Saturday, 12 October 2019 11:58

በትግራይ የተቃውሞ ሠልፍ ተካሄደ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 በትግራይ ክልል በሽረ አዲ ዳዕሮ ከተማ ነዋሪዎች በክልሉ እየተፈፀመ ነው ያሉትን መጠነ ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግር በመቃወም ሠላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፤ አረና ፓርቲ ‹‹ሠልፉ ህዝቡ መብቱን የጠየቀበት ነው›› ብሏል፡፡
በሠላማዊ ሰልፉ ላይ እስከ 15ሺህ የሚገመት የከተማዋ ነዋሪ መሳተፉ የተገለፀ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች በስም የጠቀሱት አንድ የፖሊስ ኃላፊ የፈፀሟቸውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ለማጋለጥ የተጀመረና ‹‹ፍትህ እንፈልጋለን፣ መልካም አስተዳደር እንፈልጋለን›› በሚል ተቃውሞ የተጠናከረ ነው ብለዋል - ‹‹የአረና›› ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታ፡፡
‹‹ህዝቡ በሠላማዊ ሰልፉ ያሉበትን የአስተዳደር በደሎች በይፋ መግለፁ የሚበረታታ ነው›› ያሉት አቶ አብርሃ፤ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችም ዜጐች ተመሳሳይ ተቃውሞዎችን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለሰሞኑ የተቃውሞ ሠልፍ ዋነኛው መነሻ፣ በመንግስት የስራ ኃላፊነት ላይ የሚገኝ አንድ የሳጅን ማዕረግ ያለው ግለሰብ፣ ከ10 በላይ የሚሆኑ ባለትዳር ሴቶችን አስገድዶ መድፈሩን ተከትሎ በፍ/ቤት ጥፋተኛ ነው ተብሎ ቢፈረድበትም፣ የፍርድ ጊዜውን ሳይጨርስ መፈታቱ  ነው ተብሏል፡፡
በሠልፉ ላይ የከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የወጡ ሲሆን፤ ‹‹እየደረሰብን ላለው በደል ድምፃችን ይሰማ›› የሚለው አንዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Read 8510 times