Tuesday, 01 October 2019 10:02

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብዛኞቹ ጥያቄዎች በወር ውስጥ ምላሽ ያገኛሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጥያቄዎች ለማስመለስ የተመሠረተው የተለያዩ ማህበራት ኮሚቴ በ10 ቀናት ውስጥ ከስድስት ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ጋር ያደረገው ውይይት መልካም ምላሽ የተገኘበት መሆኑን ጠቁሞ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹ የቤተክርስቲያኒቱ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው በ10 መሰረታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱና አማኒያኑ ጥያቄዎች ላይ አተኩሮ ከአማራ፣ ከደቡብ፣ ሶማሌ፣ ሃረር፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ ድሬደዋና አዲስ አበባ አስተዳደርና ክልሎች ፕሬዚዳንቶችና ም/ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም አስተዳዳሪዎች ጋር ፍሬያማና ቀና ውይይት ማድረጉን ለአዲስ አድማስ ያስታወቁት የኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ፤ እንደየ አካባቢዎቹና ጥያቄዎቹ ሁኔታ ችግሮች የሚፈቱበት ቀነ ገደብ መቀመጡን አመልክተዋል፡፡ በቀጣይም የእነዚህን ምላሾች አፈጻጸም በአንክሮ እየተከታተለ በየ15 ቀኑ ለሕዝብ ያሳውቃል ብለዋል - ቀሲስ ሙሉቀን፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠትም ከ10 ቀናት ጀምሮ የረጅም ጊዜ ቀነ ገደቦች የተሰጠ ሲሆን አብዛኞቹ ጥያቄዎች ግን በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ እንዲመለሱ መግባባት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
እስከ ጥቅምት 30 ድረስ በጣም በርካታ ጉዳዮች መፍትሔ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ረጅም ጊዜ የተሰጣቸውንም አካሄዳቸውን ገምግመን ሂደቱን ለሕዝብ እናሳውቃለን፤ ሂደቱ አርኪ ካልሆነ ጥቅምት 30 የተያዘው ሰላማዊ ሰልፍ በእቅዱ መሰረት ይካሄዳል ብለዋል፡፡
ባለፉት 10 ቀናት መግባባት ተደርሶባቸው ተግባራዊ ምላሽ እየተሰጠባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከልም በደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትና የምዕመናን ቤቶችን መልሶ የመገንባት ስራ መጀመሩ ለአብነት ተጠቅሷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተነጠቁ ይዞታዎችን የመመለስና የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ መስጠት መጀመሩም ታውቋል፡፡ ኮሚቴው ከባለስልጣናት ጋር ከመከረባቸው ጉዳዮች መካከል በጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ካህናትና ምዕመናን እንዲሁም ለተቃጠሉና ለተዘረፉ አብያተ ክርስቲያናት ካሳ እንዲከፈል የሚለው ዋነኛው ጥያቄ ሲሆን በሃይማኖታቸው ምክንያት ከቦታቸውና ከስራቸው የተፈናቀሉ ወደነበሩበት እንዲመለሱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱንና እምነቱን ለበቀላዊ ጥቃት እያነሳሱ ያሉ ሀሰተኛ ትርክቶች እንዲታረሙ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱና ምዕመኖቿ ላይ ጥፋት ያወጁና ያስተባበሩ ባለሥልጣናት፣ ግለሰቦችና ቡድኖች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲሁም ጥቃት እንዲቆም በመጠየቃቸው የታሰሩ ኦርቶዶክሳውያን በአፋጣኝ እንዲፈቱ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም የተነጠቁ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች እንዲመለሱ፣ ለአዲስ አብያተ ክርስቲያናት መትከያ፣ ለመካነ መቃብር፣ ለባህረ ጥምቀትና መስቀል ደመራ ማክበሪያ የሚውሉ ቦታዎች በሕግ እንዲሰጡም ተጠይቋል፡፡  በተለያዩ አህጉረ ስብከት የሚገኙና የተወረሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶችና ሕንጻዎች እንዲመለሱ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሰጥ እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያንን የእምነት ነጻነት የሚጋፉ ጫናዎች እንዲቆሙ የሚሉት ጥያቄዎቹ ቀርበዋል፡። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች መደረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን ሰልፈኞቹ ለጥያቄያችን ደጋፊ ናቸው  ሲሉ የኮሚቴው ሰብሳቢ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡    


Read 6966 times