Tuesday, 01 October 2019 10:25

130 ፓርቲ የሚርመሰመስበት አገር፣ ጤና አይሆንም፡፡ በጭራሽ!

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(2 votes)

“በአራት ዓመት አንዴ” የተሰኘው የምርጫ ሂደት፣ በስፔን እየተረሳ ነው፡፡ በየአመቱ ሆኗል:: ባለፈው ሚያዝያ ወር፣ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ገና ግማሽ ዓመት ሳይሞላ ነው፤ እንደ አዲስ አሁን፣ ሌላ የምርጫ ዘመቻ የተጀመረው (ከወር በኋላ ምርጫ ለማካሄድ):: በ4 ዓመታት ውስጥ፣ 4ኛው ምርጫ መሆኑ ነው፡፡
በተመሳሳይ ጊዜ፣ ሚያዝያ ላይ፣ በአገረ እስራኤል የተካሄደው ምርጫም፣ “ለአራት ዓመት ዕድሜ” አልታደለም፡፡ እንደገና ባለፈው ሳምንት፣ ምርጫ ተካሂዷል፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው? “ተመራጭ” የሌለው ምርጫ ሆኗል፡፡ ከግማሽ (ከ50%) በላይ የድጋፍ ድምጽ የሚያገኝ ፓርቲ ጠፋ፡፡
ከግማሽ በላይ የፓርላማ ወንበር ማሸነፍ ማለት ነበር፣ “ተመራጭ” ፓርቲ መሆን ማለት፡፡ ያኔ መንግስትን የማስተዳደር ስልጣን ይኖረዋል፡፡
ዛሬ ዛሬ ግን፣ ከ50% በላይ የድጋፍ ድምጽ ማግኘትና ማሸነፍ፣ ለአብዛኞቹ ፓርቲዎች፣ “ድሮ ቀረ” የሚያሰኝ የሩቅ ምኞት ሆኖባቸዋል፡፡
ለነገሩ፣ በርካታ አንጋፋ ፓርቲዎች ራሳቸው፣ “ታሪክ” ሆነው ቀርተዋል፡፡ ለአርባና ለሃምሳ ዓመታት፣ ስልጣን ላይ ሲፈራረቁ የቆዩ አውራ ፓርቲዎች፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ እንደዘበት ከጨዋታ ወጥተዋል፡፡ የድሮ ታሪክ ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡
ከሁለቱ ዋና የእስራኤል ፓርቲዎች መካከል አንዱ የነበረው፣ ሌበር ፓርቲ፣ በሰሞኑ ምርጫ፣ 6 የፓርላማ ወንበር ብቻ ነው ያሸነፈው (ከ120 ወንበር)፡፡ እንደ ድሮ ከ50% በላይ ሳይሆን 5% ብቻ፡፡
በኤርያል ሻሮን የተመሰረተውና፣ ለጥቂት ዓመታት የገነነው ካዲማ ፓርቲ፣ ዛሬ የለም፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሊኩድ ፓርቲ ነው፡፡ ከመሞት እንደገና ያንሰራራ ዋና ፓርቲ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን፣ በምርጫ የሚያገኘው ውጤት እንደ ድሮ አይደለም:: ከ120 ወንበር፣ 33 ወንበር አሸንፏል፡፡ በምርጫው ቀዳሚ ሆኖ የወጣው፣ “Blue & white” ፓርቲስ? አንጋፋውን “ሌበር ፓርቲ” ከቦታው ያፈናቀለ አዲስ ፓርቲ ነው፡፡ 35 ወንበሮችን በማሸነፍ ቀዳሚ ሆኗል:: 30% በማይሞላ የምርጫ ውጤት “አንደኛ ወጣ”፡ “አሸነፈ” ሊባልለት ይችላል፡፡
ግን የምርጫ ፋይዳ፣ ፓርቲዎችን አወዳድሮ፣ ለስልጣን የሚበቃ “ተመራጭ ፓርቲ” ለመለየት ነው እንጂ፤ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ድረስ የወጡ ቀዳሚ ፓርቲዎችን ለመሸለም አይደለም፡፡
ለዚያ ለዚያማ፤ ባለፈው ሚያዝያ በተካሄደው የስፔን ምርጫም፣ ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች፣ 1ኛ እና 2ኛ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን፣ 1ኛ የወጣውና “አሸናፊ” ተብሎ በደስታ የተጨፈረለት ፓርቲ፣ ከ350 የፓርላማ ወንበር ውስጥ 123 ብቻ ነው ያሸነፈው፡፡
አንደኛ ቢወጣም፣ “የፌሽታ ፓርቲ” ቢደግስም፣ በ35% ውጤት ብቻ፣ ስልጣን መረከብ አይችልም:: የባከነ ምርጫ!
እና ምን ተሻለ? እንደገና ሌላ ምርጫ ማካሄድ? ሦስት ምርጫዎች በከንቱ መክነው ሲቀሩ፣ እንደገና በየዓመቱ ሌላ ምርጫ መሞከር፣ እስከመቼ? ክፋቱ ደግሞ የብዙ አገራት በሽታ መሆኑ ነው፡፡
የፓርቲዎች እርባታና ትርምስ
አንጋፋ ፓርቲዎችን የሚያዳክም፣ አንዳንዶቹንም ከጨዋታ የሚያስወጣ፣ ብዙ አዳዲሶችን የሚፈለፍል፣ ምርጫዎችን ያለአሸናፊ የሚያመክን አስቸጋሪ ፈተና የገጠማቸው፣ እስራኤልና ስፔን ብቻ አይደሉም፡፡
ብዙ አገራትን ያዳረሰ ችግር መሆኑን ለማመልከት፣ “የዘመናችን ወረርሽኝ” እንደሆነ ለመግለፅም፣ “The age of Fragmentation” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡
ለምን?
ባለፉት አስር ዓመታት፣ አዳዲስ ፓርቲዎች ከመፈጠራቸውም በተጨማሪ፣ ከነባሮቹ ውስጥ ተነጥለው የሚወጡ ጥቃቅን ፓርቲዎች መበራከታቸው፣ አንዱ ምክንያት ነው፡፡
በእርግጥ፣ አዳዲስ ወይም ጥቃቅን ፓርቲዎች ድሮም ይፈጠሩ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ያን ያህልም  ከቁጥር የሚገባ የድጋፍ ድምጽ ስለማያገኙ፣ አንጋፋዎቹን ፓርቲዎች የመፈታተን እድል አልነበራቸውም፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን፣ አምና የተፈጠሩ ፓርቲዎች፣ ዘንድሮ ለነባሮቹ ፓርቲዎች የጐን ውጋት ይሆኑባቸዋል፡፡ አዲሶቹ ፓርቲዎች ውጋት ከመሆን አለማለፋቸው፣ አድገውና ጎልብተው በወጉ ማሸነፍና መንግስት የመመስረት ብቃት ላይ አለመድረሳቸው ነው ችግሩ::
“እጅግ የተረጋጋች አገር” የምትባለዋን ጀርመንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች (CDU እና SPD) በተቀናቃኝነት፣ አንዱ በምርጫ አሸንፎ ስልጣን እየያዘ፣ ሌላኛው ፓርቲ በተራው ተመርጦ ስልጣን እየተረከበ፣ በመሪነት ሲፈራረቁ ስንት ዓመታቸው?
በየመሃሉ ብቅ የሚል ፓርቲ አልጠፋም፡፡ ብቅ እያለ ይከስማል፡፡ ወይም ከ10% በላይ የድጋፍ ድምጽ ማግኘት እየተሳነው፣ ያዘግማል፡፡ አንጋፋዎቹ ሁለቱ ፓርቲዎች ግን፣ እንደወትሮው በምርጫ አንዱ ሌላውን እያሸነፈ ስልጣን ላይ ይፈራረቃሉ (አንዱ 50 ምናምን፣ ሌላኛው 40 በመቶ ገደማ ውጤት እያገኘ)፡፡ ይሄ የቀድሞ ታሪክ ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ ግን፣ የአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች የምርጫ ውጤት፣ 33% እና 25% ገደማ ነው፡፡ የጀርመን ሁለቱ ተቀናቃኞች በመጣመር ብቻ ነው፤ ስልጣን መያዝ የሚችሉት፡፡ እንደምታዩት፣ አውራዎቹ ፓርቲዎች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡
የዛሬ ሁለት ወር በተካሄዱ የክልል ምርጫዎች ላይም፣ የማገገም ምልክት አልታየባቸውም፡፡ እንዲያውም፣ የሁለቱ አውራ ፓርቲዎች ውጤት ተደምሮ፣ 50% መሙላት ስላቃተው፣ ከሌላ ሦስተኛ ተቀናቃኝ ፓርቲ ጋር ጥምረት ካልፈጠሩ፣ ስልጣን መያዝ አይችሉም፡፡
ለምን? አንጋፋዎቹ እየተዳከሙ፣ ጐን ለጐን ደግሞ፣ የዛሬ አምስት ዓመት የተፈጠረ አዲስ ፓርቲ፣ ከአንጋፋዎቹ ጋር የሚቀራረብ 25% ገደማ የድጋፍ ድምጽ እስከማግኘት ደርሷል፡፡
በጣሊያንማ፣ ከቁብ የማይቆጠሩና አዳዲስ ፓርቲዎች ድንገት ገዝፈው፣ በምርጫ አንደኛና ሁለተኛ ሆነዋል፡፡ የድሮዎቹ አንጋፋ ፓርቲዎች ከቦታቸው ተፈናቅለዋል፤ አዲስ ፓርቲዎች ዋና የስልጣን ተቀናቃኞች ሆነዋል፡፡ ግን፣ አንደኛና ሁለተኛ መውጣት እንጂ፣ ከ50%  በላይ ድጋፍ ማግኘት አልሆነላቸውም፡፡
በፈረንሳይም፣ የአንድ ዓመት ዕድሜ ያልነበረው ፓርቲ፣ ስልጣን ይዟል፡፡
130 ፓርቲ ይቅርና 13 ፓርቲም በሽታ ነው፡፡
ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ኦስትሪያ… በአውሮፓ ምድር፣ ከዚህ የዘመኑ ወረርሽኝ ያመለጠ አገር የለም ቢባል ይሻላል፡፡ በአጭሩ፣ እንደ ድሮ፣ የአውሮፓ ፖለቲካ፣ ደልዳላ አይደለም:: እየተናጋ ነው፡፡ የመፍረክረክና የመሰነጣጠቅ ወረርሽኝ የተስፋፋበት ስለሆነም፤ “Democracy” ፣ በዘመናችን፣ በ Splintocracy ማዕበል እየተናጠ ነው ያስብላል፡፡
የኢትዮጵያና የአፍሪካ አገራት ፖለቲካ፣ ወደተደላደለ የአውሮፓ ፖለቲካ ከመራመድ ይልቅ፣ በተቃራኒው፣ የአውሮፓ ፖለቲካ የኋሊት የኢትዮጵያን ለመምሰል ዳዳው እንዴ? እኛ ጋ ለመድረስ የአውሮፓ አገራት ገና ብዙ ይቀራቸዋል:: በአውሮፓ ደርዘን ፓርቲዎች፣ አገርን ያጨናንቁ ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ግን 130 ፓርቲዎች ናቸው የሚርመሰመሱት፡፡ በዚህ ሁኔታ፣ የተረጋጋ፣ በህግና ስርዓት የሚተዳደር አገር ማጽናት ዘበት ነው፡፡ እንኳን የ130 ፓርቲዎች ውሽንፍር ይቅርና የ13 ፓርቲዎች ግርግርም አገርን እንደሚረብሽ በደልዳላ የአውሮፓ ፖለቲካም ውስጥ ሳይቀር ታይቷል፡፡
ዘመነኛው ወረርሽኝ ወደ አሜሪካና ወደ እንግሊዝ እንኳ ደርሷል’ኮ፡፡
የመልክና የመጠን ጉዳይ እንጂ፣ ከበሽታው አላመለጡም፡፡ ፋታ በማይሰጥና መቋጫው በማይታወቅ ውዝግብ ሲታመስ ውሎ፣ በዚያው እንቅልፍ አጥቶ ሲካሰስ በሚያነጋ የፖለቲካ ድር፣ ሦስት ዓመት ሙሉ ተተብትቦ መዳከር፣ የጤና ነው እንዴ?
በእንግሊዝ፣ አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ከያዙት አቋም በተቃራኒ ነው አብዛኛው መራጭ፣ “ከአውሮፓ ህብረት መገላገል”ን በመደገፍ ድምጽ የሰጠው፡፡ ግን፣ ይሄውና ሦስት ዓመታቸው፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ሲነታረኩ፣ ሲጨቃጨቁ፣ አገሪቱ በእንጥልጥል ትዋልላለች፡፡ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ከስልጣን አውርዶ፣ ሦስተኛውን አሁን መከራ እያበላ ነው - የእንግሊዝ ዘመነኛ የፖለቲካ ግርግር፡፡
የአሜሪካስ? “ቅንጣት የማሸነፍ እድል አይኖራቸውም” ተብለው፣ እንደ መዝናኛና እንደ አዳማቂ ወይም እንደ ጊዜያዊ አዋኪና አደፍራሽ የተቆጠሩት ዶናልድ ትራምፕ፣ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውኮ ተራ ክስተት አይደለም:: አንዳንዱ በድንጋጤ፣ አንዳንዱ በግርምት የሚደነዝዝ፣ አልያም ደግሞ፣ በቁጣ ገንፍሎ የሚወራጭና ባልተጠበቀ የእልህ ደስታ የሚቦርቅ ነበር የበዛው፡፡
በሁለቱ የአሜሪካ አውራ ፓርቲዎች ውስጥ ቅንጣት ቦታ ያልነበራቸው፣ የፖለቲካ ምርጫ ውስጥ ዝር ብለው የማያውቁ ሰውዬ፣ ድንገት መጥተው ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ብሎ ማን አሰበ? በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች እንደዚያ አይነት ሃሳብ ሲናገሩ እንኳ፣ ጋዜጠኞች ተንከትክተዋል፡፡  አዳራሾች በሳቅ ተሞልተዋል፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ የሁለቱ ፓርቲዎች አንጋፋና ታዋቂ ፖለቲከኞች ከግራ ከቀኝ ክፉኛ የተቃወሙትና የዘመቱበት ጀማሪ ፖለቲከኛ፣ ምርጫውን አሸነፈና አገሬው ተናወጠ፡፡
ነውጡ እስከዛሬ አልበረደም፡፡ በየእለቱ ውዝግብ ነው፡፡ የድሮ አይነት ትችት፣ ወቀሳና ተቃውሞ፣ የተለመደው አይነት ይሁንታ፣ አድናቆትና ድጋፍ ዛሬ ብዙም ትኩረት አያገኝም፡፡ ይልቅስ ክስና ውንጀላ ነው የበዛው፡፡ አዎ፣ ካሁን በፊት በፕሬዚዳንት ክሊንተን ጊዜ፣ ከዚያም በፊትና በኋላ፣ አልፎ አልፎ  ‹‹ከስልጣን የማውረድ ውንጀላና ክስ” ታይቷል:: ዛሬ ዛሬ ግን፣ የእለት ተእለት ትዕይንት ሆኗል፡፡ “ፕሬዚዳንቱ በስደተኞች ላይ ያወጡት ገደብ ወንጀል ስለሆነ፣ ይከሰሱ፣ ይውረዱ” ተብሎ በአገሬው ኮንግረስ (ፓርላማ) ውስጥ ረቂቅ አዋጅ ይቀርባል፡፡
“ፕሬዚዳንቱ ዘረኛ አስተያየት ጽፈዋል” ተብሎ ከስልጣን እንዲባረሩ ሌላ ረቂቅ አዋጅ፤ ሰሞኑን ደግሞ ‹‹በዩክሬን ፕሬዚዳንት ላይ ጫና በማሳደር ተፎካካሪያቸው ላይ አሲረዋል›› ተብሎ አዲስ የውንጀላ ቀውጢ ተፈጥሯል፡፡ ውንጀላ በላይ በላይ ነው፡፡ ይሄ ድሮ ያልነበረ በሽታ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱም፣ ለአፀፋ ውንጀላ አይናቸውን የሚያሹ አይደሉም፡፡ ምናለፋችሁ፣ ፖለቲካው ቀን ከሌት እየተናጠ ነው፡፡ የጤናማዎቹ የእነ አሜሪካ እና የእነ እንግሊዝ ፖለቲካ እንዲህ ሲታመም፣ ሌላው የሌላውማ ለይቶለት ተበላሽቷል፤ ብሶበት ተተራምሷል፡፡
በአጭሩ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለአምባሳደሮች እንደተናገሩት፣ የዘመናችን ፖለቲካ ተቀይሯል፡፡ የአለማቀፍ ግንኙነት ላይ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ለመግለጽ ነው ይህን የተናገሩት፡፡
ነገር ግን፣ የፕሬዚዳንቷ ማሳሰቢያ፣ የአገር ውስጥ ፖለቲካ ላይም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል፡፡
“የ130 ፓርቲ ፖለቲካ”፣ ፈጽሞ የጤና አይደለም:: “በሚያለያየን ነገር ተቻችለን፣ በሚያስማማን ጉዳይ ላይ ተባብረን እንሰራለን” የሚለውን ፈሊጥ እየደጋገሙ መደስኮር መፍትሔ አይሆንም፡፡
የአውሮፓ ደርዘን ፓርቲዎች እንኳ፣ “ተባብረን እንስራ” ብለው መንግስት መመስረት ፈተና እየሆነባቸው ነው፡፡
ደግሞስ፣ ለመተባበርና ለመጣመር የሚፈልጉ ከሆነ፣ ከምርጫና ከስልጣን በፊት፣ ፓርቲዎቻቸውን “በሚያስማማ ነገር ላይ ማስተባበርና ማዋሀድ” በቻሉ ነበር፡፡     

Read 6733 times