Saturday, 21 September 2019 12:37

3ኛው ጣና ሶሻል ሚዲያ አዋርድ ጥቅምት 1 ቀን በባህር ዳር ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ መምህር ታዬ ቦጋለና
                     ገጣሚ ዕውቀቱ ሥዩም ታጭተዋል


           በዘመራ መልቲ ሚዲያ በየአመቱ የሚዘጋጀውና ማህበራዊ ሚዲያን ለበጐ ተግባር፣ ለአንድነት፣ ሰላምን ለመስበክ፣ ጠቃሚና እውነተኛ መረጃዎችን ለማስተላለፍ የሚጠቀሙ ግለሰቦችንና ተቋማትን አወዳድሮ የሚሸልመው “ጣና ሶሻል ሚዲያ አዋርድ” ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ በብሉ ናይል ሪዞርት ሆቴል ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ “ማህበራዊ ሚዲያን ለበጐ ተግባር፣ ለአዕምሮ ሰላምና ለኢትዮጵያዊነት” በሚል መሪ ቃል ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይሄው የሽልማት ስነ ሥርዓት፤ በአማራ ቴሌቪዥን በቀጥታ ሥርጭት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና በውጪው ዓለም ለሚገኘው ማህበረሰብ እንደሚተላለፍ አዘጋጁ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ፤ በፑሊፕ ኢን ሆቴል በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ሽልማት የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በ16 ዘርፎች ሲሸለሙ መቆየታቸውን ያስታወሱት አዘጋጆቹ፤ በዚህ ዓመት 5 ዘርፎች ተጨምረው በ21 ዘርፍ ሽልማቱ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ በዘንድሮው ሽልማት 290 ግለሰቦችና ተቋማት ተጠቁመው፣ 68ቱ ለመጨረሻው ዙር ያለፉ ሲሆን የመጨረሻዎቹ አሸናፊዎች ከባህርዳር ዩኒቨርስቲና ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ነፃ የትምህርት እድል እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡
በዘንድሮው ሽልማት በስነ ጽሑፍ ዘርፍ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና በዕውቀቱ ሥዩም ዕጩ ሲሆኑ፤ በታሪክ ዘርፍ አነጋጋሪው የታሪክ ምሁር ታዬ ቦጋለና ወጣቱ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አንበርብር ታጭተዋል፡፡ አሸናፊዎቹን ለመለየት ከተለያዩ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በዳኝነት የተመረጡ ሲሆን፣ 70 በመቶው በዳኞች፣ 30 በመቶው ደግሞ ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚገኝ መረጃ እንደሚወሰን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡


Read 8186 times