Saturday, 05 October 2019 00:00

ይድረስ … ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከአመታት በፊት ከአንድ የክፍል ጓደኛዬ ጋር ከት/ቤት ስንመለስ ውሃ ጠምቶኝ ስለነበር፣ ችኋንቻ ከሚባል ወንዝ  ውሀ እየጠጣሁ ነበር፡፡ ጓደኛዬ “ከዚህ ወንዝ ውሃ አልጠጣም” አለኝ፡፡
“ለምን? አልኩት፡፡
“እህቴን በልቷታል፤ ደመኛዬ ነው” አለኝ።
“በእርግጥ ይሄ ወንዝ እህቴን ቢበላት ኖሮ፣ እኔም ላልጠጣ ነበር ማለት ነው” አልኩ ለራሴ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ከአጎቴ ጋር ከገበያ ስንመለስ፣ አመሻ ለሚባል ትልቅ ወንዝ ውሀ ልጠጣ ስል፡-
“ብርሃኑ፣ ከዚህ ወንዝ ውሃ አትጣጣ!” አለኝ
“ለምን?” አልኩት።
“ዘመዳችንን በልቶታል፤ ደመኛችን ነው”
ይህ ታሪክ ልቦለድ ወይም ፈጠራ አይደለም:: አማራ ክልል ጓንጓ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ጀሞራ ቀበሌ የሁል ጊዜ ክስተት ነው፡፡ ከግንቦት እስከ ጥቅምት፣ ይህ የገጠር ቀበሌ፣ ለሁለቱም ትላልቅ ወንዞች ብዙ የሰው ህይወት ይገብራል፡፡ ዘንድሮ ካለሁበት ደውዬ፣ ቤተስቦቼ ጋር ሰላምታ ተለዋወጥኩ፡፡ ደህንነታቸው ከጠየቅሁ በኋላ፤
“ሰፈሩ እንዴት ነው?” አልኩት ወንድሜን፡፡
“ዘንድሮ ጥሩ ነው፡፡ አመሻና ችኋንቻ የተባሉት ወንዞችም በዚሁ ክረምት የበሉት ሰው አስር አይሞላም፡፡ ስድስት ሰው ብቻ ነው” አለኝ፡፡
 የስድስት ሰው ህይወት ጠፍቶ ብዙ አይደለም!? እርር አልኩ፡፡ ወንድሜ አሁንም እያናገረኝ ነው፡፡
“አንድ መርዶ ልነግርህ ነው፤ ተዘጋጅ” አለኝ፡፡
ከስድስት ሰው ህይወት የሚበልጥ ምን መርዶ ይኖር ይሆን? አልኩ ለራሴ፡፡ ድምጹን ዝቅ አድርጎ እንዲህ አለኝ፡-
“አስፋልቱን ሊወስዱብን ነው!”
****
በ1964 ዓ.ም እንደተመሰረተች ይነገራል ጆመራ ከተማ፡፡ የጎጃምን ለም መሬት ይዛ የተመሰረተች ውብ ከተማ ነች፡፡ እናም በዚህች ከተማ አንድ የሚነገር አፈታሪከ አለ ፡፡ አንድ የበቁ ባህታዊ ናቸው:: አንድ ቀን ከከተማው አጠገብ ከሚገኝ ጉብታ ላይ ቆመው፣ ከተማዋን ቁልቁል እየተመለከቱ እንዲህ ሲሉ ተነበዩ፡- ፋፊ መንገዶች ይርመሰመሳ፣ የሰማይ ሩምብላዎችም በሰማይ እንደልብ ይከንፋሉ፡፡
ሰፋፊ አስፋልቶች … ድልድዮች በአመሻና በችኋንቻ ወንዞች ላይ ይሰራሉ፤ አመሻና ችኋንቻ ወንዞች የሚበሉትን ሰው ያጣሉ…”
አንድ ባህታዊ ተነበዩ ተብሎ የሚወራው ይህ በከተማው በሰፊው የሚነገር አፈታሪክ ነው፡፡ በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር ብዙ ሰዎችን ለቃቅመው የሚወስዱ ሁለት ታላላቅ ወንዞች ባሉባት  በዚህች ከተማ... ድልድዩ በአመሻና በችኋንቻ ወንዞች ላይ ይሰራሉ፤ አመሻና ችኋንቻ ወንዞች የሚበሉትን ሰው ያጣሉ… የሚለው ትንቢት ከምንም በላይ ተፈጽሞ ማየት የሚፈልጉት ጉዳይ ነበር፡፡
ዘመናት አለፉ፡፡ ወንዞችም ከለም አፈር ጋር ከት/ቤት የሚመለሱ ተማሪዎችን፣ ከገበያ የሚመለሱ ነጋዴዎችን፣ አቅመ ደካሞችን ወ.ዘ.ተ መብላታቸውን (መውሰዳቸውን) አላቋረጡም፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ግን ለነዋሪው ሀሴት የሚሞላ አዲስ ዜና በከተማዋ ተሰማ፡፡ ትንቢቱ የሚፈጸምበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ጅማሬ ይፋ ሆነ፡፡ ከተማዋን ከሌሎች አጎራባች ከተሞች ጋር የሚያገናኝ ሰፊ የአስፋልት መንገድ፣ በወንዞችም ድልድይ እንደሚገነባ ተነገረ፡፡ የመሰረት ድንጋይም ተጣለ ተባለ፡፡ ህዝብ ፈነደቀ፡፡ ፈጣሪውን ማመስገን ጀመረ፡፡
“ሰፋፊ አስፋልቶች ... ድልድዮች በአመሻና በችኋንቻ ወንዞች ላይ ይሰራሉ፤ አመሻና ችኋንቻ ወንዞች የሚበሉትን ሰው ያጣሉ ሉ ሉ ሉ…”
የመሰረት ድንጋይ በ2006 ዓ.ም ተጣለ፡፡ ቁጭ --- አዮ -- ዚገም -- መንገድ ኘሮጀክት ተብሎ ስራውን እንደሚጀመር ተበሰረ፡፡ በተለይ ቀበሌው ከወረዳው ካሉት ቀበሌዎች ሰላምና ጸጥታ በማስፈን፣ በትርፍ አምራችነቷ (ከአካባቢው አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ሰፊ ምርት ያላት መሆኗ)፣ ኢንቨስተሮችን መሳብ መቻሏ ቀበሌዋን “የእህል ጎተራ” የሚል ቅጽል ስም እስከ መስጠት አድርሷታል፡፡
ጊዜው ነጎደ፡፡ ኘሮጀክቱ መጓተት ጀመረ:: ቢሆንም የአካባቢው ሰው በኘሮጀክቱ ላይ ጽኑ እምነት ስለነበረው ተስፋ የቆረጠ ማንም አልነበረም:: በ2010 ግን ያልታሰበው ሆነ፡፡ የታሰበውና ስራው የተጀመረበት የአስፓልት መንገድ የመስመር ለውጥ አድርጓል ተባለ፡፡ ስንት እቅድ መና ቀረ፡፡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠና ስራው ከተጀመረ ከአራት አመታት በኋላ ሀሳቡን የቀየረው ብቸኛው ኘሮጀክት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ያኔ ድሮ አብረን የተማርናቸው እምቦቃቅላ ልጆች፣ ዛሬ አድገው ለፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን አቤቱታ ለማቅረብ ከአራት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ አቆራርጠው አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ አገኘኋቸው፡፡ የአስፓልት መንገዱ በመቀየሩ ማዘኔን ገለጽኩላቸው፡፡
እነርሱ ግን የሚበገሩ አይደሉም፡፡ እናም “በትክክል ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የመንገዱን ፕሮጀክት ቀድሞ በታሰበው መስመር እንመልሰዋለን::
ለዚህም ነው እዚህ የመጣነው” አሉኝ፡፡
“እንዴት?” አልኳቸው፡፡
ከሶስቱ አንደኛው መናገር ጀመረ ሰሙ ሙሉነህ ይሁን ይባላል፡፡
“ በነገራችን ላይ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ ሆኛለሁ፡፡ እዚህ አብሮ ያለው አንደኛው አለሙ ወንድም ይባላል፡፡ መቼም ስሙን አልረሳኸውም፡፡ የቀበሌ አስተዳደር ነው፡፡ አንደኛው ደግሞ የኔ አለም ሽቲ ነው፡፡ ከተማው ላይ ሁነኛ ፋርማሲ ከፍቶ ያስተማረውን ማህበርሰብ እያገለገለ ይገኛል፡፡ እና ያለ አግባባ የተቀየረብንን የመንገድ ኘሮጀክት ቀድሞ ታስቦ ወደ ነበረው መስመር ለመመለስ ነው እዚህ ድረስ የመጣነው” አለኝ፡፡
“ምን ማሳመኛ አላችሁ?” አልኳቸው፡፡
“ያሉት አማራጮች ሶስት ቦሆኑም ከመንገዱ መልክዓ ምድር፣ ከሚያስውጣው ወጪ አንጻርና ለመንገዱ ማህበር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንጻር ቀድሞ ታስቦ የነበረው ቁጭ… አዮ …አምበላ… ጆመራ …. ጎሃ ዚገም መስመር የተሻለ ሆኖ ሳለ፣ አዲሱ የተቀየረው ኘሮጀክት ግን ምንም በማይጠቅምና የመንገዱንም ግልጋሎት ባለገናዘበ መልኩ 26 ኪሎ ሜትር በረሃ ለበረሃ የሚንከራተት ባይተዋር መንገድ ያደርገዋል፡፡ ከሚያስወጣው ወጪና ከመንገዱ መልክአ ምድር አንጻር የተሻለው ይህ የተነፈገው (መስመሩ የተቀየረው) መንገድ ነው፡፡ አንደኛ የመጀመሪያው መንገድ ኘሮጀክት ስምንት ቀበሌዎችንና አራት ንዑስ ከተማዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
አካባቢውን ትርፍ አምራች ለኢንቨስትመንት ምቹ ሆኖ ባለሀብቶች ከሌላ ቦታ እየመጡ፣ በግብርና ኢንቨስት አድርገው  ያመረቱትን ምርት በቂ መሰረት ልማት ያልእየጎዳው ነው፡፡ አዲሱ የተቀየረው ኘሮጀክት ግን መንገዱ ምንም ሰው ባልሰፈረበት ባዶ በረሃ ነው 26 ኪሎ ሜትር የሚያልፈው፡፡ እነዚህ ስምንት ቀበሌዎችና አራት ንኡስ ከተማዎች ተጎጂ ናቸው፡፡ ነፍሰጡር እናቶችን ወደ ጤና ጣቢያ በፍጥነት የሚወስድ መንገድ ባለመኖሩ ለምት እየተዳረጉ ነው፡፡” አለኝ፡፡
ይህንን የመጨረሻውን ዓረፍተ -ነገር እንኳን ለማዳመጥ አንጀት አጣሁ!
“ነፍሱ ጡር እናቶችን ወደ ጤና ጣቢያ በፍጥነት የሚወስድ መንገድ ባለመኖሩ ለሞት እየተዳረጉ ነው” የሚለውን፡፡
እናም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሆይ! ይህን የዘላለም እንባችንን እንድታብስልን በትህትና እንጠይቃለን፡፡
(ብርሃኑ በቀለ መንገሻ፤ የ“ድስካር”መጽሐፍ ደራሲ)

Read 1606 times