Saturday, 21 September 2019 12:48

መንግስት ዘንድሮ ስድስት የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል ያዘዋውራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ስኳር ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 13 የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክት ውስጥ ስድስቱን ወደ ግል ለማዘዋወር የዋጋ ግመታና ተያያዥ ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በስሩ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ለመሸጥ ያወጣው የአክሲዮን ሽያጭ ማስታወቂያ እንደሌለ ለማስገንዘብ በላከው መግለጫው፤ በ2012 ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር የታቀዱ ስድስት የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ አለማቀፍ እውቅና ያለው የውጭ አማካሪ ኩባንያ ቀጥሮ እያስጠና መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
ከጥናቱ ጐን ለጐን መንግስት ከባለሀብቶችና ኩባንያዎች ጋር የሚያደርገውን ድርድር እንዳጠናቀቀ ወደ ግል ይዞታ የሚዘዋወሩ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የትኞቹ እንደሆኑ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ኮርፖሬሽኑ በመግለጫው ስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የወንጂ ሸዋና የመተሃራ ስኳር ፋብሪካዎችንም ሆነ ሌሎቹን ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ከየትኛውም ባለሀብት፣ ኩባንያ ወይም ማህበር ጋር የተደረገ ይፋዊ ድርድርም ሆነ ስምምነት አለመኖሩንም ኮርፖሬሽኑ አስገንዝቧል፡፡
መንግስት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችንና ፋብሪካዎችን በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር ያሳለፈውን ውሣኔ ተከትሎ፣ ለባለሃብቶችና ኩባንያዎች በቀረበው የመረጃ ጥያቄ መሠረት፣ በርካቶች በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጐት ማሳየታቸውን የኮርፖሬሽኑ መግለጫ አመልክቷል፡፡

Read 9461 times