Tuesday, 08 October 2019 09:39

እግር መንቀል የለም - በአባይ ጉዳይ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

  ግብፆች በአባይ ጉዳይ እንቅልፍ ወስዷቸው አያውቅም፡፡ ከቪክቶሪያ ሐይቅ የሚነሳው ነጭ አባይ፣ ከኢትዮጵያ መሬት የሚነሱት ባሮ፣ አክቦና ጊሎ ወንዞች መዳረሻቸው ግብጽ ቢሆንም ትዝ ብሏቸው አያውቅም፡፡ እነሱን እንቅልፍ የሚነሳው ከከሰላ የሚነሳው የአባይ (ጥቁር አባይ) ወንዝ ነው፡፡ በየጊዜው ሥልጣን የሚይዙ የግብጽ መሪዎች፣ በአባይ ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ እንደዛቱ፤ ነገር እንደዶለቱ ነው የሚኖሩት፡፡
“አባይን ትነኩና ውርድ ከራሴ” የሚል መንፈስ የነበረው የግብፁ ፕሬዚዳንት ሳዳት ፉክራ የማይረሳውን ያህል የፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ የዘመቻ ዛቻም አይዘነጋም፡፡ የሰሞኑ የፕሬዚዳንት አልሲሲ ንግግር፣ ቀደምት የግብጽ መሪዎች ሲያደርጉት ከኖሩት የተለየ አይደለም፡፡
አሥራ አንዱን የአባይ ተፋሰስ አገሮችን ወደ አንድ በማምጣት፣ በውኃ ሃብታቸው አጠቃቀም ላይ እንዲወያዩና እንዲደራደሩ ለማድረግ ኢትዮጵያ ብዙ ደክማለች፡፡ አሥር ዓመት በወሰደው ክርክርና ድርድር፣ ግንባር ቀደም ሆና ሠርታለች፡፡ የትብብር ማዕቀፉን ከአፀደቁ ዘጠኝ አገሮችም አንዷም ናት፡፡ የትብብር ማዕቀፉን በምክር ቤታቸው ሕግ አድርገው ከአፀደቁ አገሮች አንዷ አሁንም ኢትዮጵያ ናት:: ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ የመጀመሪያ መሆኗ የምርጫ ሳይሆን ግድ ነበር፡፡
ግብጽና ሱዳን በትብብር ማዕቀፉ ድርድር ላይ የነበሩ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ወደ ጫፍ እየተጠጋ ሲመጣ አፈግፍገዋል፡፡ በተለይ ግብፅ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ጉዳይ ሊዋጥላት የሚችል አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም ከሱዳን ጋር የተዋዋለቸውንና 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ.ሜ ለሱዳን፣ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ.ሜ ውኃ ለግብፁ የሚሰጠው ስምምነት በተፋሰሱ አባል አገራት ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘት ሆድ እንዲበላትና  ሙሉ ለሙሉ ከአባይ ተፋሰስ ስምምነት ራሷን እንድታገል አድርጓታል፡፡
ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ባይታወቅም፣ ኢትዮጵያ “ፕሮጀክት ኤክስ” እያለች ስታካሂድ የቆየችውን ጥናት ጨርሳ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የሕዳሴ ግድቡን መሠረት በማስቀመጥ እቅዷን ይፋ አደረገች፡፡
በቤንሻንጉል ክልል ጐባ ክልል ጉባ ላይ የሕዳሴ ግድብን የመሠረት ድንጋይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስቀመጡ፡፡
አቶ መለስ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፤ “ታድለን ቢሆን ኖሮ ይህን ግድብ እኛ ሱዳንና ግብጽ በጋራ በሠራነው ነበር” የሚል መንፈስ ያለው መልዕክት ማንፀባረቃቸውን አስታውሳለሁ፡፡ በቦታው ነበርኩና፡፡ ይህንን ይፋ ያልወጣ ግብዣ በቅንነት ያየው ግን አልነበረም፡፡
የሕዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ እንደሚያስከትል፣ ለግብጽ ወዳጅነት ሲሉ የክፋት እጃቸውን በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዝሩ የአረብ አገሮች ከድርጊታቸው እንደሚቆጠቡ ያወቀችው ግብጽ፣ አራስ ነብር ሆና ስትነሳ ጊዜ አልወሰደባትም፡፡
በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ እየተሯሯጠች፣ በሌላው በሶስቱ አገሮች መካከል ማለትም በግብጽ በሱዳን ኢትዮጵያ መካከል ድርድር እንዲደረግ ለማድረግ ከፍተኛ ግፊት አደረገች፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ የልዑካን ቡድን በመላክ የማግባባቱን ሥራ አጠንክራ ቀጠለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የሶስቱን አገራት ተቀራርቦ መሥራት ጉዳት እንደሌለው አምኖ ለመነጋገር ፈቃደኛነቱን ገለፀ፡፡
ይህ ትክክለኛ እርምጃ እንዳልሆነ እኔ በወቅቱ በምመራው በ “ነጋድራስ” ጋዜጣ ላይ ተችተን መጻፋችንን አስታውሳለሁ፡፡ ዋና ምክንያታችን ደግሞ ኢትዮጵያ ብዙ የደከመችበትን የትብብር ማዕቀፏን ትታ በመውጣት ብቻዋን መቆም የለባትም፤ ማዕቀፉ ይበልጥ የሚያስፈልገው ለኢትዮጵያ እንጂ ሌሎች አገሮች ባለመሆኑ፣ መከላከያ ጋሻዋን አይኗ እያየ እንዴት አሳልፋ ትሰጣለች በማለት ነው፡፡ የፈራነው ደርሶ አሁን ኢትዮጵያ ብቻዋን ቆማለች፡፡ ዋና አንቀሳቃሽ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ከነገሩ በመራቋና የአባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍም ከብዙዎቻችን ህሊና ጠፍቷል፡፡ ከአለም ስዕሉ ደብዝዟል፡፡
ስለዚህም ነው 1.3 ቢሊዮን ዶላር ይወጣባቸዋል ተብለው ታቅደው የነበሩ በሶስት አገሮች የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ሣር እየበቀለባቸው የሚገኙት፡፡
ግብፆች ይህን ነገር የቆሰቁሰበትን  ጊዜ ለምን ፈለጉት? ስለ ምንስ አጀንዳውን እንደ አዲስ ሰማይ ላይ መስቀል አስፈላጋቸው? መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
በ1950 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የመጀመሪያው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር እንቅስቃሴ በጀመረ ጊዜ ካይሮና ካርቱም ላይ ቢሮውን እንዲከፍት የገንዘብ፣ የማቴሪያልና የዲፕሎማቲክ ድጋፍ ያደረጉለት ግብፆች ናቸው፡፡ አልጀሪያ ቀጥላ በአሰልጣኝነት ድርሻዋን መውሰዷና ሌሎች የአረብ አገሮች መረባረባቸውም አይረሳም፡፡ ከ30 ዓመት በላይ የወሰደው ያ የእርስ በእርስ ጦርነት፤ ኢትዮጵያን በገንዘብና በሰው ኃይል አድቋታል፡፡ በመጨረሻ ባህር አልባ አገር እንዳይረጋት የሚረሳ አይደለም፡፡ የዘንድሮውም በሌለ ችግር ኡኡታ ማባዛት፣ ለኢትዮጵያ ሊሰጡት የፈለጉት አንድ ክፉ አጀንዳ እንዳላቸው የሚያመላክት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ የሚጋዝባት አገር ሆናለች፡፡ በየቦታው ድንገት በሚስቀስቀሱ ግጭቶች ሰላም እያደፈረሰ ነው:: እዚህ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ከባድ ሥራ አይደለም፡፡ ሕዝብና መንግሥትን ማስጠንቀቅ የሚገባው በዚህ ጊዜ ነው፡፡  መንግሥት ያካባቢ ችግሮችን ፈጥኖ መፍታት፣ አንዳንዶች ሳያውቁ የሚከተሉት መንገድ ለጠላት የሚሰጠውን ያልታሰበ ጥቅም ማስረዳትና ከዚህ ተግባር መነጠል በአፋጣኝ ሊወስድ የሚገባ ተግባር ነው፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ መንግስት መወሰድ የሚገባው እርምጃ፣ በዚህ ቀደሙ አቋሙ ላይ ፀንቶ መሟገት ነው - ልክ እንደ ነፃ ትግል ታጋይ፡፡ እግር መንቀል ተወርውሮ መውደቅ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እግር መንቀል የለም!Read 841 times