Tuesday, 01 October 2019 10:47

የኢትዮጵያ ተስፋ - የተስፋ ቃሏ ነው

Written by  ብሩክ (ክርስቶዶሉ)
Rate this item
(3 votes)

 “ዛፍ እፍሬው ውስጥ እንደሚደበቅ የ-ምንፈልጋቸው ሰለሞኖች ፃድቃንና ሰማዕታት -ኢትዮጵያ ፍላጎታችንና ዓላማችን ውስጥ ይደበቁ እንጂ መውጣታቸው አይቀርም ... ባርማችን በእምነታችን ውስጥ ስለተደበቁ የሌሉ አይምሰልህ!   ስስት የለሽ፣ ፍርድ አያዛቤ፣ የጥበብ ምንጮች የሚሆኑን፣ ሐዘንን ደምሳሽ፣ ብስጭትን አጥፊ፣ ሕይወታቸው የየሱስን መንገድ የተከተለ፣ በማጣት የማይጨነቁ፣ በማግኘት የማይፎክሩ፥ በጠቅላላው ለዓለማዊ ድሎት የማያፈችሉ --- ፅኑ፥ ብሩህ፥ ታጋሽ፥ ርጉ፥ ሰለሞኖቻችን፥ ፃድቃኖቻችንና ሰማዕቶቻችን ይወጣሉ፤ ከየፍሬዎቻችን --- ከኛ የሚፈለገው በዕምነታችን ብቻ ፀንቶ መገኘቱ ነው ---” (ገፅ 291)
“ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሆነላት እንደ ሰለሞን አይነት ጠቢብ መሪ ማግኘትን አርማ ማድረጓ እንዴት አዲስ ነገር ሊሆንብህ ቻለ?”  (290)
(አደፍርስ ፡ ዳኛቸው ወርቁ)
በቅርቡ መርሓ ተውኔትና ባለቅኔ ሱራፌል ደምሴ ሲጫወተው የተመለከትኩት የአንድ ሰው ትያትር መንፈሴን  ገዝቶት ነበር።  ሎሬት ፀጋዬ ከፃፈው የቀድሞው የቴዎድሮስ ትያትር ላይ  የሌለ አንድ እሴት አገኘሁበት።
እንዲህ ሲሉ ፦ “ይኽን አምናለሁ እመኚኝ፤ነገ ትውልድሽ የሚያነሳው ቴዎድሮስ ትልቅ ራዕይ አለኝ”
ቴዎድሮስ የመቅደላው፣ ነገ ራዕዩን ኢትዮጵያ እንደምታነሳ የሚያምን መኾኑን መግለጡ ነው የመነባንቡ አንድ አዲስ ነገር። እዚህ ላይ ያሁኑ መሪያችን በድላቸውና በድላችን ማግስት  በ”አዲስ  ዕይታ” መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር  ያለፉትን መሪዎች፣ ባለ ራዕዮች፣ ሰማዕታት ማስታወሳቸውን ልብ ይሏል፡፡ በዚያው መርሐ-ግብር   ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጎን ቆሞ  ቀደም ባለው የአገርኛ ዘፈኑ ከተጫወተው ስለሺ ደምሴ ንግርት ጋር  ይገጣጠማል። ይሄ አርቲስት  አስቀድሞ “የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና ... መጡ እንደገና ... መጡ እንደገና” እያለ ማብሰሩን  ስናስበው እንገረማለን።
***  
አገራችን  እስካሁን ስለ ነበረችበት አሁንም ተለቃልቃ ስላልወጣችበት ሁናቴዋ በማስብበት ሁሉ፣ ጊዜ ነገሩ እየበዛብኝ  ውል ለመያዝ ስቸገር፣ ስቸር ስፈራ ሳለሁ፤ አንድ ጠቢቡ ሰለሞን የተናገረውን ቃል አገኘሁ።
- ስለ አገሪቱ ዓመፀኝነት አለቆችዋ ብዙ ሆኑ፤  ይላል (መጽሐፈ ምሳሌ) በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ግን ዘመንዋ ይረዝማል።  (28፥ 2)
እንደ አለቃ ሆነው ስለዚህችው ያሁኗ ኢትዮጵያችን ግምት የሰጡ፣ የተነተኑና አስተያየት የሰነዘሩ ልሂቃን፣ ጥፎ ለጣፊዎችና ደብተራዎች ለቁጥር አይመቹም። አውራ የሚባሉት ልሂቃን  የሕዝብ ናቸው ብለው በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው የአገሪቷ ያልተፈቱ ችግሮች ውስን ናቸው (ጥቂት አላልኩም)። ጥቅል ጉዳዩ የመናገር የመፃፍ መብት አለመከበር፣ የመብራት የኔትዎርክ ጉዳይ፣ የትውፊት የባህል የታሪክ መበላሸት፣ የአስተዳደር ችግር፣ ሙስና፣ አጭበርባሪ ፕሮፓጋንዳ፣ የመንግስታዊ ተቋማት በደል፣ በከፍተኛ ሁኔታ አምባገነንነትና የመሳሰሉት ናቸው። በአጠቃላይ በነዚህ ጉዳዮች ዙርያ ሺህ መጣጥፎችና ሓሜታዎች ተፈብርከዋል።
ደግሞ መፅሐፍ በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በኀጥኣን አፍ ግን ትገለበጣለች።  (መጽሐፈ ምሳሌ 11 : 11) እንዲል እነዚህ ጉዳዮች መነሻ ሆነው የግራና የቀኙ እንካ ስላንቲያ ተካሮ ጠቡ ለአንድ አገር ሳይሆን በሀገርና ሀገር መካከል መስሎ ነበር።
ገዢው አክርሮ ባርያውን ለማስገዛት ከያዘው ልጓም ይልቅ ከቀንበሩ አምርረው የተጣሉና በእልህ ውሳኔ የአንገታቸውን ቀለብት ሳያስፈቱም ሳያላሉም እንዲሁ ለማፈትለክ እንችላለን ሲሉ እስካሁን በነበረው ትግል ብዙ ወገኖቻችን ተሰውተዋል፡፡ በሥልጣን የሚባልጉ፣ የሙስና ሙያተኞችና ጨካኝ የፖለቲካ ሴረኞች - በሌላ በኩል ብስለት ብልሃት እርጋታን የናቁ ደፋር ችኩል የፖለቲካ ወጠጤዎች አገራችንን ወደ አስከፊ ፍፃሜ፣ ወደ ደም ምድርነት  የሚወስዷት ፈጣን የጥፋት ኃይላት ፈረሶች ነበሩ - እንዳካሄዳቸው።
ልክ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መመረጣቸው  በተሰማበት ቀን፣ እኔ በሀረር ክልል ከተማ ጎዳናዎች ላይ በእግሬ እጓዝ ነበር፣ ዶፍ ዝናብ ያለ ሰሞኑ ወረደ፥ ቄሮ በሚል አጠራር በከተማው ህብረተሰብ ዘንድ የሚታወቁ የአገሬ ልጆች፣ ወጣትና ህፃናት ባላገሮች ሁሉ የከተማውን መንገድ በከፍተኛ አጀብ ከድል ዜማቸው ጋር ሲፈሱበት --
“ምህረት በቀስታ እንደ ዝናብ ከሰማይ ይንጠባጠባል እንጂ መች በግድ ይመጣል?!”  ያለው ቶልስቶይ ነው አይደል? ---
የኢትዮጵያ አምላክ ፊቱን የመለሰላት መሰለኝ፤ ለአፍታም ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ሰማይ ዘርግታ በዓይነ ሕሊናዬ አየሁዋት። ነገር ግን ለወገኔና ለትውልዴ  በእዝነ ልቡናዬ ጠየኩ፦
ፈጥነን የእግዚአብሔርን ምህረት፣ ተራዳኢነት፣ አጋጣሚ የመሰለውን ተአምር ረስተን ይሆን??
ይህቺዋ ኢትዮጵያችን  በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ዘመንዋ እንዲረዝም (ምሳ 28 : 2)፣ በቅኑ በረከት ከተማችን ከፍ ከፍ እንድትል  (ምሳ 11 : 11)፣ ይኸው ዙፋን በምሕረት እንደቀና (ኢሳ 16 : 5) እናስብ።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል ብለን የምንጠብቀውና ግድ የሚለው፣ እንደ ቀላል የማንቆጥረው የኢትዮጵያ አምላክ፣ የምድር ዳርቻም ፈጣሪ ምሕረትን በልብ ማሰብና ከልብ ምስጋናውን አለመሰወር ቢቻልም በአፍም ለመመስከር  አለማፈር ነው።
ልናውቀው ልንረዳው የቻልነው ይህ ተአምር ይህ ምሕረት ብቻ ነገንና ወደፊታችንን ከተስፋ ጋር ያስችለናል።


Read 2023 times