Saturday, 21 September 2019 12:52

ግብጽ በህዳሴው ግድብ ጉዳይ የሱዳንን ድጋፍ ጠየቀች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 - ኢትዮጵያ ከግድቡ በየአመቱ 40 ቢ. ኪዩቢክ ውሃ እንድትለቅ ግብጽ ጠይቃለች
             - ኢትዮጵያ የግብጽ ሃሳብ ‹‹ሉአላዊነቴን የሚዳፈር ነው›› ስትል ውድቅ አድርጋዋለች


            የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲና የሱዳኑ ጠ/ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በካይሮ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ መምከራቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ በህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ላይ ግብጽ የያዘችውን አቋም የሱዳን መንግስት እንዲደግፍ የግብፁ ፕሬዚዳንት ማግባባታቸውን ጠቁሟል፡፡ የሱዳን አዲሱ መንግስት በበኩሉ የተለየ አዲስ አቋም አለመያዙ ታውቋል፡፡
የግብጽ መንግስት ከአዲሱ የሱዳን የሽግግር መንግስት ጋር ጠንካራ ወዳጅነት የመፍጠር ፍላጐት እንዳለው አልሲሲ ማስታወቃቸውና ሀገራቸው የአሜሪካ መንግስት ሱዳንን ለአሸባሪዎች ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ እንድታወጣ መጠየቋን አስረድተዋል ተብሏል፡፡
ባለፈው እሁድና ሰኞ በካይሮ በግድቡ ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ለመደራደር የተገናኙት የግብጽ፣ ሱዳንና የኢትዮጵያ ተወካዮች፣ ግብጽ ባቀረበችው አዲስ የውሣኔ ሃሳብ ምክንያት መሰናከሉ የተገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያም አዲሱን የግብጽ ሃሳብ ‹‹ሉአላዊነቴን የሚዳፈር ነው›› ስትል ውድቅ አድርጋዋለች፡፡
ግብጽ በዋናነት ሶስት ጉዳዮችን ለውይይቱ ያቀረበች ሲሆን፤ የግድቡ የውሃ አሞላል በ7 አመት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ኢትዮጵያ በየአመቱ ከግድቡ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድትለቅ የሚያስገድድ መሆኑ ታውቋል፡፡
‹‹በየአመቱ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ ለግብጽ ይለቀቅ የሚለው የሀገርን ሉአላዊነት በእጅጉ የሚዳፈር ነው›› ያሉት የውሃ መስኖ እና ኢነርጀር ሚኒስትሩ ኢ/ር ስለሺ በቀለ፤ ‹‹በግብጽ በኩል የቀረበው ሃሳብ ግድቡ ላይ የኢትዮጵያ ጥቅምና የመወሰን መብቷ በግብጽ ይሁንታ እንዲመሠረት የሚያደርግ አደገኛ የድርድር ሃሳብ ነው›› ብለዋል:: ሃሳቡም መቼውንም ቢሆን በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አይኖረውም” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ አሞላል ሂደት በ3 ዓመት የመጨረስ ሃሳብ እንዳላት የተገለፀ ሲሆን፤ ይህን ሃሳብ በጫና ለማስቀየር ግብጽ አለማቀፍ ማህበረሰብ ጫና እንዲፈጥር የማግባባት ስራ እየሰራች መሆኑን ‹‹ኢጅንት ቱዴይ›› የተሰኘው የድረ ገጽ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ በሶስተኛነት ግብጽ ያቀረበችው በግድቡ ግንባታ ላይ ግብፃውያን ባለሙያዎች እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ሃሳብ መሆኑም ታውቋል፡፡
ሶስቱ ሀገራትም ያቋረጡትን ድርድር ከመስከረም 19 እስከ መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡ የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ አንዳንድ የውጭ ሀገር ሚዲያዎች የሚያቀርቡት ዘገባ በተዛባ መረጃ የታጀበ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር በቀለ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሚዲያዎቹን በማስተባበር ግድቡን ቦታው ድረስ ተገኝተው እንዲመለከቱ የሚያስችል መርሃ ግብር እያመቻቸ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Read 11239 times