Tuesday, 01 October 2019 10:48

የበዓለ መስቀል ታሪክ

Written by 
Rate this item
(2 votes)


           የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዐበይትና ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ በዓለ መስቀል ነው:: ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በወርኃ መስከረም ብቻ በዓለ መስቀልን አራት ጊዜ ታከብራለች፡፡ የመጀመሪያው ምክንያተ ክብረ በዓል፣ በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ዓፄ ዳዊት ከግብፅ ንጉሥና ሊቃነጳጳሳት የተላከለትን በቅዱስ ሉቃስ እጅ የተሳለችውን ስዕለ ማርያምን፣ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የተሳለውን ኩርዓተ ርእሱን፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትንና የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል የግብፅና ኢትዮጵያ ድንበር ከነበረችው አስዋን ከተባለችው ቦታ ተረክቧል፡፡
ንጉሡ የያዘውን በረከት ወደ ኢትዮጵያ ሳያደርስ ስናር በተባለው ቦታ ዐረፈ፡፡ ከጊዜ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ የተባለው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ  ተቀብሎ በደብረ ብርሃን፣ በየረር፣ በመናገሻና በልዩ ልዩ ተራራማ ቦታዎች ሲዘዋወር ቆይቶ “መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር”  የሚል ራእይ ተገልጦለት፣ ቅዱስ መስቀሉን በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀምጦታል፡፡ መጋቢት ዐሥር ቀን ደብረ ብርሃን ሲገባ ብርሃን ስለወረደና ዐፄ ዳዊት ከግብፃውያን ጳጳሳትና ንጉሥ እጅ መስቀሉን የተረከቡበትን ቀን በማዘከር፣ የአድባራትና የገዳማት ሊቃውንት ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው የብር መቋሚያና ጸናጽል  ይዘው ወደ ነገሥታቱ ሔደው ተቀጸል ጽጌ እያሉ  እያሸበሸቡ ጸሎተ ወንጌል  ያደርሱ ስለነበር መስከረም ዐሥር ቀን የዓፄ መስቀል በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡
መስቀሉ እንዴት ተገኘ?
አይሁድ መድኃኔዓለም እውር አበራ፣ ለምጽ አነጻ፣ አጋንንት አወጣ፣ ሙታንን አስነሳ፣ በሽተኞችን ፈወሰ፣ ብለው በሰይጣናዊ ቅንዓት ሰቅለው ከገደሉት በኋላ ከሙታን ተለይቶ መነሳቱ ሲገርማቸው የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ዕውር ሲያበራ፣ ሙት ሲያስነሳ፣ ልዩ ልዩ ደዌያትን ሲፈውስ አይተው የክርስቶስ መስቀል እንዲቀበርና ደብዛው እንዲጠፋ 300 ዓመታት ያህል በከርሠ ምድር ቀበሩት:: አይሁድ የክርስቶስን መስቀል ለማጥፋት በጉድጓድ ጥለው የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሁሉ ጉድፍ እንዲጥሉበት አደረጉ፡፡ ማንኛውም ቤተሰብ የቤቱን ጥራጊ እያመጣ መቃብሩ ላይ እንዲቆለል ተደርጎ ጥራጊ ሲጣልበት በመኖሩ ቦታው ኮረብታ ሆኖ ነበር:: ምንም እንኳ ለማውጣት ባይችሉ ክርስቲያኖቹ ቦታውን ያውቁት ነበር:: ከጊዜ በኋላ ጀኔራሎች በአስቫስያንና ጥጦስ ወረራ በ70 ዓ.ም ክርስቲያኖቹ ኢየሩሳሌምን ለቀው ስለወጡ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ወዴት እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ዕሌኒ ንግሥት ልጇ ቆስጠንጢኖስ የክርስትና እምነት ፍቅርና ተቆርቋሪነቱ ቢኖረውም ገና አልተጠመቀም ነበርና አምኖ ተጠምቆ ወደ ክርስትና ሃይማኖት የገባልኝ እንደሆነ ወደ ኢየሩሳሌም ሄጄ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት አሳንፃለሁ፣ የተቀበረውን ቅዱስ መስቀሉን ፍለጋ አስፈላጊውን ሁሉ ራሴ አሟላለሁ ስትል ብፅዕት አድርጋ ስለነበር በአራተኛው መ/ክ/ዘ 337 ዓ.ም ከብዙ ሠራዊትና መኳንንት ጋር ሆና ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡
ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ቅዱስ መስቀልን ከተቀበረበት ለማውጣት አስቦ ስለነበር፣ እናቱ ከመንፈሳዊ ሃሳቡ ጋር በመተባበሩዋና ቅዱስ መስቀልን ለማስወጣት የነበሩትን ብፅዓት ለመፈጸም በማሰብ ተደሰቱ፡፡ አስቀድማ ሂዳ መስቀል ያለበትን ስፍራ እንድታጠና ሠራዊት ገንዘብ አሲዞ ላካት፤ ዕሌኒም ኢየሩሳሌም ደርሳ ኮረብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍርም መስቀሉ ያለበትን ማግኘት አልቻለችም፡፡ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ የጎልጎታን ተራራ እንዲጠርጉ አዘዘች፡፡ በምንም ሁኔታ መስቀሉ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከነሐሴ ወር ጀምራ ምሕላ ያዘች፣ ሱባኤ ገባች፡፡ ጊዮርጊስ ወልድ አሚድ ዕሌኒ ንግሥት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስን አገኘችውና መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ ጠየቀችው፡፡ አባ መቃርስም፤ ከሃዲዎቹ በላይ ብዙ አፈር አፍሰውበታል፣ አፈሩም ትልቅ ተራራ አስከ መሆን ደርሷል ብሎ አስረዳት ይላል፡፡ ኪራኮስ የተባለም ሽማግሌ ወደ ንግሥቲቱ ቀርቦ መስቀሉ ያለበት ስፍራ ቀራንዮ መሆኑን አባቴ ነግሮኛል፣ ተራራው ያ ነው፡፡ ብሎ ጎልጎታን አመልክቷል:: በያዘችው ሱባኤ መልአከ እግዚአብሔር ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ መስቀሉን በእጣን ጢስ ታገኚዋለሽ ብሎ ነግሮአት ስለነበር ኅሊናዋ አልተጠራጠረም፡፡
የመላእኩንና የሽማግሌውን ቃል መሠረት አድርጋ በምድረ ይሁዳና ኢየሩሳሌም የነበሩትን ሕዝብ በጎልጎታ የሚደመር እንጨት እየያዛችሁ ኑ ብላ አዘዘቻቸው፡፡ መስከረም 16 ቀን ከየመንደራቸው እንጨት እየያዙ በጎለጎታ ተራራ ላይ ተደመሩ:: የተደመሩትንም እንጨቶች በእሳት አስለኮሰች፡፡ ብዙ ጊዜም የዕጣኑ ጢስ በተአምራት ከላይ ወደ ታች ተመልሶ መስቀሉ በተቀበረበት ሥፍራ ላይ ተተክሎ ታየ፡፡ የኢትዮጵያ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፤ ዕጣን የመስቀልን ሥፍራ አመለከተ፣ ጢስም ለመስቀሉ ሰገደ እያለ የዘመረው ለዚህ ነው፡፡ /ምዕራፍ ዘአርያም/ ንግሥት ዕሌኒ የዕጣን ጢስ ያመለከተውን ስፍራ ወዲያው መስከረም 16 ቀን ማስቆፈር ጀመረች:: በብዙ ድካም በብዙ ጥረት በተፋጠነ ቁፋሮ መስቀሉ መጋቢት 10 ቀን ተገኘ፡፡
ንግሥት ዕሌኒ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና ሁለቱ ወንወበዴዎች ጥጦስና ዳክርስ የተሰቀሉባቸው መስቀሎች በተገኘ ጊዜ፣ ከእነዚህ ሁለቱ መስቀሎች ጌታችን የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀል በምን አውቀዋለሁ ብላ ለኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስን ጠየቀችው፡፡ አባ መቃርስም የጌታ መስቀል እንደ ልማዱ ሙት ላይ ሲያኖሩት ሙት ያስነሳልና በዚህ ለይተሽ ታውቂዋለሽ ብሎ ምልክት ነገራት፡፡ ወዲያው የጌታ መስቀል ሙት ላይ ቢያኖሩት ሙት ማስነሳቱ፣ ደዌ ቢያቀርቡለት ፈወሰ፡፡ ይህ የጌታችን የኢየሱስ መስቀል ነው ብለው አመኑ፡፡ መስቀል እንዲው ችቦ አብርተው አበባ ይዘው እንዲህ አበራ፣ እንዲህም አበበ አብቦም ፍሬ ክብርን አፈራ እያሉ አሸበሸቡ፡፡
የምስራችንም የቆስጠንጢኖስ ዙፋን እስከነበረበት ቆስጠንጢንያ ድረስ አስተላለፈ:: ከኢየሩሳሌም እስከ ቆስጠንጢኖስ ድረስ አስተላለፈ:: ከኢየሩሳሌም እስከ ቆስጠንጢኖስ ድረስ የነበሩ ሕዝቦች፣ ችቦ በማብራት በየደጁ ተሰብስቦ የደመራ እሳት ወጋገን በማሳየት አበባ ይዞ በመዘመር እልል በማለት ደስታውን በሕብረት ገለጡ፡፡
ዕሌኒ ንግሥት የጌታን መስቀል በማግኘቷ ስለተደሰተች፣ ጌታ በተወለደበት ቤቴልሔም፣ ጌታ በተቀበረበት ጎለጎታ ላይ አብያተ ክርስቲያናት ማሳነጽ ጀመረች፡፡ በዕንቍ በወርቅ በብር አስጌጠች አሠራች፡፡ ቆስጠንጢኖስም በገንዘብና በንዋየ ቅድሳት ረዳት፡፡ ቅዳሴ ቤተክርስቲያኑ መስከረም 17 ቀን የእስክንድርያ፣ የአንጾኪያ፣ የቆስጥንጥንያ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጵስ ቆጶሳት መጥተው በዋዜማው መስቀል 16 ቀን ባረኩ፡፡ ቅዳሴ ቤቱንም አከበሩ:: መስቀል ጥንዓ ይዘው ቅዱሳት መካናት ሁሉ ዞሩ ሥርዓተ ዑደት አደረጉ፡፡ የዕጣን ጢስ አመልክቶ ቁፈራ የተጀመረበትና ቅዳሴ  ቤቱ የተከበረበት አንድ ዕለት ሆነ፤ በዚህም ዕለት ሆነ፤ በዚያም ዕለት የዓለም ሕዝብ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም እየተሰበሰቡ በዓሉን በድምቀት ያከብሩት ነበር:: ይህም መስቀል በኢየሩሳሌም ካስቀመጠችው በኋላ ዘረፋና ምርኮ አጋጥሟታል፡፡
ኢየሩሳሌም በየጊዜው ከጦርነት ከምርኮ ያላረፈች ሃገር በመሆኗ ቅዱስ መስቀልም በአሕዛብ እጅ እየተማረከ፣ ካንዱ ወዳንዱ መዘዋወሩ አልቀረም ነበር፡፡ የክርስቲያን ነገሥታትም በዚህ ነገር እየተናደዱ እየተቆጡ ጦራቸውን መስቀል ወደ ሔደበት ቦታ ሁሉ ከማዝመት አልተገዙም፡፡ ከዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው የሮም ንጉሥ ሕርቃል ነው፡፡ ሕርቃል በተንባላት ተማርኮ ወደ ፋርስ /ኢራቅ/ የሔደውን መስቀል በጦርነት አስመልሷል:: የመስቀል ዘመቻና ጦርነት እየተባለ ብዙ ክርስቲያን ደም ፈሶበታል፡፡
ደመራ
ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትንና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል በማያምኑበት አይሁድ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል እንዳይገኝ ተደርጎ ከተቀበረ በኋላ በዕሌኒ ንግሥት ፍለጋ በደመራው የዕጣን ጢስ ስግደት የተደበቀበት ስፍራ ተለይቶ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን ከተቀበረበት ወጥቷል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ተቀምጦ መስከረም 16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፤ ስለሆነም ደመራ ዕንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡
(መስከረም 26, 2016
BY AMDETEWAHDO)

Read 1631 times