Tuesday, 08 October 2019 10:10

ህንድ በ18 ሚ. ዲያስፖራ ከአለማችን አገራት ቀዳሚ ሆናለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)


              ህንድ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ በውጭ አገራት የሚኖሩባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗንና አገሪቷ በመላው አለም የሚገኙ ህንዳውያን ዲያስፖራዎች ቁጥር በ2019 የፈረንጆች አመት 18 ሚሊዮን ያህል መድረሱን ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ዲያስፖራ ህንዳውያን የሚኖሩባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር አሜሪካ ናት ያለው መረጃው፤ በ2017 የፈረንጆች አመት ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ ብዛት 1.3 በመቶው የህንድ ዝርያ ያላቸው እንደሆኑ አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ የላቀ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ካቋቋሙት መካከል 8 በመቶ ያህሉ ህንዳውያን ዲያስፖራዎች እንደሆኑ የጠቆመው መረጃው፤ ጎግልና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ በርካታ ህንዳውያን በታላላቅ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዉስጥ በሃላፊነት እየሰሩ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡
በዲያስፖራ ብዛት ከአለማችን አገራት የሁለተኛነት ደረጃን የያዘችው ሜክሲኮ መሆኗን ያመለከተው  ተቋሙ፣ 11.8 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች በተለያዩ የአለማችን አገራት ውስጥ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡ ቻይና በ10.7 ሚሊዮን፣ ሩስያ በ10.5 ሚሊዮን፣ ሶርያ በ8.2 ሚሊዮን፣ ባንግላዴሽ በ7.8 ሚሊዮን፣ ፓኪስታን በ6.3 ሚሊዮን፣ ዩክሬን በ5.9 ሚሊዮን፣ ፊሊፒንስ በ5.4 ሚሊዮን እንዲሁም አፍጋኒስታን በ5.1 ሚሊዮን ዲያስፖራ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሶስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ እንደያዙም መረጃው ይጠቁሟል::
በአለማችን ከሚገኙ አጠቃላይ አለማቀፍ ስደተኞች መካከል ግማሽ ያህሉ በአስር አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ ያስታወቀው መረጃው፤ 19 በመቶው ወይም 51 ሚሊዮን ያህሉ በአሜሪካ እንደሚኖሩም ገልጧል፡፡
ጀርመንና ሳኡዲ አረቢያ 13 ሚሊዮን ያህል የሌሎች አገራት ዜጎች የሚኖሩባቸው ሲሆን ሩስያ 12 ሚሊዮን፣ እንግሊዝ 10 ሚሊዮን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ 9 ሚሊዮን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳና አውስትራሊያ እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን፣ እንዲሁም ጣሊያን 6 ሚሊዮን የሌሎች አገራት ዜጎች ይኖሩባቸዋል፡፡

Read 2135 times