Tuesday, 08 October 2019 09:58

የአገር አንድነትን ያለመው ‹‹ጊፋታ››

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 “በሀዘን ልቡ የተሰበረ ሀዘኑን ይተዋል፣ በከፍተኛ ቅያሜ ውስጥ ያለ ሰው በአገር ሽማግሌዎች ይታረቃል፡፡ ያስቀየመም ይቅርታ ይጠይቃል፤ የተቀየመም ቂሙን ትቶ ከልብ ይቅር ይላል፤ እዳ ያለበት ዕዳውን ሳይከፍል ጊፋታን አያከብርም--”
       
             ከዳሞታ ኪንግደም ዘመንና ከዚያም በፊት ከመስከረም 14 ቀን እስከ 20 ባለው አንዱ እሁድ በጉጉትና በከፍተኛ ዝግጅት በየዓመቱ የሚከበር የወላይታ የዘመን መለወጫ ነው - ጊፋታ፡፡ ዘንድሮም ለበርካታ ወራት ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቶ በልዩ ልዩ ትዕይንቶች ደምቆ ተከብሯል፡፡
“ጊፋታ”፤ ከአሮጌ ነገር ወደ አዲስ ነገር መራመድን፣ ከአሮጌ መንፈስ ወደ አዲስ መንፈስ መሻገርን የሚያመለክት ቃል መሆኑን የወላይታ አባቶች ይናገራሉ፡፡ ለጊፋታ ሰው ሁሉን ነገር አዲስ አድርጐ ይጠብቃል፡፡ ለምሳሌ በሀዘን ልቡ የተሰበረ ሀዘኑን ይተዋል፣ በከፍተኛ ቅያሜ ውስጥ ያለ ሰው በአገር ሽማግሌዎች ይታረቃል:: ያስቀየመም ይቅርታ ይጠይቃል፤ የተቀየመም ቂሙን ትቶ ከልብ ይቅር ይላል፤ እዳ ያለበት ዕዳውን ሳይከፍል ጊፋታን አያከብርም፤ ብድሩ የመጣው ከግልም ይሁን ከመንግስት ዕዳውን ጊፋታን ሊያከብር አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ መክፈልና ነፃ መሆን በወላይታ ባህል ግዴታ ነው፡፡ ቤተሰብ ለራሱም ሆነ ለልጆቹ አዲስ ልብስ ይገዛና በጊፋታ ዋዜማ ምሽት ወይም ሊነጋ ሲቃረብ የራሱንም ሆነ የልጆቹን ገላ ሙልጭ አድርጎ ያጥብና፣ አዲሱን ልብስ ይለብሳል፡፡
ይህ እንግዲህ ሰው በእርቅ ብድሩን በመክፈልና ገላውንም በመታጠብ፣ በአዕምሮ በአካልና በመንፈስ ነጽቶ አዲሱን አመት በጊፋታ ለመቀበል የሚያደርገው ሁለንተናዊ ንጽህና መሆኑን ነው የወላይታ አባቶች የሚያስረዱት፡፡ ከመንግስትም የሚጠበቅ ትልቅ ነገር አለ፡፡ በጊፋታ መንግስት አመቱን ሙሉ በየዘርፉ ሲያከናውን የከረመውን ሥራ፣ ለህዝቡ የሚያስገመግምበት ዕለት ነው:: መንግስት አጠቃላይ ሥራውን ለህዝቡ በማስገምገም፣ ግብአት የሚሰበስብበት፣ በጉድለቱ የሚወቀስበት፣ በመልካም ስራው ደግሞ የሚወደስበት ሲሆን ለአዲሱ አመት የያዘውንም ዕቅድ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግበት፣ በማህበረሰቡ ትልቅ ቦታና ክብር ያለው የዘመን መለወጫ ቀን ነው - ጊፋታ፡፡
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳገቶ ኩምቢ፤ ጊፋታ ለወላይታ ህዝብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ስነልቦናዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ አገራዊ አንድነትን በማምጣት ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲኖረው በማሰብ፣ ከወራት በፊት በዞኑ መንግስት በኩል ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ጊፋታ የእርቅ፣ የሰላምና የይቅርታ በዓል እንደመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ቂምና ጥላቻን ለአሮጌው አመት ትተው፣ በአዲስ መንፈስ በወላይታ በመታደም በዓሉን እንዲያከብሩ ከወትሮው የተለየ ጥሪ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
እንደተለመደው በደብዳቤ ሳይሆን ራሳቸው አቶ ዳገቶ፣ ልዑካን ቡድናቸውን ይዘው በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ በአካል በመሄድ፣ የግብዣ ጥሪውን እንዳደረጉ ተጠቁሟል፤ “ጊፋታን በውቧ ወላይታ ተገኝታችሁ፣ በፍቅርና በአንድነት አክብሩ፤ ሀገራዊ አንድነታችን በጊፋታ ይጠናከር” በማለት፡፡  ይሄም ጥረታቸው የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ በመስቀል በዓል እለት በጊፋታ ዋዜማ፣ በወላይታ ሰማይ ሥር ያልተገኘ እንግዳ አልነበረም፡፡ የየክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞንና የወረዳ ሃላፊዎች፣ የባህል አምባሳደሮች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ሙዚቀኞችና አርቲስቶች እንዲሁም ጋዜጠኞች በከተማዋ ታድመው ነበር፡፡
መስከረም 16 ቀን አመሻሽ ላይ በሶዶ ከተማ አሮጌ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በምትገኘው ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን፣ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የደመራ በዓል በድምቀት የተከበረ ሲሆን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ መስቀልና ጊፋታ የተለያዩ በዓላት ቢሆኑም መስቀል ከወላይታና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አልፎ በአለም ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገበ በመሆኑ፣ በከተማዋና በዞኑ በድምቀት እንዲከበር ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የነበሩባትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች አዲሱ አመራር በሂደት በመፍታት፣ ህዝበ ክርስቲያኑ ደስ ብሎት አምልኮውን እንዲከውን ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳገቶ፤ ያልተፈቱ ችግሮችም ካሉ፣ በየደረጃው እንደሚፈቱ ቃል በመግባት ለምዕመኑ መልካም በዓልን ተመኝተዋል፡፡
ሥርዓተ ደመራውን ሲመሩ የነበሩት የደብሩ አባት፤ የዞን አስተዳዳሪው ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለምዕመኑ የሰሩትን ዘርፈ ብዙ መልካም ስራዎች በዝርዝር አቅርበው ቡራኬና ምርቃት የሰጡ ሲሆን ህዝቡም ለወጣቱ አስተዳዳሪ ያለውን ክብርና አድናቆት በዕልልታ፣ በጭብጨባና በፉጨት ገልጾላቸዋል፡፡
በዕለተ መስቀል በጊፋታ ዋዜማ ምሽት ዞኑ፤ ለከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ለአባ ገዳዎች፣ ለባህል አምባሳደሮችና በአጠቃላይ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ የእራት ግብዣ በሌዊ ሪዞርት ያደረገ ሲሆን በምሽቱም የህወሓትና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ሃላፊና የአማራ ክልል ተወካዩ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ በርካታ የክልል አመራሮችና ሌሎች እንግዶች ታድመው ነበር፡፡ የወላይታ የባህል ቡድን ምሽቱን በሙዚቃ ያደመቀው ሲሆን አንዲት  ወጣት ድምፃዊት ባቀነቀነችው ውብ ዜማም በተለይ አቶ ጌታቸው ረዳና አቶ ንጉሱ ጥላሁን ወዝወዝ ብለዋል፡፡  
በነጋታው ለጊፋታ በዓል ሁሉም የተሰባሰበው በወላይታ ስታዲየም ነበር፡፡ ስቴዲየሙ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ የነበረ ሲሆን ሌላ ጊዜ እንዲህ ጢም ብሎ የሚሞላው “ወላይታ ዲቻ” የእግር ኳስ ጨዋታ ሲኖረው ብቻ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች አጫውተውኛል፡፡
የበዓሉ መርሃ ግብር በዞኑ አስተዳዳሪ የእንኳን ደህና መጣችሁና የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር የተከፈተ ሲሆን አስተዳዳሪው ጨረቃ በሚመስለው ታዳሚና በአጠቃላይ ትዕይንቱ መደሰታቸውን የፊታቸው ገጽታ ይመሰክር ነበር፡፡ አክብረው የጋበዟቸው ሁሉ ታድመዋል፤ በዓሉን በጋራ ለማክበርና ኢትዮጵያዊ አንድነት ለመፍጠር - በጊፋታ፡፡  
በበዓሉ ላይ ሌላው ንግግር ያደረጉት አዲሱ የደቡብ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፤ “የዘንድሮውን የጊፋታ በዓል ለየት የሚያደርገው ስልጣን ወይም ሞት ከሚል ሥር የሰደደ ክፉ አስተሳሰብ ተላቅቀን በአዲስ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ሆነን በማክበራችን ነው፤ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ማለት ለማንም እንደማይበጅ ወላይታ ያፈራቻቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው በመልቀቅ ምስክር ሆነዋል›› ያሉ ሲሆን ጊፋታ ሁሉም በአዲስ አስተሳሰብና በአዲስ መንፈስ ሆኖ በአንድነት የሚያከብረው በዓል እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡  
ይህንን የመሰለ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ መሃል እንዲገኙ የጋበዟቸውን የዞኑን መስተዳድር በማመስገን ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ ጊፋታ በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ በሚደረገው እንቅስቃሴ በግላቸውም ሆነ እንደ ትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ ከወላይታ ህዝብ ጐን እንደሚቆሙ በመግለጽ፣ የአክሱም ሀውልትን ቅርጽ በስጦታነት አበርክተዋል፡፡
አቶ ንጉሱ ጥላሁን ባደረጉት ንግግርም፤ የወላይታ ህዝብ ከጥንት ከጠዋቱ፣ ከስልጣኔ ጋር የተዋወቀ ህዝብ መሆኑን አውስተው፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በጐንደር የፋሲለደስ ቤተ መንግስት ሲታነጽ፣ የወላይታ ህዝብ የእጅ አሻራ እንደነበረበትና በግንባታው እንደተሳተፈ ታሪክን አጣቅሰው ተናግረዋል፡፡ ህዝቡ ወደፊትም ከአማራ ህዝብና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አንድነቱን እንዲያጠናክር ጥሪ ያቀረቡት አቶ ጥላሁን፤ የጐንደር ቤተ መንግስትን ሀውልት ለዞኑ፣ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን ምስል ደግሞ ለከተማ መስተዳድሩ በስጦታ አበርክተዋል፡፡ የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ግርማ አመንቴም በበዓሉ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከሁሉም የህዝቡን ስሜት የነካው ከጌዲኦ ዞን የመጡት የባሌ ሥርዓት (የአባገዳ ሥርዓት አይነት ነው) መሪ ያደረጉት ንግግር ነበር፡፡ በጌዲኦ አንድ የባሌ ሥርዓት መሪ፣ በየትኛውም ሁኔታና ግብዣ፣ ተወካይ ይልካል እንጂ ራሱ ከቦታው አይንቀሳቀስም ያሉት መሪው፤ ሆኖም በጌዲኦ ክፉ ቀን ሲከሰትና ህዝብ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ ሲወድቅ ከሁሉ ቀድሞ ለደረሰልን የወላይታ ህዝብና መንግስት፣ ተወካይ መላክ፣ ለክብሩ ስለማይመጥን፣ ራሳቸው  መገኘታቸውን በመግለጽ፣ ህዝቡን አመስግነው  ስጦታ አበርክተዋል፡፡
በወላይታ የባህል ቡድን እየተዋዛ በተለያዩ የአካባቢው ተወካዮች ንግግር የታጀበው የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል መርሃ ግብር፤ የጊፋታ መገለጫ በሆነው “ለኬ አያያ ለኬ” የተሰኘ ታዋቂ ሙዚቃ ነው የተዘጋው፡፡ ከዚያም በወላይታ የባህል ማዕከል በሆነው ጉተራ አዳራሽ በተዘጋጀ የዞኑ ባህላዊ ምግቦችና ቁርጥ ሥጋ የምሳ ግብዣ፣ እንዲሁም በሌዊ ሪዞርት በተሰናዳ የእራት ግብዣ እንግዶች ከታደሙ በኋላ የበዓሉ መርሃ ግብር ተጠናቅቋል፡፡
በዓሉ ከመስከረም 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የ‹‹2012 ሚስ ጊፋታ የቁንጅና ውድድር››፣ የዞኑ ባህላዊ አልባሳት ለእይታ የቀረበበት የፋሽን ትርኢት፣ “ለጊፋታ እሮጣለሁ” የተሰኘውና 20ሺህ ሰው የተሳተፈበት የ3.5 ኪ.ሜ ሩጫ፣ የብሔሩ የባህልና የቋንቋ ሲምፖዚየም፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የደመራ ማብራትና የእርድ ሥነ ሥርዓት እንደየቅደም ተከተላቸው እስከ ዋናው የበዓሉ መዳረሻ ድረስ በድምቀት ተከናውነዋል፡፡ እኛም ለወላይታ ህዝብ ዮዮ ጊፋታ ብለናል፡፡    

Read 1958 times