Monday, 23 September 2019 00:00

ኦክስፎርድ ለ4ኛ ጊዜ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ተብሏል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የአለማችንን ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መስፈርቶች በማወዳደር በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ታይምስ ሃየር ኢጁኬሽን የተባለው ተቋም ከሰሞኑም የ2020 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን ባለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት በ1ኛ ደረጃ ላይ የዘለቀው የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዘንድሮም ክብሩን አስጠብቋል፡፡
የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የአመቱ ምርጥ ሁለተኛ የአለማችን ዩኒቨርሲቲ ሲባል፣ አምና ሁለተኛ የነበረው የእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካምብሪጅ ዘንድሮ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል፡፡
በአመቱ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ ከአራተኛ እስከ ዘጠነኛ ያለውን ደረጃ የያዙት የአሜሪካዎቹ ስታንፎርድ፣ ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ ፕሪንስተን፣ ሃርቫርድ፣ የል እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፣ የእንግሊዙ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን በ10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በ13ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው የስዊዘርላንዱ ኢቲኢች ዙሪክ በስተቀር ከአንደኛ እስከ ሃያኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የእንግሊዝና የአሜሪካ መሆናቸውንም ተቋሙ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ከአንደኛ እስከ 200ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ከተካተቱት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ግማሽ ያህሉ የአውሮፓ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፣ አሜሪካ 60 ያህል ዩኒቨርሲቲዎችን ማካተት መቻሏ፣ የደቡብ አፍሪካዎቹ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውንና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዊትዋተርሳንድ እስከ 200 ባለው ደረጃ የተካተቱ ብቸኛ ሁለት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በዘንድሮው የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ በ92 የተለያዩ አገራት ውስጥ የሚገኙ 1ሺህ 400 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ተቋሙ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማወዳደርና ደረጃ ለመስጠት ከማስተማር፣ ከምርምርና ከእውቀት ሽግግር ጋር ተያያዥ የሆኑ 13 ያህል የብቃትና ጥራት መመዘኛ መስፈርቶችን መጠቀሙን አስታውቋል፡፡


Read 1350 times Last modified on Friday, 27 September 2019 11:54