Print this page
Saturday, 21 September 2019 13:07

“የማይሞተው ንጉሥ”

Written by  ጌጡ ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


                 “በኮንሶ ምድር ዛፎችን መቁረጥ ኃጢአት ነው”
            
            ጋሞሌ መንደር
የካቲት 8 ቀን 1996 ዓ.ም
ከቀትር በኋላ፤ 9 ሰዓት
“ናካይታ” (Nagayta) የኮንሶዎች የወል ሰላምታ ነው፡፡ ሰላም በላያችሁ ላይ ይፍሰስ የሚል ትርጓሜን ይዟል፡፡ “ናይካታ” ይሁን መልሳችሁ፡፡ በኮንሶ ማኅበረሰብ ከሥራ አልያም ከመንገድ የሚመጣን ሰው “አካዶ”፣ “አሻማ”፤ “እንኳን ደህና መጣህ” ይሉታል፡፡
እንኳን ደህና መጣችሁ!
አሁን በታላቁ የምሥራቅ አፍሪቃ ሸለቆ፤ በኢትዮጵያ ዋና ስምጥ ሸለቆ ደቡባዊ ዳርቻ፤ ኮንሶ ትገኛላችሁ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ነገሥታት የሕዝቡን ሐሳብ ለማወቅ “አዝማሪ ምን አለ?” ይሉ ነበር፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በኮንሶ ማኅበረሰብ “ቶያንፓያ ወይንም ኹማንባያ ምን አሉ?” ይባላል፡፡ ኹማንባያ በሀገር ሊመጣ ያለውን ክፉና በጐውን ቀድመው የሚያዩ፣ መጪውን ጊዜ የሚያመላክቱ፣ እንደ ነቢያት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡
ቶያንፓያ፤ ኹማንባያ “ጨረቃን አይተው፣ ከዋክብትን ፈትሸው ዘመኑ የደስታና የጥጋብ ወይንም የችግር (መከራ) መሆኑን ይተነብያሉ” ይላሉ፡፡ ኮከብ ቆጣሪዎች፤ ባልና ሚስት ከዋክብትን በመመልከት ዝናብ - ርሃብንና ጥጋብን ያመላክታሉ፡፡ የከዋክብት ስብስብን “ቡሳ” እንዲሁም ከዋክብት መስመር ሰርተው ሲነጉዱ “አራባ” በመመልከት መጪውን ጊዜ ይተነብያሉ፡፡ እነዚህ መጪውን አመልካቾች፣ የኮንሶ ቶያንፓያና ኹንባያ፣ በ1995 ዓ.ም የካላ ወልደዳዊት ካዮቴን ዜና እረፍት ሲሰሙ ምን ተንብየው ይሆን? ካላ ወልደ ዳዊት ካዮቴ፤ የኬርቲታ ጐሳ 19ኛው ባህላዊ መሪ ነበሩ፡፡ ለ13 ዓመታት የ “ኮንሶ ንጉሥ ነኝ” የሚል ድምፃቸውን እያሰሙ አርፈዋል፡፡
የኮንሶ ጐሳዎች ዘጠኝ ናቸው፡፡ ዘጠኙም ጎሳዎች የቤተሰብና የወል ስም አላቸው፡፡ ሳውዳታ (ቶላ ማቶ)፣ አርካማይታ (ቶላ ሃልቢያ)፣ እሻላይታ (ቶላ አፋርታ)፣ ቶክማሌታ (ቶላ አይሎ)፣ ትክሳይታ (ቶላ ኦርጌታ)፣ ማክሌታ (ቶላ ከርዲባ)፣ ፓሳንታ (ቶላ ሎኾፓ)፣ ኤላይታ (ቶላ ትጫኔ) እና ኬርቲታ (ቶላ ካላ) ይባላሉ፡፡ ዘጠኙም የጐሳ መሪዎች እኩል (ባህላዊና መንፈሳዊ የሥልጣን እርከን አላቸው፡፡ ካላው ሲሞት በትረ ሥልጣኑ ከአባት ወደ በኩር ልጅ ይተላለፋል፡፡
ሰኔ 1995 ዓ.ም ካላ ወልደዳዊት ካዮቴ በጨጓራ ሕመም ምክንያት በ60 ዓመታቸው አረፉ፡፡ ይህ ዜና እረፍት በኮንስኛ “ፖቆላ ኢ አርማይቶዴ” ይባላል፡፡ ትርጉሙም “ፖቃላው (ጌቶች) ጉንፋን ይዟቸዋል” ማለት ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ጌቶች ሞቱ ተብሎ አይነገርም፤ አይወራም፡፡ “ባህላዊ መሪያቸው” በልባቸው “የማይሞተው ንጉሥ” ነውና ዝንታለማዊ እንደሆነ ያስባሉ፡፡
የካላ ወልደዳዊት ካዮቴ አስከሬን ለዘጠኝ ወራት፣ ዘጠኝ ቀናትና ዘጠኝ ሰዓታት፣ ማርና ቅቤ እየተቀባ ተቀመጠ፡፡ ዘጠኝ (ወራት፣ ቀናትና ሰዓታት) በኮንሶ የሚኖሩትን ዘጠኝ ጐሳዎች ለማመላከት ነው፡ የካላው ሚስት ቢሞቱ ግን ለስድስት ወራት፣ ስድስት ቀናትና ስድስት ሰዓታት አስከሬናቸው በክብር ቆይቶ ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል፡፡
ግብጻዊያን ለአስከሬን ማድረቂያ መሚ እንደሚጠቀሙ ሁሉ፤ ኮንሶዎችም ከተለያዩ ቅጠላ ቅጠልና የዛፍ ቅርፊቶች አስከሬን ማድረቂያ ይቀምማሉ፡፡ የካሳ ወልደዳዊት የሆድ ዕቃ ፈሳሽ (አንጀት፣ ሳንባ፣ ኩላሊት፣ ጉበትና ልብ) በማውጣት አስከሬኑ ሳይፈርስ፤ አስከሬን የማድረቅ ሥራ አከናውነዋል፡፡ የሟቹ የጐሳ መሪ ሆድ ዕቃ ወጥቶ በእንስራ ተቀምጧል፡፡ ዓይናቸውም ወጥቶ የሰጐን እንቁላል በዓይን ቅርጽ ተቀርጾ ተገጥሞላቸዋል:: የአስከሬኑ የደረቀው ሰውነት ጥቁር ጣል ጣል ያለበት ደማቅ ቀይ አቡጀዲ ለብሶ ወንበር ላይ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ አስከሬኑን ለመጎብኘት ተጠጋን፡፡ ከአስከሬን ጠባቂዎቹ አንዱ ‹‹ጌቶች በጣም ስለታመሙ መናገር አይችሉም፡፡ ስለዚህ  የክብር ሰላምታ ብቻ አቅርባችሁ ውጡ›› አለን፡፡ አስክሬኑ የተቀመጠበት ክፍል ውስጥ ገባን፡፡ እንደታዘዝነው እጅ ነስተን ወጣን፡፡
የካላ ወልደዳዊት አስከሬን ጠባቂዎች ለዘጠኝ ወራት በክብር ዘብ ቆመዋል። በዚህ የጥበቃ ጊዜ የሚፈልጉትን እህል ውሃ ለማግኘት ‹‹ካላ እንዲህ ያለ ምግብና መጠጥ አሰኝቷቸዋል›› ብለው ያዛሉ። በዚህ ትዕዛዝ፤ አስከሬን ጠባቂዎቹ ከጥሬ እስከ ብስል፣ ከጨቃ እስከ ደረቅ የማር ጠጅ ለዘጠኝ ወራት አጣጥመዋል፡፡ አስከሬን ጠባቂዎቹ ትዕዛዝ በሟቹ ቤተሰብ ሳይጓደል ተፈጽሟል፡፡ የአስከሬን ጠባቂዎቹ ትዕዛዝ ከዘጠኝ ወራት፣ ዘጠኝ ቀናትና ዘጠኝ ሰዓታት በኋላ አብቅቷል፡፡
በጋሞሌ መንደር ‹‹ማንታ›› በሚባል ሞራ፤ የሕዝብ አደባባይ ሦስቴ ከበሮ ተመታ፡፡ በተለምዶ ‹‹ጥሩንባ ነፊ›› የምንለው ሰው (መልዕክተኛ) በኮንሶኛ ቋንቋ ‹‹አራፓታ›› ይባላል፡፡ አራፓታው ‹‹ፓቆላ - ጌቶች - አረፉ›› እያለ ድምፁን አሰማ፡፡ መንደርተኞቹ ተሰባሰቡ፡፡ ይሁንና ለቅሶና ዋይታ አልተደመጠም:: የጠመንጃዎች አፈሙዞች ወደ ሰማይ ተወደሩ፡፡ ጥይት ተንጣጣ፣ የህብረት ዝላይና ጭፈራ ‹‹ማና›› ትዕይንት ተጀመረ፡፡
የካላው፤ የፖቆላ ቤተሰብ ንብረት በሆኑ ቲንባዎች (ከበሮዎች) ተደለቁ፡፡ ከበሮ መቺዎቹ ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተመላለሱ ሟቹን ካላ ወልደዳዊትን ጀግንነታቸውን እያነሱ መዘከር ያዙ:: አስከሬኑ በእርጥብ የላም ቆዳ ተጠቀለለ፡፡ ለሟቹ ክብር ለመስጠትም ደማቅ ቀይና ጥቁር ጨርቅ ለበሰ፡። በአስከሬኑ ግንባር የነበረው የመሪዎች ምልክት ‹‹ኻላሻ›› አልወለቀም፡፡ አስከሬኑ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ ነው፡፡ ሐዘንተኞቹ አስከሬኑን የያዘውን ወንበር በትከሻቸው ተሸክመው ለቀብር ጉዞ ጀመሩ:: በጉዞ ላይ አስከሬኑን በርቀት ለተመለከተው በሕይወት ያለ ሰው ወደ መቃብር የሚጓዝ ይመስላል። በእርሳቸው አምሳያ ከጥድ እንጨት የተቀረፀው የጀግንነት ሐውልት ‹‹ዋካ›› አስከሬኑን እየተከተለ ነው፡፡ የመቀበሪያው ጉድጓድ አስከሬን እንደተቀመጠ እንዲቀበል ተደርጎ ተቆፍሯል፡፡ አስከሬኑ ከነወንበሩ ጉድጓድ ውስጥ በክብር አረፈ፡፡ የካላ ወልደዳዊት ካዮቴ ጉይታ (ጉዩ) ሥርዓተ ቀብር ከዘጠኝ ወራት፣ ዘጠኝ ቀናትና ዘጠኝ ሰዓታት በኋላ የካቲት 8 ቀን 1996 ዓ.ም ተፈጸመ፡፡
‹‹የጌቶች›› አስከሬን የመቃብር ጉድጓድ ውስጥ ገባ፡፡ በእንስራ ተቀምጦ የነበረው የሆድ ዕቃ እንጥፍጣፊም ተቀበረ፡፡ ከመቃብራቸው አናት የጀግንነት ሐውልት (ዋካ) ቆመላቸው፡፡ ይህ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደ ዘይሴ ማኅበረሰብ አስደምሞኛል:: የዘይሴ ማኅበረሰብ ባህላዊና መንፈሳዊ መሪ ሲሞት አስከሬኑ መቃብር ጉድጓድ ውስጥ ከገባ በኋላ የሚሞላው አፈር ሳይሆን ጥሬ እህል ነው፡፡
በካላ ወልደዳዊት ካዮቴ ሥርዓተ ቀብር የበኩር ልጃቸው አልተገኙም፡፡ ‹‹አቶ ገዛኻኝ ወልደዳዊት ለምን አባታቸውን አልቀበሩም?›› ስል ራሴን ጠየቅኩት፡፡ መልስ አጣሁለት፡፡ መልስ ፍለጋ አቶ ገዛኸኝ፣ ‹‹አልጋ ወራሹ››ን መፈለግ ጀመርኩ፡፡
ጋሞሌ አምባ ከዋርካው ሥር ነጠላ ጋርደው በተጠንቀቅ የቆሙ ሰዎችን ተመለከትኩ፡፡ ወደ እነርሱ ተጠጋሁ፡። ‹‹እነማን ናቸው?... ማንን እየጠበቁ ነው?›› እያልጎመጎምኩ ሳለሁ፣ ነፋስ ነጠላውን ገለበው፡፡ አቶ ገዛኸኝ ወልደዳዊት ተቀምጠው ተመለከትኩ፡፡ አልጋ ወራሹ ከተቀመጡበት ተነሱ:: የአልጋ ወራሹ ጠባቂዎች ስለት (ጋሻ፣ ጎራዴ፣ ጦር፣ የአውራሪስ ቀንድ) ይዘዋል፡፡ አልጋ ወራሹ፣ ልጃቸው አቶ ገዛኸኝ ወልደዳዊት ሲንጎማለሉ፣ ጠባቂዎቻቸው የሙት መንፈሱ እንዳይወድቅባቸው በተጠንቀቅ እየጠበቋቸው ነበር፡፡
አቶ ገዛኸኝ አባታቸውን ያልቀበሩበት ምክንያት የአባታቸው የሙት መንፈስ እንዳያገኛቸው፤ እንዳያርፍባቸው ነበር፡፡ የካላ ወልደዳዊት ካዮቴ የእጅ አምባር ‹‹ቱማ›› አልባሳታቸውና የመመገቢያ ዕቃዎቻቸው ተሰበሰቡ፡፡ ያልተኮላሸ ጠቦት ታረደና በበጉ ‹‹ፈርስ›› የማጽዳት ሥራ መከናወን ጀመረ፡፡
የአራት ልጆች አባት የሆኑት ገዛኸኝ ወልደዳዊት ካዮቴ፤ ‹‹ሙልቃ›› (የብረት አምባር) በእጃቸው በማሰር ሃያኛው የኬርቲታ ጎሳ ባህላዊና መንፈሳዊ መሪ ሆኑ፡፡ የአባትና የልጅ፣ የካላው ቀብርና የልጃቸው ሥልጣን ርክክብ ሥነ ሥርዓት መሳ ለመሳ ተካሂዶ አበቃ፡፡ የዚያኑ ቀን ባህላዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ካላ ገዛኸኝ ማደሪያቸውን ከቤተሰባቸው ነጠሉ፤ ከልጆቻቸው ጋር ማዕድ መቅረብ አቆሙ:: ከእንግዲህ ከራሳቸው የእርሻ መሬት ከተዘራ፣ ከተፈጨ በቀር ከቤተሰባቸው ጋር መመገብ አይፈቀድላቸውም፡፡ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከገበያ የሚመጣ እህል ውሃን መቅመስ አይችሉም፡፡ ባህላዊ ሥርዓቱ አይፈቅድላቸውም። ይህ ከካላ ቤተሰብ ተያይዞ የመጣ ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡  
የጎሳ መሪዎች ከፍተኛ ሥልጣንና ሀብት ያላቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ መሪዎች ዋና ሥራ ሸንጎ ይዞ መዳኘት ነው፡፡ የጎሳ መሪዎች እንደተራው ሕዝብ ቀፎ አይሰቅሉም፤ እርሻም አያርሱም፡፡ ይሁንና ሰፊ መሬት ስለሚኖራቸው ወዶ አራሹን በማሳረስ ይተዳደራሉ፡፡ አንድ የኮንሶ የጎሳ መሪ ከቤቱ ወጥቶ የትም ሄዶ አይበላም፣ አይጠጣም፡፡ ይህንን ሥርዓት ካላው ባይፈጽም የካላው የሥልጣን ኃይል ይረክሳል ተብሎ ይታመናል፡፡ በጋሞሌ መንደር የጎሳ መሪዎች ከሚያስተዳድሯቸው ጫካዎች መካከል ሙራ ካላ ይጠቀሳል፡፡ ካላ ወልደዳዊት የኖሩትም፤ የተቀበሩትም በሙራ ካላ ጫካ ውስጥ ነው፡፡
ከጋሞሌ አምባ መንደር አዛውንቶች ጋር ወግ ይዣለሁ፡፡ ‹‹ሙራ ካላ ጫካ 19 የጎሳ መሪዎች ተቀብረዋል፡፡ የቀድሞዎቹ ካላዎች አስከሬን ለ9፣18፣27 እና 36 ዓመታት ቆይቷል›› ይላሉ፡፡ የአስከሬኑ የቆይታ ዘመን የሚወሰነው የሀገሩ ሰላምና ደህንነት ተጠንቶ፣ የጎተራው የእህል መጠን ግምት ውስጥ ከገባ በኋላ ነው፡፡
በሙራ ካላ ጫካ ‹‹ኦላሂታ››፤ የትውልድ የሥልጣን ዓርማ ለማዘጋጀት ካልሆነ በቀር ዛፍ አይቆረጥም:: በኮንሶ ምድር ዛፎችን መቁረጥ ኃጢአት ነው፡፡ ከሀገር ሽማግሌዎች ፈቃድ በስተቀር ከቅዱስ ጫካ ዛፍ የሚቆርጥ ሰው ያብዳል ወይንም ይሞታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ የመጥረቢያ ድምጽ ከተሰማ የኮንሶ ማኅበረሰብ አባላት የዛፉን ሕይወት ለመታደግ ይሯሯጣሉ፡፡
‹‹ዛፍ ሕይወት ነው!›› የሚለው መርህ በተግባር የተረጋገጠው ከኮንስዎችና ከጌዲኦዎች ምድር ነው:: በጌዲኦ ባህል መሰረት ባልና ሚስት ብቻቸውን ፍቺ ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ከጌዲኦ ተፈጥሮአዊ ደን ውስጥ ያለፈቃድ ባልም ሆነ ሚስት ዛፍ የቆረጠ፤ የቆረጠች እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ሽማግሌ ወይም ዘመድ አዝማድ ጣልቃ ሳይገባ እንዲሁም ፍርድ ቤት፣ ችሎት ፊት ሳይቀርቡ ፍቺ ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡
በኮንሶ ምድር ከአግራሞት ታሪኮች ውስጥ ከካላ ወልደዳዊት ካዮቴ ቀብር በኋላ ‹‹አራፓታ›› (ጡርንባ ነፊው) የቀንድ ጡሩንባውን ይዞ በጋሞሌ መንደር አልታየም፡፡ ምክንያቱም በመንደሩ ተገኝቶ እህል ውሃ ቢቀምስ ‹‹ሞቱ ይፈጥናል›› ይባላል፡፡ እናም አራፓታ ሞቱን ለማዘግየት ከመንደሩ ሸሽቷል፡፡ የት እንዳለ አይታወቅም፡፡ 

Read 1572 times