Saturday, 21 September 2019 13:19

አሜሪካ በጓንታናሞ ቤይ ለቀሩት 40 እስረኞች በአመት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በብራዚል በየቀኑ ቢያንስ 180 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ይፈጸማሉ

              አሜሪካ በኩባ ባስገነባችው ግዙፉ የጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ውስጥ 40 እስረኞች ብቻ እንደሚገኙና አገሪቱ ጥበቃን ጨምሮ ለእነዚሁ እስረኞች በአመት ከ540 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ የመስከረም 11 የሽብር ጥቃትን ተከትሎ እጅግ አደገኛ ያለቻቸውን አሸባሪዎች ለማሰር ስትል ባቋቋመችው የጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ውስጥ ለሚገኙት 40 ያህል እስረኞች ጥበቃ፣ ህክምና፣ የህግ ባለሙያዎች ድጋፍ ወዘተ በ2018 ብቻ ለእያንዳንዳቸው 13 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ ማድረጓን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
የአሜሪካ መንግስት እጅግ የሰለጠኑ 1 ሺህ 800 የልዩ ሃይል ጥበቃ ወታደሮችን በማሰማራት 40ዎቹን እስረኞች ሌት ተቀን እንደሚያስጠብቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ለእነዚሁ ወታደሮች ቀለብና የተለያዩ ወጪዎች የሚወጣው ገንዘብም እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
እስከ 770 ያህል የሌሎች አገራት ዜጎች ታስረበውበት እንደነበር የሚነገርለት ጓንታናሞ ከ720 የሚበልጡት በቡሽና በኦባማ አስተዳደር ዘመን መተፋታቸውንና በአሁኑ ሰዓት 40 ወንድ እስረኞች ብቻ መቅረታቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በብራዚል በየቀኑ ቢያንስ 180 ያህል የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ የአገሪቱ መንግስት ከሰሞኑ ባወጣው የህዝቦች ደህንነት ብሔራዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በአገሪቱ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ ከ66 ሺህ በላይ የወሲባዊ ጥቃት ድርጊቶች መፈጸማቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው መካከል 54 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ13 አመት በታች የሆነ ስለመሆናቸውም አመልክቷል፡፡
በአመቱ መሰል ጥቃቶች ከተፈጸሙባቸው ብራዚላውያን መካከል 82 በመቶ ያህሉ ሴቶች እንደሆኑና ከእነዚህ መካከልም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ለፖሊስ ያመለከቱት 7.5 በመቶው ያህል እንደነበሩ ተነግሯል፡፡

Read 1756 times