Tuesday, 01 October 2019 09:54

ባለፈው ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች 1 ሺ 229 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  - 1400 የሚጠጉት የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
           - 1.2 ሚ. ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
          - ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት ወድሟል
                
           ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ 1 ሺ 229 ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ያስታወቀው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ 1 ሺ 393 ዜጎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ጠቁሟል፡፡
ከፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ 1.2 ሚሊዮን ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዜጎች ንብረትም ወድሟል፡፡
በዚህ ግጭት ሕይወታቸውን ካጡት ዜጎች መካከል ሰላማዊ ሰዎች እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል፡፡ ግጭቱን በማነሳሳትና በዜጎች ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ 1323 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱንና ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል 645 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ ተናግረዋል:: 667 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አለመዋላቸውንና አሁንም እየተፈለጉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራና በቤኒሻንጉል ክልሎች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የተቀሰቀሱ ግጭቶች ለዜጎች ሞትና ለንብረት ውድመት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በዚሁ ግጭት ሳቢያ ሕይወታቸውን ካጡ ለአካል ጉዳት ከተዳረጉና ከቀዬአቸው ከተፈናቀሉ ዜጎች በተጨማሪ በ19 ሰዎች ላይ የግድያ ሙከራ መፈፀሙን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

Read 812 times