Print this page
Saturday, 12 October 2019 11:54

ነገ ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ከመንግስት ምላሽ እየተጠበቀ ነው

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ባለ አደራ ም/ቤት፣ በነገው ዕለት ለጠራው ሠላማዊ ሰልፍ ከመንግስት ምላሽ እየጠበቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ትላንት ም/ቤቱ በተቃውሞ ታጅቦ በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለማካሄድ ባቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተቃውሞ የሚያነሳቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በዝርዝር ያስታወቀ ሲሆን በገዢው ፓርቲና ከፓርቲው ውጭ ባሉ ፅንፈኞች፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄዎች መጠለፋቸውን መቃወም በግንባር ቀደምትነት ተጠቅሷል፡፡   
በሀሳባቸውና በፖለቲካ ልዩነታቸው ምክንያት ብቻ በአዲስ አበባና በክልሎች ታስረው የሚገኙ “የህሊና እስረኞች” ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እንጠይቃለን ብሏል - ባለ አደራ ም/ቤቱ:: አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ ይዞ መውጣት  ህገ-ወጥ መሆኑን የሚደነግገው ህግ እንዲሰረዝም  ጥያቄ እናቀርባለን ያለው ም/ቤቱ፤ መንግስትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡና ለሀይማኖት ተቋማት ጥበቃ እንዲደረግ እንደሚጠየቅ ታውቋል፡፡  
መንግስት የዋጋ ግሽበትና የስራ አጥነት ችግር ላይ አተኩሮ እንዲሠራ እንዲሁም በአዲስ አበባ “ልዩ መብትና ጥቅም አለን” በሚሉ ቡድኖችና ግለሰቦች እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት እንዲያስቆም በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ይጠየቃል፡፡
በነገው ዕለት በተጠራው ሠላማዊ ሰልፍ ላይ እንዲገኙ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለባህል መሪዎች፣ ለሀገር ሽማግሌዎችና ተጽእኖ ፈጣሪዎች ጥሪ እንደተደረገላቸው የም/ቤቱ አባል አቶ ሔኖክ አክሊሉ በመግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡  
ሰላማዊ ሠልፉን ለመታደም የሚመጡ አካላት ማድረግ የሌለባቸው ነገሮች በሚል ም/ቤቱ በሰጠው ማብራሪያ፤ ሁሉም ተሳታፊ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በጨዋነት ሃሳቡን እንዲገልጽ እንዲሁም የማንንም አስተሳሰብ፣ ቋንቋና እምነት ከማንጓጠጥና ለጠብ ከመጋበዝ እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በነገው ዕለት ለጠራው ሠላማዊ ሠልፍ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ዕቅውና ለማግኘት ቀደም ብሎ ደብዳቤ ማስገባቱን የገለጸው ም/ቤቱ፤እስከ ትላንት ምሽት ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡ እኛ ደንቡን ተከትለን አመልክተናል ያለው የም/ቤቱ ሰብሳቢ እስከንድር ነጋ፤መስተዳድሩ ምላሽ አለመስጠቱ  በህጉ መሠረት እንደተፈቀደ ይቆጠራል ብሏል፡፡ ዛሬ ወይም ነገ መመሪያ ይሰጣል ብለው እንደሚጠብቁ የገለጸው ጋዜጠኛ እስክንድር፤መስተዳድሩ በጠላትነት ስለሚመለከተን የዕውቅና  ደብዳቤ ሊሰጠን ፈቃደኛ አይደለም ብሏል፡፡ “ይሄ ማለት አሠራርን ጥሷል ነው እንጂ መስተዳድሩ ከለከለን አያስብልም፤ በዝምታው መፍቀዱን አረጋግጠናል” በማለት አብራርቷል - ጋዜጠኛ እስክንድር፡፡ የከተማው ነዋሪዎች ምንም ሳይሰጉ ጥያቄያችንን መነሻ በማድረግ በሠላማዊ ሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል - ባለአደራ ም/ቤቱ፡፡

Read 1016 times