Tuesday, 01 October 2019 11:18

“መኮራረጅ የኪነ ጥበብ ምሽቶችን ሊያከስም ይችላል”

Written by  (ምስክር ጌታነው፤ የኪነጥበብ ምሽት አዘጋጅ)
Rate this item
(1 Vote)

በምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን የሚዘጋጀው የኪነ ጥበብ ምሽት የጀመረው በ2009 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ነው፡፡ እስካሁን ወደ 26 ያህል ምሽቶችን አዘጋጅተናል፡፡ የኪነ ጥበብ ዋና ፋይዳው የሀሳብ መድረክ መሆን መቻሉ ነው፡፡ ሰዎች የተለያዩ ሃሳቦችን በተለይ በኪነ ጥበብ በኩል ማስተላለፍ ጠቃሚ ነው ብለው በዚህ መድረክ፣ ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ ሀሳቦች የሚንሸራሸርበት መሆኑ ዋና ፋይዳው ነው፡፡ ሰለጠኑ የምንላቸው አገራትንም የኋላ ታሪክ ብንመለከት፣ የስልጣኔያቸው ዋና መሰረት የነጠሩ ሀሳቦች ናቸው፡፡ በሀሳብ ላይ ለመነጋገር መድረክ ሆነው ማገልገላቸው ትልቁ ፋይዳቸው ነው፡፡ ሀሳብ በደረቁ በፖለቲከኞች ከሚቀርብ ኪናዊ ሆኖ በሚያዝናና መንገድ ቢቀርብ፣ የበለጠ ሀሳቡ የመስረፅ  ሀይል ይኖረዋል:: ለዚህ ደግሞ የኪነ ጥበብ ሰዎችና መድረክ ዋና መሳሪያዎች ናቸው:: አንድን ሀሳብ ካድሬ ከሚያቀርበው የኪነ ጥበብ ሰው ቢያቀርበው፣ አንድም ሀሳቡን የማስረጽ አቅም፣ ሁለትም ቅቡልነት አለው፡፡ ሦስተኛው የሀሳብ ልዩነቶች ይስተናገዱባቸዋል - የኪነ ጥበብ ምሽቶቹ፡፡ አማራጭ የሀሳብ ብፌዎች ይስተናገዱባቸዋል፤ ሀሳቦች ይፈልቁባቸዋል፡፡
እኔ ስጀምር ‹‹ጦቢያ ግጥም በጃዝ›› ብቻ ነው የነበረው፡፡ እንደ ብርቅ ነበር የሚታየው፡፡ ግጥም በጃዝን ለየት የሚያደርገው ግጥም በጃዝ ላይ ማተኮሩ ነው፤ አንድ ወይም ሁለት ዲስኩር ነው የሚቀርበው:: በመድረኩ የሚነግሰው ግጥም ነው፡፡ እኔ ስነሳ መሰረት ያደረግሁት ደግሞ ዲስኩርን ነው፡፡ በእኔ መድረክ  አምስት ዲስኩር ቀርቦ፣ ግጥም ሁለት፣ ቢበዛ ሶስት ነው የሚቀርበው፡፡ የእኔ መነሻና አላማዬ ደግሞ ዲስኩር እንዲሰፋና እንዲነገር ነው:: ሰው ዲስኩሩን በጣም ወደደው፡፡ ‹‹ጦቢያ ግጥምን በጃዝ››ን ጨምሮ ሌሎቹ ምሽቶች ላይ ለዕለቱ ፕሮግራም ርዕስ ሁሉ አይሰጥም ነበር፡፡ ይህንን እኔ ነኝ የጀመርኩት:: ለምሳሌ “ስንደመር” “ከኢትዮጵያዊነት ውጭ አማራጭ የለንም” እና ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም አንድ ምሽታችን ላይ ድንገቴ እንግዳ ሆነው መጥተው፣ ሰው ሁሉ ማመን አቅቶት ነበር፡፡ እናም ለፕሮግራሙ ርዕስ አዘጋጅቼ፣ በዚያ ርዕስ ላይ ሰዎች እንዲዘጋጁ ጊዜ ሰጥቼ ነው ስንሰራ የቆየነው፡፡ ይሄ አንድ መንገድ ነው፡፡ ሌላ ሰው ደግሞ ከፈለገ በቴአትር፣ በድራማና በሌላም መንገድ ማቅረብ ይችላል፡፡
የኪነ ጥበብ ምሽቶች መብዛታቸው አይደለም ችግሩ፣ ተመሳሳይ ይዘት በተመሳሳይ ሰዎች መቅረባቸው ነው:: አሁን ከፖስተር ግራፊክስ ዲዛይን ጀምሮ ተመሳሳይ ነው:: ሁሉም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አሰልቺ ነው፡፡ ሰዎቹም ተመሳሳይ ናቸው:: ብንችል የተለያየ ሰው ብንጋብዝ ጥሩ ነው፡፡
ይህን ለማድረግ የሚጥሩ አዘጋጆች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡  አሁን እንደ ታዳሚ የያዝናቸው ሰዎች አሉ፡፡ ፕሮግራማችንን ወደው አውቀው ይመጣሉ፡፡ አዳራሽ ይሞላል፡፡
እንደ ዕድል ሆኖ ፕሮግራማችን የተመልካች ችግር የለበትም፤ ሁሌ ሙሉ ነው አዳራሹ፡፡ ነገር ግን ሂደቶቹ ያሰጋሉ:: የሃሳብ ድግግሞሽና ተመሳሳይነት ታዳሚውን አሰልችቶት ቤቱ ቁጭ እንዳይል እሰጋለሁ:: መኮራረጅ የኪነ ጥበብ ምሽቶችን ሊያከስም ይችላል፡፡


Read 931 times