Saturday, 16 June 2012 12:00

ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢያቋቁሙስ?

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

እንደ ማር ከሚጣፍጥ እንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የሞባይሌ ጩኸት ነበር፡፡ ጋዜጠኛው ወዳጄ ነበር የደወለው፡፡ በድምፅም በአካልም ከተገናኘን ብዙ ወራት አልፎናል፡፡ በደጉ ጊዜ (ከአንድ ዓመት በፊት ማለት ነው) ድራፍት እየጠጣን ኢህአዴግን የምናማበት ግሮሰሪ ከች በል አለኝ - በ20 ደቂቃ ውስጥ፡፡ በደጉ ጊዜ ያልኩት ጓደኛዬ የገዢው ፓርቲ አባል ከሆነ ወዲህ ጠባዩ ስለተለወጠብኝ ነው፡፡ (ጠባዩን የለወጠው ኢህአዴግ ነው አልወጣኝም!) አትታዘቡኝና ---- አንዳንዴ ዝም ብዬ ሳስበው ይሄ ወዳጄና የኢትዮáያ ፖለቲካ ይመሳሰሉብኛል (ልብ አድርጉ! የኢትዮáያ ፖለቲከኞች አላልኩም) ሁለቱም እንደ እስስት ይቀያየራሉ - ወዳጄና ፖለቲካችን! (“የኢትዮáያን ፖለቲካ ያመነ ጉም የዘገነ” የሚል ተረት መፈጠር አለበት) ወዳጄን እያማሁ እንዳይመስልብኝ አንዳንድ ማስረጃዎች ላቅርብ፡ (ለፍርድ ቤት የሚሆን መረጃ ግን የለኝም!) እናላችሁ --- ይሄ ወዳጄ ከ97 ዓ.ም በፊት የገው ፓርቲ ደጋፊ  ነበር - “አክራሪ” ሳይሆን ለዘብተኛ፡፡ በ97 ደግሞ የፖለቲካ ነፋሱን ተከትሎ የተቃዋሚዎች ደጋፊ ሆነ፡፡ (መብቱ ነው!) ግን ብዙም አልዘለቀበትም፡፡ አመራሮቹ እስር ቤት ሲገቡ “Non – poltical” ነኝ  የሚል ጨዋታ አመጣ፡፡ (ከፖለቲካ ወይም ከደሙ ንፁህ ነኝ ለማለት ፈልጎ ነው) በሁዋላ ላይ መንግስት  ለትምህርት ቻይና ልኮት ሲመለስ ካድሬ ሆኖ አረፈው - የአብዮታዊ ዲሞክራሲ፡፡ (ይሄም መብቱ ነው!) አያችሁ ወዳጆቼ ---- ይሄን ሁሉ የምነግራችሁ ለጠቅላላ እውቀት ነው እንጂ ለፍረጃ አይደለም፡፡

ወዳጄን ካወቅሁት ጀምሮ የእስስትነት ባህርዩን ያላየሁበት በአንድ ጉዳይ ብቻ ነው - በምን መሰላችሁ? ጠ/ሚኒስትሩን በተመለከተ ባለው አቋም፡፡ በቃ አንደኛ አድናቂያቸው ነው፡፡ የዘመኑ ወጣት የአውሮፓ ፕሪሚየር ሊግን ሲደግፍ እሱ ፕራይም ሚኒስትሩን ብቻ ነው የሚደግፈው፡፡  ይገርማችሁዋል ---- የቅንጅት ደጋፊም እያለ እኮ በሳቸው ጉዳይ ቀልድ አያውቅም ነበር፡፡ በቃ obsessed ሆኖዋል (ልክፍት በሉት!)

በጣም የሚገርመው ምን መሰላችሁ ---- የኢህአዴግ ሊ/መንበር እንደሆኑ እያወቀም “እሳቸው ሌላ ኢህአዴግ ሌላ” እያለ ይከራከርላቸዋል - ለፕራይም ሚኒስትሩ፡፡ ይሄ ወዳጄ የሚያደንቀው አክተር¤ ዘፋኝ¤ ደራሲ ወዘተ የለውም፡፡ የወዳጄ “ቴዲ አፍሮ” እሳቸው ናቸው - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ “ጥቁር ሰው” የሚል አልበም ባያወጡም እሱ ንግግራቸውን እንደዘፈን ይሰማዋል - እየደጋገመ፡፡ ባለፈው የትንሳኤ በዓል የአዳም ዘር ለሞባይል ሪንግ ቶን የቴዲ አፍሮን ዘፈን ሲጭን እሱ ሆዬ¤ የጠ/ሚኒስትሩን የፓርላማ ንግግር ቀንጭቦ ጫነላችሁ፡፡ (ይሄ ፍቅር ሳይሆን አባዜ ነው!)

የተከራያት አንዲት ክፍል ቤቱ በሳቸው ፎቶዎች ነው የተሞላችው -  በፖስተር¤’ በፍሬም¤’ በአልበም ወዘተ ጠ/ሚኒስትሩ ብቻ ናቸው፡፡ ከገርል ፍሬንዱ ጋር ተጣልቶ የተለያየው  በሳቸው ምክንያት ነው፡፡ “ኮንዶሚኒየም እንኩዋን የማያሰጥ አድናቂነት” እያለች ስታፌዝበት “እኔ የምወደውን ካልወደድሽልኝ ገደል ግቢ!” አላትና መንዱን ጨርቅ ያድርግልሽ የሚለውን መረቀላት  (ይሄው እስከዛሬ ድረስ ፍቅረኛ የለውም!)

ወዳጄ እስካሁን ተመኝቶ ያላገኘው ምን መሰላችሁ - የጠ/ሚኒስትሩን ፊርማ ነው’፡፡ አንዳንዴ ሳስበው የኢህአዴግ ካድሬ የሆነው ፓርቲውን ወዶት ሳይሆን በአቋራጭ ፊርማቸውን አገኛለሁ ብሎ ይመስለኛል፡፡ (ጠ/ሚኒስትሩ በተራቸው ፓርቲዬን ካልወደድክ ገደል ግባ ቢሉትስ? በቃ ሰው አይሆንም!)

ወደ ወዳጄ ቀጠሮ ጋ ስሄድ “ለምንድነው በሌሊት የፈለገኝ” እያልኩ የተለያዩ መላ ምቶችን ብመታም ቁርጥ ያለ ግምት ላይ መድረስ አቃተኝ፡፡ እንዴ --- ከቤቴ ስወጣ ገና አንድ ሰዓት አልሞላም እኮ ! በ5 ደቂቃ ውስጥ የሰፈሬን ኮብልስቶን መንገድ ላፍ አድርጌ አስፋልት ወጣሁ፡፡ ታክሲም ወዲያው ነው የቀናኝ፡፡ ገና እንደተሳፈርኩ ይዞኝ ከነፈ፡፡ ለትርፍ የሚሰራ ሳይሆን የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጥ ነበር  የመሰለኝ፡፡ ትንሽ እንደከነፈ የነጋ ሳይሆን የመሸ የመሰላት ሽቅርቅር ወጣት አስቆመችውና ተሳፈረች፡፡ መቼም መሃረብ የምታህለዋን ቀሚስ የለበሰችው ከፓንቱዋ ጋር ማች እንዲያደርግላት እንጂ ሌላ ጥቅሙ አልታየኝም፡፡ ከሸፈነው ገላ ይልቅ ያጋለጠው ይበዛል፡ ጫማዋ ደግሞ ትንሽዬ ፎቅ ላይ የወጣች አስመስሉዋታል፡ “ይቻላል?” ብላኝ መልሴን ሳትጠብቅ አጠገቤ ተቀመጠች፡፡ ወፍራ ይሁን  ነገር ፍለጋ --- ከፊል ዳሌዋ እኔ ላይ ተጫነ፡፡ አልፎ አልፎ የሽቶና የመጠጥ ድብልቅ ወደ አፍንጫዬ ይደርሰኝ ነበር፡፡

ረዳቱ ትንሽ ከጠራ በሁዋላ መኪናው ተንቀሳቀሰ፡ ወዲያው ግን የትራፊክ ፖሊስ ፊሽካ አስቆመው፡፡ “ምናባቱ ፈልጎ ነው?” አለ ረዳት፡፡ ጎረምሳው ሹፌር ምንም አልመለሰለትም፡፡  የትራፊክ ፖሊሱ የተለመደውን ሰላምታ ሰጠና¤ የተከለከለ ቦታ ላይ ሰው መጫኑን በመግለፅ በጠዋቱ ሊቀጣው ከኬፑ ውስጥ ደረሰኝ አወጣ፡፡ ሹፌሩም  ከሁዋላ ኪሱ ውስጥ ዋሌቱን  አወጣና ተሽቀዳድሞ አንዲት ቀይ ካርድ አሳየው - ለትራፊኩ፡፡ ተቀብሎ እንኳን ማየት አላስፈለገውም፡ “ቀድመህ አታሳየኝም---- ለምን ታለፋኛለህ?” አለውና ከመኪናዋ ገለል አለ፡፡ ሾፌሩ መኪናዋን እየረገጠ ሽምጥ ጋለበ - የባከኑ ሽርፍራፊ ደቂቃዎችን ለማካካስ በሚመስል ጥድፊያ፡፡

“ብራዘር እዚህ አገር ላይ የሚሰራውን ግፍ ታያለህ?” አለችኝ ከጎኔ የተቀመጠችው ሽቅርቅር ወጣት - በክርንዋ እየጎነተለችኝ፡፡ ያለችው ስላልገባኝ “የምን ግፍ?” ስል ጠየቅሁዋት፡፡

“እንዴ ---- የአባልነት ካርዱን ሲያሳየው እኮ ነው የለቀቀው! መቼ ነው ግን እዚህ አገር ህግ የሚከበረው? እኔና አንተን ቢሆን እኮ ---- 160 ብራችንን ይቆነድደን ነበር!”

ረዳቱ  ያለችውን ሰምቱዋል መሰለኝ ከላይ እስከ ታች በግልምጫ አነሳት፡፡

“እቺም ውሪ ራስዋ ---- አባል ሳትሆን አትቀርም” እየሳቀች ወደ ረዳቱ ጠቆመችኝ፡፡

“የማን --- የኢህአዴግ ?” ጠየቅሁዋት

“እንክት! የግንቦት 20 ጊዜ ስታዲየም አልገባህም? የ10 ዓመት ልጆች ሁሉ እኮ ነበሩ !”

ገብተሽ ነበር እንዴ ብዬ ልጠይቃት ሳመነታ እስዋ ተናገረች፡፡

“የዛሬን አያድርገውና እኔም ቀንደኛ የወጣቶች ሊግ አባል ነበርኩ” ፈፅሞ ያልጠበቅሁትን ነገር ነው የሰማሁት፡፡ (ማን ያውቃል! እንደጋዜጠኛው ወዳጄ የጠ/ሚኒስትሩ አድናቂ ልትሆን ትችላለች)

“አሁንስ ተውሽው ?” የእኔ ጥያቄ ነበር

“የዛሬ ሳምንት ከቃሊቲ ስፈታ ነው የአባልነት ካርዳቸውን ቀዳድጄ የጣልኩላቸው!” በንዴት ጦዛ ነበር  የምትናገረው፡፡

“ታስረሽ ነበር ማለት ነው? ምን አድርገሽ?”

“ ይገርምሃል --- ምንም  በማላውቀው ጉዳይ እኮ ነው”

“ቆይ  ለስንት ጊዜ ነው የታሰርሽው?”

“ግንቦት 21 ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ  ከተኛሁበት ወስደው 10 ቀን ካሰሩኝ በሁዋላ በዋስ ለቀቁኝ”

“ ለምን እንዳሰሩሽ አልነገሩሽም?”

“በማላውቀው ጉዳይ ነው ስልህ---- እነሱ የሚፈልጉት አብሮኝ ያደረውን ሰውዬ ነበር፡፡ እሱ ሲሸውዳቸው ጋማዬን አይሉኝ መሰለህ!”

“ሰውየውን ታውቂዋለሽ አይደል?”

“ዊች ዋን? ያሰረኝን?”

“አረ አብሮሽ ያደረውን?”

“እመብርሃንን! ያለዚያን ቀን አይቼውም አላውቅ---- በሁዋላማ ቆጨኝ”

“እንዴት?”

“በአንድ ምሽት ትውውቅ እኮ ዓለሜን ነው ያሳየኝ! የለቀቀብኝን ዶላር ተወው! በዚያ ላይ ያደርነው ባለአራት ኮከብ ሆቴል!”

“እሺ ሰውየው ለምንድነው የሚፈለገው አሉሽ?”

“ሽብርተኛ ነው አሉ!” አለችኝ - እንደቀላል ነገር

“ሽብርተኛ?”  በድንጋጤ የተናገረችውን ደገምኩት - እየተርበተበትኩ

“እኔን እኮ አይደለም ---- ሰውየውን ነው ያሉት!” አለችኝ - ልታረጋጋኝ እየሞከረች

እኔ ደሞ ፈርዶብኝ ሽብርተኛ የሚለውን ቃል ከሰማሁ እንደጉድ እሸበራለሁ፡፡ በተለይ በቅርቡ የወጣውን የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ስፈራው ለጉድ ነው፡፡ አሁን ግን ከህጉ በላይም እስዋን ነው የፈራሁት፡፡ “ወራጅ--- ወራጅ!” አልኩኝ መውረጃዬ ሳይደርስ

“ምነው ፈራኸኝ እንዴ?” አለችኝ - ዓይንዋን ዓይኔ ላይ እያንከባለለች

“የእኔ እመቤት ----- የፀረ ሽብር ህጉ ምን እንደሚል ታውቂያለሽ? እንኩዋን አንድ አልጋ ላይ አብሮ የተኛ---- በስልክ ፤ በኢሜይል፤በአካል  የተገናኘ --- ሻይ አብሮ የጠጣ -- የተጨባበጠ--- ረዳት ወራጅ--- ወራጅ ---” የጀመርኩትን ሳልጨርስ ጥያት ወረድኩ - ጣጣ ውስጥ ከምገባ ጥቂት በእግሬ ብሄድ ይሻላል ብዬ፡፡ በልቤ ግን ፀልዬላታለሁ - ፈጣሪ ከሽብር እንዲያወጣት፡፡

ወዳጄ የቀጠረኝ ግሮሰሪ ስገባ ኦና ነበር፡፡ ዓይናቸው ላይ ያልጨረሱት የተንጠለጠለ እንቅልፍ ያለባቸው የሚመስሉ የወንድ አስተናጋጆች ቤቱን ያፀዳዳሉ፡፡ ዋናውን ክፍል አልፌ ወደ ውስጥ ስዘልቅ ጋዜጠኛው ወዳጄ ጥጉን ይዞ  ጃምቦ ድራፍቱን  ይጨልጣል፡፡ የገረመኝ ደግሞ ለኔም አስቀድቶ መጠበቁ ነው፡፡

ገና ሳልቀመጥ አጠገቡ የነበረውን ጥቁር ቦርሳ ከፈተና አዲስ መፅሃፍ አውጥቶ ሰጠኝ፡፡ “ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢያቋቁሙስ?” ይላል - የመፅሃፉ ርዕስ፡፡

“ደራሲ- ቢንያም ኤ.”   (ይኸው ጋዜጠኛው ወዳጄ መሆኑ ነው፡፡) ብዙም አልገረመኝም - ወዳጄ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ መፅሃፍ በማዘጋጀቱ፡፡ እሱ ያልፃፈ ማን ሊፅፍ ይችላል፡፡ (አድናቂያቸው አይደለም  እንዴ?) መፅሃፉን ገልበጥ ገልበጥ አድርጌ ተመለከትኩኝና “ኮንግራ!” ብዬ እጄን ዘረጋሁለት - ለወዳጄ፡፡

ከመጨባበጣችን በፊት ግን የቢሮዬ በር ተንኳኳና ከእንቅልፌ አባነነኝ፡፡ ከምሳ በሁዋላ ናፕ ልውሰድ ብዬ ነበር በሬን ቆልፌ ሶፋው ላይ ጋደም ያልኩት፡፡

ይኸው ግማሽ ሰዓት ገደማ ተኛሁኝ ማለት ነው፡፡ ተነስቼ የቢሮዬን በር ከፈትኩት፡፡ በሩ ላይ የቆመውን ሰው ስመለከት ግራ ገባኝ፡፡ ጋዜጠኛው ወዳጄ ነው - አሁን በህልሜ ያየሁት፡፡ ግን የትኛው ነው ህልም ----- የትኛው ነው እውን? ተጨባበጥንና ወደ ውስጥ አስገባሁት፡፡ አሁንም ግን በህልም ይሁን በእውን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ይሄንን ፅሁፍ የፃፍኩላችሁ በህልሜ ነው በእውኔ? በነገራችሁ ላይ አንዳንድ የማትፈልጉት ነገር ከተከሰተ በሁዋላ እውንነቱን ወደ ህልም መለወጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ቢሰራ ምን ይመስላችሁዋል? አቤት! እኛ አገርማ በጣም ተፈላጊ ነው! ስንት ህልም እንዲሆን የምንፈልገው አሳፋሪ የእውን ታሪክ አለን መሰላችሁ! (በተለይ ፖለቲካችን!)

 

 

Read 4121 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:26