Print this page
Tuesday, 08 October 2019 10:22

ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም (የትውልድ መስታወት ወይስ የግለሰብ ገድል?)

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

                             
             በዚህ ክረምት፤ የአንባቢያንን ጥም የሚቆርጡ ድርሳናትን በብዛት ባንመለከትም፤ ፍሬ ያላቸው አንዳንድ ታሪክ ቀመስ መጻሕፍት፣ ለአመል ብቅ ብቅ ማለታቸው ግን አልቀረም:: ከኢሕአፓ የበላይ አመራር መካከል አንዱ በነበረው፤ መላኩ ተገኝ የተጻፈው “ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም” በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆን ይችላል፡፡ መጽሐፉ፤ በ300 የገጽ ብዛት፣ በ22 ምእራፍ የተከፋፈለ ነው፡፡ በየገጹ ድንቅፍቅፍ የሚያደርገንን የፊደል ግድፈት ስንታዘብ፤ የአርትኦት ሥራው  ደካማ እንደሆነ ቢገባንም፤ ግሩም የሆነው የአተራረክ ዘይቤ፣ ድክመቱ  እንዳይጋነንበት አድርጎታል፡፡  
በድርሳኑ ግንባር ላይ የተከተበው ርዕስ፤ በውስጡ ለቋጠረው ዳጎስ ያለ ቁምነገር የሚመጥን አይደለም፡፡ ከግለ ታሪክ ያለፈ፤ የሀገር ገመናን፣ ከላይ እስከ ታች ለአውደ ርዕይ የሚያቀርብ ሰነድ ነው፡፡ በመሆኑም፤ ለመጽሐፉ የተሻለ ርዕስ መጠቀም ቢቻል ኖሮ፣ የተሸከመውን የሀገር ታሪክ በወጉ መግለጽ ይችል ነበር፡፡
 ጸሐፊው፤ መጽሐፉ የግለሰባዊ ገድል ማንጸባረቂያ እንዳልሆነ፣ ገና ከእልፍኙ እንደዘለቅን በማስጠንቀቂያ አዘል መልእከቱ ይቀበለናል፡- “ይኽ መጽሐፍ፤ በመሠረቱ ትውስታ እንጂ የግል ታሪክ አይደለም፡፡ ደግሞም፤ ኢህአፓን ተንተርሼ ስለ ግል ሕይወቴ ለመጻፍ ታሪካዊ ተገቢነቱም መብቱም አለኝ ብዬ አላምንም፤” ይላል፡፡  
ይኽ ምንአልባትም፤ የግራ-ዘመም ርዕዮተ ዓለም ዋንኛ መገለጫ ከሆነው፣ ከቡድናዊ (collective) የልቦና ውቅር የሚመነጭ ነው:: ለጋራ አላማ፣ ለጋራ ርዕይ ራስን አሳልፎ የመስጠት ገድል፤ የግራ-ርዕዮተ ዓለም ቀኖና ስለሆነ፣ የግለሰቦች ጀብዶ፣ ከወል ታሪኩ ተነጥሎ መጋነን አይኖርበትም፡፡
የመላኩ ተገኝ ድርሳን፣ የያን ትውልድ ተጋድሎ፤ ከጥንስሱ እሰከ መቋጫው በቀላል ቋንቋ ነው የሚተርክልን፡፡ አብዛኞቹ ኹነቶች፣ በስሚ ስሚ የተቃረሙ ሳይሆን፤ ከራሱ ከታሪኩ ተዋናይ፣ እንደወረደ ነው የቀረቡት፡፡ በተለይ፤ በቄሳራዊው አገዛዝ ላይ ንቃቃት በመፍጠሩ ረገድ፣ ጉልህ ሚና የነበረውን የ1953 የመንፈቅለ መንግሥት ሙከራን ተከትሎ፣ የተጋጋመውን የተማሪዎች ንቅናቄ ዝግመተ ለውጥን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ዘውግ-ዘለል /meta-ethnic/ የሆኑትን ኢሕአፓንና መኢሶንን የወለደው የተማሪዎች ንቅናቄ፤ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ አድማስን፣ በተራኪው የሕይወት ተሞክሮ አማካኝነት እንረዳለን፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ከናኙት የታሪክ አንጓዎች መካከል፤ ውይይት ይጋብዛሉ ብዬ ያስብኳቸውን ዋና ነጥቦች  ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
ያ-ትውልድ እንደ ዋዛ የተከለው ሰንኮፍ
 “የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በ1962 በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ የቀረበው የዋለለኝ ጽሑፍ፣ በብዙ ለጋ የ “ያ-ትውልድ” አባላት ልቦና ላይ ለማደር ጊዜ አልፈጀበትም ነበር፡፡ ይኽ የሀገራችንን የዘውጌ ማኅበረሰቦች በተንሸዋረረ መልኩ በመፈረጅ የሚታወቀው የዋለልኝ እሳቤ፤ ውሎ አድሮ እንደ ሀገር ለገባንበት ቅርቃር፣ የጎላ ሚና ተጫውቷል ቢባል፤ ከእውነታው ጋር መጋጨት አይሆንም፡፡
የዋለልኝ የተጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት፤ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን፤ በፀረ-እውቀት ዘይቤ፣ በቀጥታ ከማርክስ አስተምህሮት የተቀዳ ነበር፡፡ ማርክስ፤ በዲያሌክቲካል መንገድ፣ ተጻራሪ መደቦችን የገለጸበት አውድ፤ በቅጡ ሳይፈትሽ፣ የሀገራችንን የዘውጌ ማኅበረሰቦችን መፈረጂያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ትውልዱ፤ ግድ ያለው፣ ማርክሳዊ ቀኖና እንጂ፤ ሰፊውን ሕዝብ ያጎበጠው  ሁለንተናዊ የጉስቁልና ቀምበር አልነበረም፡፡
 ያ ትውልድ፤ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት መርምሮ፣ በጊዜው ለተንሰራፋው ፖለቲካዊ ምስቅልቅል፣ ዘመን ተሻጋሪ እሳቤዎችን የሚሰንቅበት፣ የእውቀት ንጣፍ እንዳልነበረው፤ ከዚህ ቀደም ለሕትመት ብርሃን በበቁ ድርሳናት ላይ በተደጋጋሚ ተወስቷል:: ይኽኛውም ድርሳን፤ በተዘዋራሪ የትውልዱን ችኩል ድምዳሜን፣ በአንዳንድ አጋጣሚ ሊመሰክርለን ይዳዳዋል፡፡ ለአብነት ያህል፤ ብሔራዊ ጭቆና በሚለው የተውሶ ጽንሰ ሀሳብን በመረዳት ረገድ፣ የትውልዱን ግልብነት በሚገባ  የምናወቀው በገጽ 122 ላይ ነው፤
 “በብሔር ጥያቄ ላይ የተጻፉት ሁለቱ ጽሑፎች ውይይት ቀስቅሰው፣ የተለያዩ ትርጓሜዎች ቢሰጡትም፤ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ፣ በተለይም፤ ኢትዮጵያ የብዙ ሕዝቦች አገር የሆነችና የእነዚህ ሕዝቦችም እኩልነት በሁሉም ረገድ መጠበቅ እንዳለበት ስምምነት ነበር፡፡ ከዚህ በተረፈ፤ ሌኒንም ሆነ ሌሎች ስለ ብሔር ጥያቄ የጻፏቸውን  እንኳን ልናነብ፤ ስለ መኖራቸውም ከዋለልኝ ጽሑፍ ነበር የተረዳነው፤ “ ይላል፡፡    
በርግጥ፤ የዋለልኝ ጽሑፍ ሰለባ ያደረገው፤ የያትውልድ ለጋ ወጣትን ብቻ አልነበረም:: ነፍጥ አንስተው ፣በረሃ የወረዱትም  አውዳሚ የጎሳ ድርጅቶች፤  እስትንፋሳቸውን ሲቀጥሉ የኖሩት፣ በዚህ ሐሳዊ ትርክት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን፤ በግልብ እሳቤው ከመደባበስ አላመለጥንም፡፡ እንደ ጥላ እየተከተለን ዙሪያ ገባችንን እያመሰቃቀለብን ይገኛል፡፡ መጽሐፉ፤ ከዚህ መሰሉ መሪር ሐቅ ጋር እንድንጋፈጥ፤ ቋስቋሽ ሊሆኑ የሚችሉ ኹነቶችን  በየምእራፉ ይደነቅርብናል፡፡
የተድበሰበሰው የኢሕአፓ እና የመኢሶን ቁርቋሶ
በኢሕአፓ እና በመኢሶን መካከል የነበረው መቃቃር፤ በታሪክ፣ በእውቀት ባህልና በሥነልቦና ማእቀፍ በአጥጋቢ ሁኔታ ካልተብራራ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ታሪካዊ ዳራዎቻችንን ለአብነት ብንመረምር አንኳን በጥንታዊ የጉልት ሥርዓት ውስጥ በአካባቢ ባላባቶች መካከል የነበረው የዜሮ ድምር ግንኙነት (የመጠፋፋት ቁርኝት)፤ በቀጥታ በሁለቱ ሀገራዊ ፓርቲዎች ላይ እንደተንጸባራቀ እንረዳለን፡፡ ኢሕአፓ እንዲኖር መኢሶን መጥፋት ነበረበት፤ በግልባጭሙ እንዲሁ፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች፣ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ነባራዊ ኹናቴ ይልቅ፤ ለማርክሲዝም ፍልስፍናዊ ቀኖና ባሳዩት ተላላነት ምክንያት ራሳቸውንም ሆነ ሕዝባቸውን ከአስፈሪ ቅርቃር ውስጥ ሊጨምሩት ችለዋል፡፡ ጸሐፊው፤ የኢሕአፓ እና የመኢሶን ድርጅቶች የቆመበትን ረግረግ ከመሄስ ይልቅ፤ ልዩነታቸውን በጣም አቃሎ ነው ለማቅረብ የሚሞክረው፡፡
እንደ እሳት ጎመራ ለመፈንዳት በቋፍ ላይ የሆነውን፤ የሕዝቡን አመጽ አስተባብሮ ወደ ድል ጎዳና የሚመራ፤ “የቫንጋርድ” ፓርቲን አስፈላጊነት፣ ኢሕአፓ አስቀድሞ የተረዳ ቢሆንም፤ በመኢሶን መሪዎች ዘንድ ይስተዋል የነበረው ዳተኝነት፤ ለመቃቃሩ ዋንኛ ምክንያት እንደሆነ፤ በገጽ 212 ላይ እንዲህ ሰፍሮ እናገኛዋለን፡-
“ዋነኛው ልዩነት ኢትዮጵያ ውስጥ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በመገምገም ላይ የተነሣ ነው፡፡ እኛ አብዮታዊ ሁኔታ አለ፤ ለአብዮት መነሣት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በነባራዊ ጠባዩ (objective conditons) በአገሪቱ ለዚኽ የተመቻቸ ሁኔታ አለ፣ ስለዚህ ሕዝቡን አደራጅቶና አስተምሮ የሚታገል አብዮታዊ የሆነ ድርጅት ያስፈልጋል አልን”
በርግጥ፤ የኢሕአፓ ውትወታ ውሃ የሚቋጥር ቢመስልም፤ የሁለቱን ፓርቲዎች ልዩነት፣ ወደዚህ  ቀጭን አጃንዳ ደረጃ ብቻ አውርዶ ለመተንተን መሞከሩ፤ የጸሐፊውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ይሆናል፡፡
ሂሳዊ ትንተናን ለማድረግ አለመድፈር
ጸሐፊው፤ እናት ድርጅቱ ኢሕአፓ ላይ የሚጨክን አንጀት እንደሌለው የምንረዳው፤ ምንም አይነት ጠንካራ ሂስ ለመሰንዘር አለመድፈሩን ስንታዘብ ነው፡፡ የኢሕአፓን ገድል በመዘርዘር ነው ጊዜውን የጨረሰው፡፡ ለቆምንበት ዘመን፤ ትምህርት ሊሆን የሚችል ሂሳዊ ትንተና ቀርቦ ቢሆን ኖሮ፤ ታሪኩን የበለጠ ምሉዕ ባደረገው ነበር፡፡ ኢሕአፓ በወቅቱ የነበረውን የጭቆና አገዛዝ ለመስበር ትልቅ ተጋድሎ ማድረጉ የሚካድ ባይሆንም፤ ድርጅቱ በግብር ይውጣ ያሳለፋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች፣ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የጣሉ ነበሩ፡፡ ከዚህም ውስጥ፤ የዚያድባሪ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የተከተለው የፖለቲካ አድርባይነት ሁሌም በክፉ የሚነሳ ነው፡፡
ኢሕአፓ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚለው ፖለቲካዊ ስሌት፤ ደርግ ለሀገር ሉአላዊነት ሲፋለም፤ በተጻራሪ ለመሰለፍ፣ መሬት ላይ ከነበረው እውነታ ይልቅ፤ የሩሲያን ተሞክሮ እንዳለ በመቅዳት፣ በጥቁር የታሪክ መዝገብ ላይ የሰፈረ ስህተትን ለመፈጸም  በቅቷል፡፡ በቅርቡ ለሕትመት ብርሃን በበቃው የአንዳርጋቸው ጽጌ “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር”  በሚለው መጽሐፍ ላይ ይህንን አስመልክቶ በግርጌ ማስታወሻ 332 ላይ ከገለጸው በጥቂቱ፡-
“የታሪክ ተመሳሳይነት መፈለግ ካስፈለገ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚቀርበው ቻይና በ1930ዎቹ ለነበረችበት ሁኔታ ነው፡፡ ኢሕአፓ ከሩሲያ ይልቅ ለሀገራችን ሁኔታ የሚቀርበውን የቻይና ታሪክ በምሳሌነት አልተጠቀመም፡፡ በሕይወት ያሉ የኢሕአፓ አመራሮች በወጉ መልስ ሊሰጡበት  የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡”   ይላል፡፡
የግርጌ ማስታወሻ
በታሪካዊ ጉድባዎቻችን ላይ አትኩሮታቸውን ያኖሩ ድርሳናት መታተማቸው ፋይዳቸው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ፤ ወርቃማ እድሎቻችን እንዴት እንደዋዛ  እያባከንን ካለንበት ዘመን ላይ እንደደረስን  በቅጡ ለመመርመር ይኽን መሰሉ የታሪክ ስንቅ ያስፈልገናል፡፡ የትላንት ውጣ ውረዶቻችንን የምናጠናው መልሰን፣ መላልሰን በከንቱ እንዳንዋጅባቸውና ነገን የምንሻገርበትን አስተውሎት ለመጎናጸፍ ነው፡፡
ጸሐፊው፤ በ“ያ ትውልድ” ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ከሆኑት አመራሮች መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን፣ ታሪኩ በድርሳን መልክ መሰናዳቱ፤ ጠቀሜታው ሁለንተናዊ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ፤ መጽሐፉ በግለ-ታሪክ ደረጃ ብቻ ታጥሮ የሚገለጽ ሳይሆን፤ የ“ያ ትውልድ”ን ገድልና ውድቀት ወለል አድርጎ የሚያሳይ የትውልድ መስታወት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

Read 1657 times