Print this page
Thursday, 03 October 2019 00:00

የመደመር ጽንሰ ሃሳብና አካታች ካፒታሊዝም

Written by  ሀብታሙ ግርማ (የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር)
Rate this item
(1 Vote)

አንድ አመት ተኩል ያስቆጠረው የአገራችን ሁለንተናዊ ማሻሻያ ጅምር፣ ከሚተችባቸው ነጥቦች አንዱ ለውጡን ለመምራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ (roadmap) የለውም የሚል ነው:: የለውጡ አመራሮች፣ የለውጡ መዘውር የመደመር መርህ መሆኑን ቢናገሩም፣ ይህ የመደመር እሳቤ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ገጽታዎች በተብራራ መልኩ ሳይቀመጥ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ መደመር ፍልስፍና መጽሐፍ እያዘጋጁ እንደሆነ ከመነገሩ ውጪ ቢያንስ ህዝብ የሚያውቀው ሰነድ እስካሁን የለም፡፡ ነገር ግን የዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያለፉትን 18 ወራት የአመራር ፍልስፍናና መንግስታዊ ተግባራትን ከገመገምን፣ የአመራር መርሃቸው የሆነው የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ርዕዮተ ዓለማዊ መሰረት እንዳለው፣ ይህም  አካታች ካፒታሊዝም እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
ለመሆኑ የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ምንድነው? ከተለምዷዊው ካፒታሊዝም (conventional capitalism) የሚለየው በምንድነው? ይህ መጣጥፍ ለእነዚህ እና ተዛማጅ ጉዳዮች መልስ ያፈላልጋል፡፡
የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ምንነትና ግቦች
አካታች ካፒታሊዝም የህዝብን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ስነ ምግባራዊ ጉድለቶች  ለማስተካከል መንግስት ፣ የግሉ ዘርፍና ማህበረሰቡ በጥምረት የሚሰሩበትን ምጣኔ ሀብታዊ (economic)፣ ፖለቲካዊ (political)፣ ማህበረሰባዊ (sociological)፣ ስነ ባህላዊ (anthropological)፣ ስነ ምግባራዊና ሞራላዊ (ethics and moral) አስተምህሮቶችን ባንድ ላይ ያቀፈ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡
የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በ1947 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በአገረ አሜሪካ  urban Land Institute በሚል ርዕስ በታተመ አንድ ሰነድ ላይ ነው፡፡ በቅርብ አመታት አለን ሃሞንድ እና ፕራህላድ የተባሉ የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብት በምርምር ስራዎቻቸው  የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብን በስፋት አስተዋውቀዋል:: የአካታች ካፒታሊዝም መነሾዎች ሁለት ናቸው:: የመጀመሪያው ድህነትና የማህበራዊ ፍትህ እጦት የጅምር ካፒታሊስት አገራት መሰረታዊ ችግሮች ናቸው የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው በኢኮኖሚ ስርዓቱ የግል ዘርፉ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን (ማለትም በድህነት አዘቅት ውስጥ የሚማቅቁ ዜጎችን፣ ሴቶችን) ማገዝ እንዳለበት ያስገነዝባል::
በመሰረቱ አካታች ካፒታሊዝም አላማው ተለምዷዊው የካፒታሊስት ስርዓት (conventional capitalist system) የሚያመጣውን የኢኮኖሚ ፍትህ እጦትና የሚስከትለውን ማህበራዊ ቀውስ ማርገብ ነው:: የማህበራዊ ተጠቃሚነትና  ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ዋነኛ የኢኮኖሚው ዘርፍ ግቦች ናቸው:: በመሆኑም የግልም ሆነ የመንግስት ተሳትፎ ይህን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በአካታች ካፒታሊዝም አስተምህሮ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻውን ዜጎች በህይወታቸው ትርጉም እንዲያገኙ አያደርግም፤ ማህበረሰባዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ጉዳዮችም ከኢኮኖሚ ህይወታቸው የተነጠለ ሳይሆን እንዲያውም የተጎዳኘ መሆኑን  ያስተምራል:: የአካታች ካፒታሊዝም ግብ፤ የኢኮኖሚ እድገትን ዘላቂ ማድረግና የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ሲሆን ለዜጎች መንፈሳዊና ቁሳዊ ልማት በትኩረት  ይሰራል፡፡
አካታች ካፒታሊዝም ከተለምዷዊው  ካፒታሊዝም የሚለየው በምንድነው?
የካፒታል ክምችትና ሃብት ማፍራት የተለምዷዊ ካፒታሊዝም ዋነኛ ግቦች ናቸው:: በመሆኑም ማህበራዊ ፍትህ በዚህ ሂደት ሊቀረፍ የሚችል፣ ዋነኛ የኢኮኖሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚው ዘርፍ በነጻ ገበያ መርህ ይመራል፤ የኢኮኖሚው ባለድርሻዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በግለኝነትና ፉክክር ጽንሰ ሃሳብ ይመራሉ፡፡ ከተለምዷዊው ካፒታሊዝም የሚለየው ሰብዓዊ ተጠቃሚነትን ዋናው ምሰሶው ማድረጉ ነው፡፡ በተለምዷዊው ካፒታሊዝም ዋነኛ የኢኮኖሚ መዘውር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሲሆን በአካታች ካፒታሊዝም የግልና የመንግስት ክፍለ ኢኮኖሚ በጥምረትና  በቅንጅት የሚሰሩበት ነው፡፡
ተለምዷዊው ካፒታሊዝም መሰረቱ በፉክክርና በነጻ ገበያ በተመራ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የተሻለ የኢኮኖሚ ብልጽግና መጣል የሚል ነው፡፡ የገበያ መጓደል (market failure) ሲያጋጥም ራሱ ገበያ ይፈታዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ የአካታች ካፒታሊዝም መነሻ  የገበያ መጓደል (market failure) እና የመንግስት መጓደሎች (Government failure) የፈጠሩትን የማህበረሰባዊ ሚዛን መዛባትን (social imbalance) ማስተካከል ነው፡፡ በዚህም በገበያ የማይፈቱ የገበያ ጉድለቶችን መንግስት ይፈታል፤ በመንግስት መጓደል  ችግሮች ሲከሰቱ ገበያው (የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ) ይፈታዋል:: የማህበረሰቡን ስነ ምግባራዊና ሞራል መዛባት ለማስተካከል ደግሞ መንፈሳዊና ባህላዊ ተቋማት፣ ከመንግስትና ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር በጥምረት ይሰራሉ፡፡  
በአካታች ካፒታሊዝም የግለኝነት አስተሳሰብና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሚና
በመሰረቱ የካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ መነሻ (micro foundation) የሰው ልጅ የስነ ልቦና ውቅር ነው፡፡ የሰው ልጅ በህይወት እንቅስቃሴው ሁሉ (ለኢኮኖሚያዊ ስኬቱም ሆነ ውድቀቱ) የውሳኔው ውጤት ነው፡፡ በውሳኔው ሂደት ደግሞ  የፉክክርና የትብብር ስሜቶች የተለያየ ውጤት (የተጽዕኖ ደረጃ) ቢኖራቸውም፣ የፉክክር ስሜት ግን በተጽዕኖውም ሆነ የውሳኔውን ውጤት በመወሰኑ ረገድ የጎላ ነው:: ስለሆነም የሰው ልጅ በኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎቹ ሁሉ የግል ዓላማውን ለማሳካት በፉክክር መንፈስ ይመራል፡፡ የዚህን አስተምህሮ መሰረት በተብራራ ሁኔታ ያስቀመጠው እንግሊዛዊው የምጣኔ ሃብት ሳይንቲስት አዳም ስሚዝ ነው፡፡
አዳም ስሚዝ በ 1776 ዓ.ም (እ.ኤ.አ)  ‘An Inquiry into the Nature and Cause of Wealth of Nations’ በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ እንዳሰፈረው፤ የፉክክር መንፈስ የሰው ልጅ የብልጽግናው መሰረት ነው፤ የሰው ልጅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በፉክክር መንፈስ የሚመራ ከሆነ ለኢኮኖሚ ብልጽግና ቁልፍ የሆኑት የስራ ክፍፍል (division of labor)፣ የቁጠባ ባህል (saving culture)፣. ለፈጠራና ራስን ለመለወጥ መጣር (innovative mindsets and zeal for self-development) የመሳሰሉትን እሴቶች ያዳብራል፡፡ የፉክክር መንፈሱ አይሎ መቀማማትን እንዳያስከትል፣ ማለትም ከልክ ያለፈ ግለኝነት (greed)  እንዳይኖር የገበያ ሃይል የራሱ የማረሚያ ስርዓት (corrective mechanism) አለው፡፡ አዳም ስሚዝ ይህን የማይታየው የገበያ ሃይል (invisible hand of the market) ይለዋል፡፡ በኢኮኖሚ ህይወታቸው ከልክ ያለፈ የግለኝነት (greedy behavior) ባህሪ ያላቸው ግለሰቦች (የቢዝነስ ሰዎች) ሃላፊነት በማይሰማቸው መልኩ መንቀሳቀሳቸው አደጋው ለራሳቸው ነው፤ የገበያ ሃይል ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን በሚነካ መልኩ ቅጣት ስለሚጥልባቸው እንዲታረሙ ይገደዳሉ፡፡
በተለምዷዊው ካፒታሊዝም ስርዓት የመንግስት ሚና ይህ የገበያ ሃይል ስራውን እንዲከውን ምቹ ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ማበጀት፣ በኢኮኖሚ ስርዓቱ ውስጥ የገበያ መርህ መተግበሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት የገበያ ልማትን ማፋጠን፣ የገበያ ስርዓት መርህን የሚጥሱ ይፋዊም ሆነ ድብቅ የኢኮኖሚ አደረጃጀቶችም ሆነ አካሄዶችን መከታተል፣ መቆጣጠርና እርምጃ መውሰድ ነው፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በተለምዷዊው ካፒታሊዝም፣ የሰው ልጅ የፉክክር መንፈሱ ከትብብር መንፈሱ አይሎ ይገኛል የሚል እሳቤ ስላለው የኢኮኖሚ ሃልዮቱም ሆነ ተዛማጅ ፖሊሲዎቹ  ፉክክርን መሰረት ያደረጉ ናቸው:: ከዚህ በተቃራኒው አካታች ካፒታሊዝም፣ የሰው ልጅ በአጠቃላይ የህይወት መስመሩ በተለይም በኢኮኖሚ ህይወቱ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ለውሳኔው መነሻም ሆነ መድረሻ የሚሆነው የሁለቱም፣ ማለትም የፉክክርና የትብብር ዝንባሌዎች ተጽዕኖዎች አሉበት የሚል ነው፡፡ የኢኮኖሚ አስተሳሰቦቹም ሆነ ፖሊሲዎቹ የዚሁ ስነ ልቦናዊ ውቅር ነጸብራቆች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሰዎች በኢኮኖሚ ህይወታቸውና በውሳኔዎቻቸው ሁለቱንም ሃይሎች ከግምት ያስገባሉ፡፡
ከዚህ የምንወስደው ነገር የግለኝነት አስተሳሰብ ግለሰባዊ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በመስጠትም ውስጥ ይኖራል የሚል አመክንዮ አለው፡፡ ከዚህ አንጻር የሰው ልጅ ለሌሎች ጥቅም ዋጋ መክፈልን (altruism) ምክንያታዊ ማድረግ ያሻል የሚል እምነት በመያዙ በጥንታዊው ግሪክ ስልጣኔ ዘመን የነበረውን የኢኮኖሚ አስተሳሰቦች መነሻዎች ይጋራል፡፡ የዘመኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፈላስፋ የነበረው አርስቶትል፣ የግለኝነትን ዝንባሌ (individualistic motive) ጽንሰ ሃሳብ ሲያብራራ፤ ለሌሎች ጥቅም ማሰብ (altruistic motive) እና የግለኝነት ዝንባሌዎች ተጻራሪ አይደሉም፤ ይልቁንም ለሌሎች ጥቅም ማሰብ ምክንያታዊ ግለኝነት (rational selfishness) ነው ይለዋል፡፡ አርስቶትል ለዚህ አስረጅ የሚያደርገው የሰው ልጅ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች የህይወት መስመሮቹ፣ ከውሳኔዎቹ ጀርባ ቁሳዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ እርካታ መሻትም ጭምር መኖሩን ነው፡፡ ስለሆነም ለሌሎች ጥቅም የግል ፍላጎትን መገደብ በራሱ ግለኝነት ነው፤ ምክንያቱም መንፈሳዊ እርካታን ያስገኛልና፡፡ አካታች ካፒታሊዝም፤ ሰዎች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው በግል ታጥረው ከሚጓዙ ይልቅ በጋራ ቢንቀሳቀሱ የተሻለ ማህበረ ኢኮኖሚ ብልጽግና ላይ ይደርሳሉ የሚል አስተምህሮ አለው፡፡
በአካታች ካፒታሊዝም የመንግስት ሚና
በአካታች ካፒታሊዝም መንግሥት ከላይ የተጠቀሱት ግቦች እንዲሳኩ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ድጋፍ ያደርጋል::  መንግስት፤ በማህበረሰቡ ዘንድ የትብብርና የአብሮ መስራትን እንዲሁም የመረዳዳትን እሴቶች የሚያጠነክሩ ተግባራትንና ተቋማትን የመገንባትና የማጠናከር ሚና አለው፡፡ በቀጥታ በኢንቨስትመንትና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች ላይ ከሚያደርገው ኢንቨስትመንት በተጨማሪ የህብረተሰቡን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ወይም የቁሳዊና መንፈሳዊ ደህንነነቱን የሚያሳድጉ  የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችንና ማበረታቻዎችን ያዘጋጃል፡፡ ዜጎች የአቅማቸውን ያህል የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ እንዲሰማሩ ያስተምራል፤ የቢዝነስ ሰዎች ደግሞ ከትርፋቸው ለማህበራዊ ሃላፊነት የሚወጡትን እንዲያሳድጉ ይመክራል፡፡ የመንግስት የመሰረተ ልማት ግንባታ አስፈላጊነት መነሾም፣ ማህበረሰቡ ትርጉም ያለው የህይወት መሻሻል እንዲያመጣ   ማድረግ ነው፡፡
መንግስት ከዚህ አንጻር ስራ አጥነትን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን የተፈጠረው ስራ የሰራተኞችን የስራ ደህንነትና ዋስትና የሚያስጠብቅ  እንዲሁም ለኑሯቸው በቂ መሆኑን የማረጋገጥ ሃላፊነትም አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር የማህበረ ኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶች ተደራሽነትና  ተጠቃሚነት ከማስፈን ባለፈ፣ የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ የቤት ልማት ብቻ ሳይሆን የመኖሪያ ከባቢውን ለኑሮ ምቹ ማድረግ፤ የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን፣ የትምህርት ከባቢው ለመማር ምቹ እንዲሆን መስራት፤ የጤና  ተቋማት ከመገንባት በተጓዳኝ ህብረተሰቡ ሊጠብቃቸው የሚችሉ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ ዘዴዎችን ማላመድ፣ ማስተማር፣ ማስረጽ ይኖርበታል፡፡  
የማህበራዊ ሰላምን ከመጠበቅ አኳያ የህዝብ ደህንነትን በፖሊሳዊና በደህንነት መዋቅር ከማጠናከር ጎን ለጎን፣ የግጭት መንስዔ የሆኑ ልዩነቶች በውይይት የሚፈቱበትን ሃገር በቀል ተቋማትን ማጠናከር፣ የተለያዩ ህብረተሰባዊ አደረጃጀቶች ካሉ ማጠናከር፣ ከሌሉ ደግሞ እንዲፈጠሩ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የህዝብን ስነ ምግባርና ሞራል የሚያንጹና እንደ ሃይማኖት ተቋማት፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰባዊ አደረጃጀቶችን እንዲጠናከሩ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ መንግስት እንደነዚህ አይነት ህዝባዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራትና የሥነምግባር እሴቶች እንዲጎለብቱ ማህበረሰባዊ ንቅናቄ ያደራጃል፤ ዜጎችን ማህበረሰባዊ ፋይዳ ባላቸው በጎ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ከመቀስቀስ ባለፈ የተለያዩ ማበረታቻዎችንም ያደርጋል፡፡
እንግዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ሃይል  ስልጣኑን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ እያከወናቸው ያሉ መንግስታዊ ተግባራት ፍኖተ ካርታ የላቸውም የሚለው እምብዛም አያስኬድም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚከተሉት የመደመር ፍልስፍና (መርህ) እንደሆነ ስልጣን ከያዙበት ማግስት ጀምሮ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ለዚህ መርህ ርዕዮተ ዓለማዊ መነሻቸውን እስካሁን ይፋ ባያደርጉም፣ ከሚከተሉት የአመራር ፍልስፍናና ከሚያከናውኗቸው መንግስታዊ  ተግባራት ተነስተን፣ የአካታች ካፒታሊዝም አራማጅ ናቸው ማለት እንችላለን፡፡  
ቸር እንሰንብት!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 6150 times