Tuesday, 01 October 2019 10:12

“ኢትዮጵያን ማንም ከማያወርድበት ሰገነት ላይ ለማውጣት እንነሳ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)


             የመስቀል በዓል በዐደባባይ ከሚከበሩ የኢትዮጵያውያን በዓላት መካከል አንዱ ነው፡ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህንን ታላቅ በዓል በአደባባይ እንድናከብረው ሥርዓት ሲሠሩ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡
ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ሦስት ታላላቅ ሐሳቦችን ሁላችንም እንድንመራባቸው ፈልገው ሳይሆን አይቀርም፡፡
እውነትን ቀብሮ መኖር እንደማይቻል፤ ታሪክ የሚለወጠው በቆራጥነትና በአንድነት መሆኑን፤ አንድ ታላቅ ሐሳብ ኢትዮጵያውያንን እንዲጠቅም ከፈለግን ሐሳቡን ኢትዮጵያዊ ማድረግ እንዳለብን፣ በዓሉ በደመራው ብርሃን ወገግ አድርጐ ያሳየናል፡፡
የክርስቶስን መስቀል የቀበሩ ሰዎች፣ እውነትን ለዘለዓለም ቀብረው ማስቀረት የሚችሉ መስሏቸው ነበር፡፡ ለጊዜው መስቀሉ ከአፈር ሥር ሲቀበር፣ ዓላማቸው የተሳካላቸው መስሏቸው ነበር፡፡ በመስቀሉ ላይ የቆሻሻ ክምር እንዲከመር ሲያደርጉ መስቀሉን ከታሪክ ገጽ ያጠፉት መስሏቸው ነበር፡፡ ይህ ግን የመሰላቸውን መስሎ መቆየት የቻለው (የዋሆችም መስቀሉ ተቀብሮ፣ ተረስቶ፣ ትቢያ ሆኖ ጠፍቷል ብለው እንዲረሱት ያስቻላቸው) ዕሌኒ የምትባል ብርቱ እንስት፣ ከተለየ ብርታት፤ ጽናትና የይቻላል መንፈስ ጋር እስክትከሰት ድረስ ብቻ ነበር፡፡
በየመዘናቱ እውነትን ለመቅበር የሞከሩ ነበሩ፡፡ በተንኮል፤ በሤራ፣ በግጭት፣ በክፍፍል፣ በጦርነት፣ በጉልበትና በኃይል እውነትን ለመቅበር ብዙዎች ሞክረዋል፡፡ እውነተኞችን በማጥፋትና በመግደል፣ በማሠርና በማስፈራራት እውነት የምትጠፋ መስሏቸው ብዙ ደክመዋል፡፡ መጻሕፍትን አቃጥለዋል፤ የዕውቀት ቦታዎችን አውድመዋል፡፡
እውነት ግን ብትቀጥንም አትበጠስም፡፡ እውነተኞችን በመግደልና በመቅበር በፍጹም እውነትን ማጥፋት አይቻልም፡፡
እውነትና ተስፋ አብረው የሚሄዱ ናቸው:: እውነተኞች ተስፈኞች ናቸው፡፡ ውሸተኞች ጨለምተኞች ናቸው፡፡ ከእውነት ጋር ያልቆመ ሰው፣ ተስፋ ሊኖረው አይችልም፡፡ ተስፋ እውነተኛ ሰው ብቻ የሚያደርገው መነጽር ነውና፡፡ ተስፋ ባለበት ሁሉ እውነት ትኖራለች - እውነት ባለችበትም እንዲሁ፡፡
መስቀሉን የቀበሩት ሰዎች ሐሰተኞች ስለነበሩ ወደፊት የሚወጣ አልመሰላቸውም፡፡ የመስቀሉ ወዳጆች ግን እውነተኞች ስለነበሩ አንድ ቀን እንደሚገለጥ ያምኑ ነበር፡፡ ለዚህ ነው፣ መስቀሉ የት እንደተቀበረ፣ ከልጅ ልጅ በሚተላለፍ የቃል ትውፊት መረጃውን ለዘመናት አቆይተው፣ ለመስቀሉ አስተርእዮት ዘላለማዊ ገድል የፈጸሙት፡፡
ኢትዮጵያውያን፣ ታላቅ፤ የበለፀገችና ለሁላችንም እንድትሆን ለማስቻል የያዝነው ዓላማ መሳካቱ የማይቀር እውነት ነው፡፡ ይህን እውነት የሚገዳደሩ ኃያላን ይኖራሉ፡፡ ለጊዜው ዝናራቸውን እስኪጨርሱ፣ ጉልበታቸውንም እስኪያፈሱ ድረስ፣ ያሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ድምፃቸው  እንደ ነጐድጓድ፣ ጩኸታቸውም እንደ ብዙ ፏፏቴዎች የወል ጩኸት፣ ጐልቶ ይሰማ ይሆናል፡፡ እውነታችንን የቀበሩት መስሏቸው፣ ለጊዜው ይደሰታሉ፡፡ በዙሪያችን ያሉትም፣ እውነታችን የተቀበረ መስሏቸው፣ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡
ይህ ግን የእውነትን ባሕሪይ ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡፡ እውነትን መገዳደር እንጂ ማሸነፍ፣ መቃወም እንጂ ማጥፋት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ የብዙዎች ጩኸት፣ የሰነፎች ተረትና የአላዋቂዎች ትምክህት፣ እውነትን ሊያጠፋት እንደማይችል በጽኑ እናምናለን፡፡ እውነት፣ የተቀበረችበትን ዐመድ እንደ ፍግ እሳት አሙቃ፣ እንደ ገሞራ ትፈነዳለች፡፡ የተሸፈነችበትን አቧራና የክፋት ቁልል፣ ቅርፊቱን እንደሚሰብር ጫጩት፣ ፈንቅላ ትነሳለች፡፡
ነገ ከእውነተኞች ጋር ናት፡፡ እውነተኞች ዛሬ ጥቂቶች ቢመስሉም፣ ነገ እየበዙ ይሄዳሉ፣ ሐሳውያን ዛሬ ብዙዎች ቢመስሉም፣ ነገ እንደ ስንቅ እያነሱ ይሄዳሉ፡፡ ለዚህ ነው፣ ከኢትዮጵያ እውነት ጋር እንቆም ዘንድ፣ እስከ የትኛውም ጥግ ተጉዘን፣ የትኛውንም እንቅፋት በጀግንነት እንሻገር ዘንድ የምንታገሰው፡፡
ማንም በማያስብበት፣ ነገሩ ሁሉ የተረሳ በሚመስልበት፣ ኃያላን ሁሉ ዝም ባሉበት፣ በዚያ ጊዜ ዕሌኒ የምትባለ ቆራጥ እናት ተነሳች:: ማንም የማይደፍረውን ደፈረች፡፡ ከእውነት ጋር ለመቆምም ቆረጠች፡፡ ያልተሞከረውን ለመሞከር፣ የማይታሰበውን ለማሰብ ወሰነች፡፡
ታሪክ በሥራ እንጂ በወሬ አይለወጥም:: የሚያወሩ ሰዎች በታሪክ ውስጥ ያልፋሉ:: ታሪክ ግን አይሠሩም፡፡ ማኅበረሰቡ የሚያውቀውን፣ የለመደውን፣ ደጋግሞ የሞከረውን ነገር በማድረግ ታሪክ አይለወጥም፡፡ ሌሎች ባዘገሙበት መንገድ ብቻ ደጋግሞ በመጓዝ፣ ካሰቡት ለመድረስ አይቻልም፡፡ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ፣ አዲስ መንገድ መከተል፣ አዲስ ልማድም መትከል አዲስ ሥራም መሥራት ይጠይቃል፡፡
ጫካ የሚያቃጥል እሳት ከአንዲት ክብሪት ይነሳል፤ ሀገር የምትለውጥ ውብ ሐሣብም ከአንዲት ቦታ ትመነጫለች፡፡ ተገዳድለን፤ ተጨፋጭፈን፣ ተናቁረን ሞክረነዋል፡፡ ማሳደድና ማሠር የታሪካችን አካላት ሆነዋል፡፡ ሤራና ሸር፣ “ይውደምና ይመታ”፣ መዛግብተ ቃላትን ሞልተውታል፡፡ ለዚህ ነው፣ በአዲስ መንገድ እንሂድ ብለን የተነሳነው፡፡
ዕሌኒ፣ እንደብዙዎቹ የዓለማችን ባለ ቅን ልብ ቅን ሰዎች፣ ዓይነተኛ የመደመር ተምሳሌት ናት:: የእርሷ ቆራጥነት፣ የሕዝቡ ፀሎት፣ የወታደሮቹ ብርታት፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሰዎች ትጋት፣ መረጃውን የሰጧት ሰዎች ቀናነት፣… እነዚህ ሁሉ አስተባብራ፣ ሐሳቧን ተግባር፣ ተግባሯን ታሪክ ለማድረግ ቻለች፡፡ “ተቀበረ” የሚለውን ታሪክ፣ “ወጣ” በሚለው ቀየረችው፡፡ “ጠፋ”ን በ “ተገኘ” “ተሰወረ”ን በ “ተገለጠ” አጸደለችው፡፡
እውነትና ተስፋ ነበሯትና፣ የሚቻል የማይመስለውን ቻለች፤ ተራራውን ናደች:: የውሸትን ክምር አፍርሳ፣ የእውነትን ሐውልት አቆመች፡፡ አይሆንም የተባለው ሆነ፡፡ አይቻልም የተባለው ተቻለ፡፡ ቀባሪዎቹ አልፈው፣ የተቀበረው ህያው ሆነ፡፡ የቀባሪዎቹ ታሪክ ተዘግቶ፣ የተቀበረው ታሪክ ተከፈተ፡፡ ለዚህ ነው ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን፣ የመስቀልን በዓል ከየቦታው በሚሰበሰብ እንጨት፣ ከእንጨቶችም በሚሠራ ደመራ እንድናከብረው ያደረጉን፡፡ እውነትን ለማጽናት፣ ከመደመር የተሻለ ነገር የለም ሲሉን ነው፡፡
መሟላት እንጂ መባላት እንደማይበጀን፣ ትግግዝ እንጂ ውግግዝ እንደማይረባን፣ ትቅቅፍ እንጂ ንቅቅፍ ዋጋ እንደሌለው፤ ዕሌኒ አሳይታናለች፡፡ በዚያ የመስቀል ፍለጋ ጉዞዋ፣ ክርስቲያኖችንም፣ አይሁድንም፣ ሌላ እምነት ያምኑ የነበሩትንም አስተባብራለች፡፡ መንገዷ የጥበብ እንጂ፣ የመጥበብ አልነበረም፡፡ ጉዞዋ ሁሉንም ለእውነት ለማንበርከክ እንጂ፣ አንዱን ለሌላው ለማንበርከክ አልነበረም፡፡ ዛሬ - ሁሉም የታሪኩ ባለቤት ሆነዋል፡፡
አባቶቻችንና እናቶቻችን ግን ይህን ታላቅ ነገር፣ ወደ አገራችን አምጥተው፣ ኢትዮጵያዊ አድርገውታል፡፡ ከእኛው መልክአ ምድር፣ ከእኛው የዘመን አቆጣጠር፣ ከእኛው ባህል ጋር አስማምተው፣ ኢትዮጵያዊ መልክ ሰጥተውታል:: በብዙ ማህበረሰቦች ዘንድ፣ በእያንዳንዱ ገጠር፣ ዘመናትን እየተሻገረ እንዲሄድ አስችለውታል፡፡ የእኛው የመስቀል አከባበር፣ ዓይነተኛ ቅርሳችን ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበውም ለዚህ ነው፡። ኢትዮጵያዊ ስለሆነ፡፡
ሁሉን ነገር መቅዳት፣ ቀድተን እንዳለ  በአገራችን ምድር ላይ መድፋት፣ ውጤት አላመጣም፡፡ ሀሳቦችን፣ ልምዶችን፣ መርሆችን፣ እውቀቶችን፣ ከሚገኙበት ወስደን ኢትዮጵያዊ መልክ ልንሰጣቸው ይገባል፡። ከኛው ባህል፣ እምነት፣ ልማድ፣ አስተሳሰብ፣ አኗኗርና ፍላጎት ጋር ማጣጣም አለብን፡፡ መደመር እንዲህ ነው፡፡
ከምዕራብም ከምሥራቅም አየን፣ በጎ በጎው ወሰድን፣ የራሳችንን ሐሳብ አዋለድን፣ ከኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ፣ ፍላጎትና አቅም ጋር አዋሀድን፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ የመደመር መንገድንም ጀመርን፡፡ ቀደምቶቻችን፣ የመስቀል በዐል በየመንደሩ እስኪደርስ ድረስ እንደደከሙት ሁሉ፣ መደመርም በየኪሳችን እስኪገባ ድረስ መድከም አለብን፡፡
አንዴ ከምዕራብ፣ ሌላ ጊዜ ከምሥራቅ አምጥተን፣ ምሥራቁንና ምዕራቡን ለመሆን ጥረን ነበር፡፡ እየቀዳን የምናመጣው ግን፣ በኢትዮጵያ ምድር ሊያፈራ አልቻለም፡፡ ለዚህ ነው፣ ግራ ቀኙን አይተን፣ የኛኑ ችግር በኛው መፍትሔ ለመሞከር የተነሳነው፡፡ በመደመር፡፡
መደመር፣ እንደ ደመራው ሁሉ፣ በየመንደሩ በየጥጋቱ ሁሉ ማብራት አለበት፡። ዛሬ፣ የደመራ በዓላችንን ለማየት፣ ዓለም ሁሉ ወደ እኛ እንደሚመጣው ሁሉ፣ ነገ መደመር ያስገኘልንን ለውጥና ብልጽግና፣ የተለምነውም የፍቅር ጎዳና ለማየት፣ አይተውም ለመደመር፣ ብዙዎች ይመጣሉ፡፡
እውነተኞች ተስፋ አላቸው፡፡ ደመራን በየአመቱ የሚያይ ሕዝብ፣ መደመር የሚኖረውን ሀይል ይገነዘባል፡፡ መደመርም እንደ ደመራው ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ኢትዮጵያዊ - የኢትዮጵያ መንገድ፡፡
እንደ ዕሌኒ ታሪክ ለመለወጥ ቆርጠን፣ በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ በእውነትና በፍቅር አስተባብረን፣ እንደ ደመራው ተደምረን - ኢትዮጵያን ማንም ከማያወርድበት ሰገነት ላይ ለማውጣት እንነሳ፡፡
መልካም የመስቀል በዓል ይሁን፡፡
 

Read 6743 times