Print this page
Saturday, 21 September 2019 12:46

‹‹ንስር›› ለሥራ ፈጣሪዎች በ5 አመት ውስጥ 450 ሚ. ብር ማበደሩን ገለጸ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የተመሰረተበትን 5ኛ አመት ዛሬ የሚያከብረው ንስር ማይክሮ ፋይናንስ አ/ማ፣ ባለፉት አምስት አመታት ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ለስራ ፈጣሪዎች ማበደሩን አስታወቀ፡፡
በወጣት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተመሰረተው ተቋሙ፤ በባንኮችም ሆነ በሌሎች የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የማይሸፈኑ የብድር አገልግሎቶችን ለሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱንና በዚህም ውጤታማ ተግባር ማከናወኑን ገልጿል፡፡
ልዩ አነስተኛ የብድር ፍላጎት ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚያደርገው ‹‹ንስር››፤ ተማሪዎችን ማዕከል ያደረገና ዝቅተኛ የወለድ መጠን ያለው የላፕቶፕ መግዣ ብድር ሲሰጥ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡
ተቋሙ ብድር ለሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄውን ባቀረቡ ከ3 እስከ 5 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ የሚሰጥ ሲሆን እስካሁን ካበደረው ገንዘብ 95 በመቶ የሚሆነውን ተበዳሪዎች ‹‹አትርፈንበታል›› ብለው መመለሳቸውን አስታውቋል፡፡
በ215 ባለአክሲዮን ወጣቶች በሁለተኛ የተቋቋመው ንስር ማክሮፋይናንስ፤ ወደ 1 ሺህ 8 መቶ ያህል የሚጠጉ ተበዳሪዎች እንዲሁም 3 ሺህ 2 መቶ ቆጣቢዎች በድምሩ 5 ሺህ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ለቆጣቢዎች በአመት እስከ 12 በመቶ ወለድ እንደሚከፍል ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተቋሙ ስራ በጀመረ አመቱ ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩን፣ በአሁኑ ወቅት 70 ሰራተኞች እንዳሉትና በቅርቡ 6ኛ ቅርንጫፉን ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በቀጣይም የሞባይል ባንኪንግ፣ ኤቲኤም ካርድ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግና ሌሎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተደገፉ አገልግሎቶችን ለመስጠት እቅድ መያዙም ተገልጿል፡፡

Read 3949 times
Administrator

Latest from Administrator