Print this page
Wednesday, 02 October 2019 00:00

መሪና ተመሪ ሆይ!!

Written by  ማርታ
Rate this item
(1 Vote)

እንደ ዜጋ የምኖረው ኑሮ ያሳስበኛል::  ምስቅልቅሉ ያመሳቅለኛል፡፡ ውዥንብሩ ያናውዘኛል፡፡ የምነሳው ከራሴ ነው፡፡ የማወራው ግምቴን ተደግፌ ነው፡፡ ስለ ምን ግምት ተደግፈሽ ታወሪያለሽ የሚል ካለ፣ ሁሉም ነገር እዚህ አገር በግምትና በድፍረት ነው - እላለሁ:: ፖለቲካው… ኢኮኖሚው… ትንታኔው…ሁሉም ነገር በግምት ነው! (ሳይንሳዊ ይሁን ኢ-ሳይንሳዊ እገምታለሁኝ)
እኔ ማነኝ?
ከእኔ በፊት ምድሪቱ ነበረች፡፡ ለምሳሌ አባቴ የተወለደው ቁጥር “20” በሚባል የምድሪቱ ክፍል ነው፤ እናቴ ደግሞ ቁጥር “21” ከሚባለው ጥግ:: እናትና አባቴ ቁጥር “22” ከሚባለው የምድሪቱ ክፍል ተገናኙና እኔን ወለዱ፡፡ ቁጥር 20,21 እና 22 የእኛነታችን መነሻ ቦታዎች እንጂ እኛነታችን አይደሉም፡፡
ያልተስተካከለ አመለካከት የሰው ልጅ ህመም ነው፡፡ እኔ የተገኘሁት ከዚህ ቦታ ስለሆነ፣ ከዚያኛው ቦታ ከተገኘው የበለጠ “ሰውነት” አለኝ ብዬ ካሰብኩኝ ህመም ውስጥ ነኝ፡፡ ምድሪቱ ቀድማ ሰውን ለማገልገል ተፈጠረች:: እንድንገለገልበት የተፈጠረች ምድርን፤ ሰው ከመሆን ካስቀደምን፤ ሰው መሆንን እንዴት እንገልፀዋለን?
አሁን እኛ ሕመም ውስጥ ነን፤ ስለ ሕመማችን ማውራት ይገባናል፡፡
ሕመም
1ኛ/ “ካፈርኩ አይመልሰኝ”  
እንደ እኔ፤ “እኔ ትክክል ነኝ” ወይም “እኔ ተሳስቻለሁኝ” ማለት ዋጋቸው እኩል ነው:: ምክንያቱም ትክክል ነኝ ብዬ ትክክል መሆኔን ማስረዳት ከቻልኩ እንዲሁም ትክክል ያልሆንኩበት ቦታ ካለና መሳሳቴን ከተረዳሁ፤ እናም ተሳስቻለሁ ማለት ከቻልኩ፣ ወደ ትክክል መሆን መጥቻለሁ ማለት ነው፡፡ “ካፈርኩ አይመልሰኝ”ን እንደ አቅጣጫ ይዞ መጓዝ ግን የከፋና አጥፊ አስተሳሰብ ነው፡፡ እኛ በዚህ ህመም ውስጥ እየተሰቃየን ነው፡፡
2ኛ/ የፍፁምነት አመለካከት
ይህ ሕመም “ፍፁም” ነኝ ባዩም፣ “ፍፁም”ነትን ጠባቂውም ጋ ይገኛል፡፡ በውስጣችን ዘረኝነትን እያብላላን፣ እያገዘፍን፣ እያናጥን… በተራራው ላይ ወጥተን ዘረኝነትንና ዘረኞችን እንረግማለን:: ከተራራው ወርደን ግን የዘረኝነት ሸለቆ ውስጥ ገብተን፣ ሸለቆውን ለማልማት ሌት ተቀን እንጥራለን:: የሚሰማን የሚያየን ያለ አይመስለንም፡፡ በዚሁ ትይዩ የምንሰማውን እንጂ የምናየውን የማናምን አለን፡፡ ይህ እንግዲህ ባዶነት ነው፤ ትልቅ የጤና ማጣት ቀውስ!  
3ኛ/ በችግራችን ምክንያቶች ላይ ብቻ እናተኩራለን
ዘረኝነት ችግራችን፣ ምክንያቱ ደግሞ እስካሁን የመጣነው መንገድ ሲሆን ውጤቱ አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያትና ውጤትን ማውራት ብቻ መፍትሔ አይሆንም:: መፍትሔው ምክንያቱን ማድረቅ፣ ውጤቱን ማከም ነው፡፡ ይኸ እውነተኛ መሆንን፣ ቁርጠኝነትን፣ ብልሃትን  ይጠይቃል፡፡ እሾክን በእሾክ ለማከም ማሰብ ግን የባሰ የህመም ምክንያት ነው፡፡ የዚህ ህመም ተጠቂነትም ይታይብናል፡፡
4ኛ/ ግብግብ ውስጥ መሆናችን
የኃይማኖት አባቶች ከእምነታቸው፣ ከአስተምህሮታቸው፤ ሌሎች የሕብረተሰብ መሪዎች ወይም ምልክቶች፣ ከመርሃቸው ይልቅ ዘራቸውና ሥልጣናቸው ከአእምሮአቸው እየገዘፈ፣ በሁለት ዓለም ትግል ውስጥ እራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን ያናውጣሉ፡፡ ይኸ ዋጋ ቢስነት ነው:: ህመሙ የሥጋም የነብስም ነው፡፡ ብዙዎቻችን በዚህ ስቃይ ውስጥ ነን::
5ኛ/ የምሁራን፣ የአዋቂዎች እንቅፋትነት
አውቆ አጥፊና እኔ ብቻ አዋቂ የሚሉት አስተሳሰብ ውጤቱ በእጅጉ እየጐዳን ነው፡፡ ሁለቱ ሲተጋገዙ ደግሞ ህመሙ ካንሰር ያክላል፡፡
6ኛ/ ሚዲያ፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን ወዘተ..
እነዚህ ሙያተኞች አንድ ጊዜ ችግር ፈጣሪዎች መርዝ ነስናሾች፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ችግር ፈቺ፣ መርዝ አርካሽ የሚሆኑበት ተለዋዋጭ ባህሪ እያሳዩ፣ ህዝቡንም ሙያውንም፣ እራሳቸውንም እያረከሱ ጉስቁልናችንን የሚያሳዩ መስታወቶች ናቸው፡፡ እራስን ያለማየት ትልቅ በሽታ በውስጣችን አለ፡፡ ይኸ ትልቅ ችግር ነው፡፡
እንዲህም ሆኖ ግን ተስፋ የምናደርግባቸው ሰዎች መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሙያተኞችና ምሁራን ጨርሶ የሉም ማለት አይደለም፡፡ የምንፋቀርበት የምንግባባበት… አንድ የሚያደርገን ነገር አላጣንም፡፡ አንድነታችን ከልዩነታችን የበለጠ ሰፊና ግዙፍ ነው:: ነገር ግን ምንዛሬውን አሳንሰነው ያልተገባ ኪሣራ ላይ ወደቅን፡፡ በጥቂቶች ተታለን አብዛኞቻችን ዋጋ እንደሌለው እንደ ምናምንቴ ተቆጠርን፡፡ ከዚህ ለመውጣት ለራስ ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል:: ለራሱ ዋጋ የሰጠ የሌሎችንም ዋጋ በትክክል ያውቃል። መፍትሔ የሌለው ችግር የለምና መፍትሔን ልንፈልግ ያሻናል፡፡
የኔ የመፍትሔ ሃሳብ፡-
1ኛ/ ሕገ መንግስታችን ከፖለቲካችን አቅም መብለጥ አለበት፡፡
ሕገ መንግስታችን ለመታደስና ለመዘመን፣ ለአገልጋይነት የተዘጋጀና እራሱን የሰጠ መሆን ይገባዋል፡፡ በፖለቲከኞች፣ በፓርቲዎች የማይነቃነቅ!!
2ኛ/ ፖለቲከኞች/መሪዎች፣ የሕዝብ መሪዎች እንጂ ገዥዎች አለመሆናቸውን መረዳት ይገባቸዋል:: ገዥው ሕዝብ ያመነበትና የተስማማበት አስተሳሰብ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ መሪነት፣ ኃላፊነት መሆኑንና ኃላፊነትም ተጠያቂነት፣ ሽልማትና ቅጣት እንዳለው በአንክሮ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
3ኛ/ የሐይማኖት አባቶች የጎሳ መሪዎች፣ አባገዳዎች፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ምልክቶችና የአገር ሽማግሌዎች፤ ከአምላክ ወይም ከሕብረተሰቡ የተሰጣቸውን አደራ ያለአግባብ መጠቀም፣ የሰጪውንም እምነት ማጉደል በመሆኑ፣ ተጠያቂነቱ ከባድ ሲሆን ከንቱነትም ጭምር ነው፡፡ የተቀበሉትን አገልግሎት በትክክል መፈፀም ዋጋ ያሰጣልና ሊኖሩበትም የሚገባ ምክንያት መሆን አለበት፡፡
4ኛ/ ምሁራን ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን ወዘተ… ሁሉም ዓይነት ሙያተኛ፣ ሙያው የሚጠይቀው ልኬትና መስመር አለውና ይኸን አልፎ ‹‹እኔነት››ን የሙያ መለኪያና ቀንዲል አድርጎ፤ ‹‹እኔ ካላወራሁና ካላበራሁ፣ እውነትም እውቀትም የለም›› የሚል አባዜ፤ መንገዳችንን ዙሪያ ጥምጥም ያደርገዋል:: ዳር ሆኖ መመልከት፣ ለመፈረጅና ለመንቀፍ ንቁ መሆን ብኩንነት ነው፡፡ በጋራ በእውቀትና በእውነት መሰለፍ፣ የመኖር ትርጉም ይሰጣልና ለራስ ከመኖር በላይ ከፍ ላለው፣ ለሌሎች የመኖር ትርጉም ባለቤት መሆንን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡
5ኛ/ ሕዝብ፤ ሕዝብ ከመሆኑ በፊት ሰው ነው፡፡ እናት፣ አባት፣ ሚስት፣ ልጅ፤ ቤተሰብ ያለው፤ በእርሱ ወይም በቤተሰቡ ላይ ሊፈጸም የማይፈቅደውን ነገር በሌሎች ላይ ለማድረግ ማሰብም ሆነ ማድረግ ሰውነትን መካድና ፈጣሪንም አለማወቅ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይኸ ተደጋግሞ የተነገረ ቢሆንም፣ እየተንሸራተትንበት ያለ የቁልቁለት መንገዳችን ነው፡፡ በአጠቃላይ እምነቶቻችንንና እሴቶቻችንን በወሬ ፈተናቸዋል፡፡ ጆሯችን ከአይናችን፣ ከሕሊናችን አእምሯችን ገዝፏል፡፡ ነገ ከዛሬ እንደሚወለድ ዘንግተን፣ የልጆቻችንን፣ የልጅ ልጆቻችንን ቀን እናሳጥራለን፡፡
እኛ ብርቱ ‹‹ሕዝቦች›› ሆነን ሳለን፣ ብርታታችንን፣ ኃይላችንን አሳልፈን ‹‹መሪ›› ለምንላቸው ፈቅደን የሰጠን፣ ማንነታችንን ለመመለስ ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን፤ ስለዚህ የእስከ ዛሬውን ሽንቁር ለመድፈን መፍትሔው በጋራ መነሳትና በፍቅር መጓዝ ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን ዋጋ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን፤ ያለበለዚያ ግን እንደ ሰናኦር ግንበኞች በጅምር እንቀራለን፡፡ ይህ እጣ ፈንታችን ይሆናል:: በቃ ስንል በቃችሁ እንባላለን፡፡ በበረከት እንኖራለን:: ይኸ የኔ ግምት ነው፡፡ ከግምት ከወጣን ደግሞ የተሻለ ለመሆን እንችላለን፡፡
 የሰላም አምላክ ሰላም ይስጠን!!

Read 1927 times