Tuesday, 24 September 2019 00:00

የአለማችን ስደተኞች ቁጥር 272 ሚሊዮን መድረሱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የአለማችን ስደተኞች ቁጥር ባለፉት አስር አመታት የ23 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአሁኑ ወቅት በመላው አለም የስደት ህይወትን በመግፋት ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 272 ሚሊዮን መድረሱንና ከአለማችን ህዝብ 3.5 በመቶው ስደተኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ተመድ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ ባለፉት አስር አመታት የስደተኞች ቁጥር በ51 ሚሊዮን የጨመረ ሲሆን በፈረንጆች አመት 2019 በአውሮፓ 82 ሚሊዮን፣ በሰሜን አሜሪካ 59 ሚሊዮን በሰሜን አሜሪካና ምዕራብ እስያ አገራት ደግሞ በተመሳሳይ 49 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የስደት ህይወትን በመግፋት ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ከአለማችን 272 ሚሊዮን ስደተኞች መካከል ግማሽ ያህሉ በአስር አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ክፍል ሪፖርት፣ 51 ሚሊዮን ስደተኞች የሚኖሩባት አሜሪካ ብዛት ያላቸው ስደተኞችን በማስተናገድ ቀዳሚነቱን እንደምትይዝ አመልክቷል፡፡
ጀርመንና ሳዑዲ አረቢያ እያንዳንዳቸው 13 ሚሊዮን ስደተኞችን በማስተናገድ የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ ሩስያ በ12 ሚሊዮን፣ እንግሊዝ በ10 ሚሊዮን እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በ9 ሚሊዮን ስደተኞች እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ብዙ ዜጎቿ የተሰደዱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ህንድ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ 18 ሚሊዮን ህንዳውያን አገራቸውን ጥለው በመሰደድ በሌሎች አገራት ኑሯቸውን እየገፉ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡
ሜክሲኮ በ12 ሚሊዮን፣ ቻይና በ11 ሚሊዮን፣ ሩስያ በ10 ሚሊዮን፣ ሶርያ በ8 ሚሊዮን ዜጎች ስደት ብዛት ያላቸው ዜጎች ወደሌሎች አገራት ተሰድደውባቸዋል ተብለው በሪፖርቱ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ የተቀመጡ አገራት ናቸው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከአለማችን የህዝብ ቁጥር እድገት ይልቅ የአለማችን ስደተኞች ቁጥር እድገት ብልጫ እንዳለው የገለጸው ሪፖርቱ፣ በአመቱ በስደት ላይ ከሚገኙት 272 ሚሊዮን ስደተኞች መካከል 48 በመቶው ሴቶች መሆናቸውንም አክሎ አስታውቋል፡

Read 4552 times