኳ፣ አንዱ የሌላውን ብቃት፣ አንዱ የሌላኛዋን ትጋትና ስኬት አየር ባየር መጋራትና መውረስ አይቻልም፡፡
ትክክለኛውና ቀናው መንገድ፣ አገርን ፈጥረው አንቅንተውና ጠብቀው ለማቆየት በትጋት የጣሩ፣ በጥበብ የሰሩ፣ በብቃት ስኬትን ያስመዘገቡ ሰዎችን (በስም ብናውቃቸውም ባናውቃቸውም፣ ታሪካቸው ቢመዘገብም ባይመዘገብም)፣ አኩሪ ስራቸውን በአድናቆት ማክበር፣ በምስጋና ስጦታቸውን መቀበል በዚህም የመንፈስ ልጆቻቸው መሆን፣ በተራችንም፣ እያንዳንዳችን፣ ፋይዳ ያለው ነገር ለመስራት፣ አዲስ ትልቅ ታሪክ ለመጨመር፣ በእውቀትና በጥበብ መትጋት ነው!

Read 7766 times