Tuesday, 01 October 2019 10:19

አገባሽ ያለሽ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ አንድ ትንሽ ልጅ ነበራቸው:: በአብዛኛው ልጃቸውን ሲያስፈራሩ፡-
‹‹ዋ! ለጅቡ ነው የምንሰጥህ!›› ይሉታል፡፡
ጅብ ከውጪ ሆኖ ያዳምጣል፡፡
እናትና አባት ልጃቸውን አባብለው፣ አረጋግተው አስተኙት፡፡
ቆይተው አያ ጅቦ መጣ፡፡
‹‹እንዴት ነው የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?››
ቤተሰብ ልጁን አቅፎ ለጥ ብሏል፡፡ ማንም የቱን እንደሚጠይቅ አያውቅም::
አያ ጅቦ ነገሩ ሁሉ ግራ ይገባዋል፡፡ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ልጁን አይጥሉትም::
ሲቸግረው፤
‹‹ኧረ ጎበዝ፤ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?››
ቤተሰቡ ሁሉ በር ዘጋግቶ ለጥ ብሏል፡፡
አያ ጅቦም ‹‹አዬ ሰውን ማመን?›› እያለ ወደ ጫካው ሄደ፡፡
***
ተስፋ የምናደርገው፣ የምንመኘው ሁሉ ይፈፀምልናል ማለት አይደለም፡፡ ይሆናል ያልነው ሳይሆን፣ አይሆንም ያልነው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ክስተት መቀልበስም ላይሳካ ይችላል፡፡ ከበደ ሚካኤል ያገራችን ዕውቅ ደራሲ፡-
አለ አንዳንድ ነገር
አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር
የሚሉት ለዚያ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለዚህ ነው፡፡ አገር በአንድ ጀምበር አትቀናም፡፡ አብዬ ዘርጋው የከርሞ ሰው ዋናው ገፀ ባህሪ፤
“…ተስፋዬ እንደጉም መንጥቃ
ምኞቴ እንደጉድፍ ወድቃ
የወንድሜን ልጆች እንኳ ለርስታቸው ሳላበቃ
የኔ ነገር በቃ በቃ…”
የሚለን ለዚህ ነው፡፡
በዚህ የመስቀል በዓል የሚበራው ችቦ ሁሉ ቀናችንን ያፈካልን ዘንድ ልባችን እንደ ደመራው እናብራ! እንደችቦው እናፍካው፡፡ ብርሃን ፀጋ ነው! ብርሃን የብሩህ ነገ ምልክት ነው!
የመስከረም ፀሐይ ፍንትው ብላ ስትወጣና፣ ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ እንደሚሉት “አደይ ተከናንባ ስትስቅ መሬት” በሚሉት ግጥማቸው፡-
“…ማን ያውቃል እንዳለው ለድንጋይስ ቋንቋ
ዛፍ፤ ለሚቆረጥ ዛፍ እንዳለው ጠበቃ
ማን ያውቃል?
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል?...”
ይላሉ፡፡
አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ዕቅድ ማቀድ፣ አዲስ ህልም ማለም፣ አዲስ ነገን ማየት የብዙሃን አስተሳሰብ ገጽታ ነው፡፡ በየዓመቱ የምንገልፀው ገጽ አለን፡፡ የምናገኘው ገጽም አለን፡፡ ዋናው ልባችንን ንፁህ ማድረግ ነው!
እስቲ ዘንድሮ ልባችንን ንፁህ አድርገን እንነሳ!
ዕውነትን ካልደፈርን ውሸት ይወረናል፡፡ ፀሐፊው እንዳለው “ዕውነት የጉዞ ጫማዋን እስክታጠልቅ ውሸት ዓለምን ዞራ ትጨርሳለች፡፡” ዕውነቱ ይሄው ነው፡፡ “እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ” የምንለው እንደው የዓመት አመል ሆኖብን አይደለም፡፡ ብርሃን የፍቅርና የተስፋ ማፀህያ ስለሆነ እንጂ!
ይህ የመስቀል በዓል ለክርስትና አማኞች የተስፋ፣
የመልካም ምኞት፣
የመፈቃቀር፣
ከክፉ ሃሳብ የፀዳ፣
አገርን የሚያለመልም፣
የህዝብን መንፈስ የሚያድስ፣
የዘራነውን የሚያስቅም፣ የወለድነውን የሚያስም እንዲሆን በልባችን ደግ በኩል እንመኝ!
ዓመቱን የተባረከ ያድርግልን!

Read 10306 times