Saturday, 21 September 2019 12:18

በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

 • የኳታር መሰናዶ 5 ዓመታትን ፈጅቷል፡፡ ከ30ሺ በላይ እንግዶች ከዓለም ዙርያ ትቀበላለች፡፡
     • የሰዓታት ለውጥ በውድድሮች ላይ ይኖራል፤ በተለይ ማራቶን በሌሊት መካሄዱ ይጠቀሳል
     • ለኢትዮጵያ ግምት የተሰጠው በ10ሺ፤ በ5ሺ ሜትር፤ በማራቶን እንዲሁም በ3ሺ ሜትር መሰናክል ነው፡፡
     • በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ለኢትዮጵያ ከ10 ወራት በፊት በቀረበው ትንበያ በአጠቃላይ ሁለት የወርቅ፤ ሁለት የብርና 4 የነሃስ ሜዳልያዎች
     • ባለፉት 16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 77 ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ 27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ           ሜዳልያዎች ናቸው፡፡


            በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ላይ ለሚካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮንሺፕ 10 ቀናት ቀርተዋል፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህበር አባል ከሆኑት 213 አገራት መካከል 208 በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው መወዳደራቸው የሚጠበቅ ሲሆን ከ3500 በላይ አትሌቶች፤ አሰልጣኞች፤ ማነጀሮች እና ሌሎች ባለሙያዎች የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ትልቁን ውድድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ በምትገኘው ኳታር መዘጋጀቱ የአረቡን ዓለም ከፍተኛ ጉጉት ውስጥ ከቶታል፡፡ ከአምስት ወራት ቀደም ብሎ በዶሃ ከተማ ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ከ1983 እስከ 2019 እኤአ በ35 ዓመታት ያለፈባቸውን የታሪክ ሂደቶች የሚያሳይ ኤግዚብሽን መካሄዱም በቂ ትኩረት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡   የኳታር መንግስት እና ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በሻምፒዮናው ላይ ከመላው ዓለም 10000 ያህል ልዩ እንግዶችን ዶሃ እንደምታስተናግድ ጠብቀዋል፤ በ10 ቀናት ውስጥም የዓለም ሻምፒዮናው በስታድዬም እና ከስታድዬም ውጭ ከ30000 በላይ ታዳሚዎች እንደሚኖሩት ተገምቷል:: የዓለም ሻምፒዮናው በመላው ዓለም የሚካሄዱት የተለያዩ ውድድሮች ተጠናቅቀው በውድድር  ዘመኑ የማረፊያ እና የማገገሚያ ወራት መስከረምና ጥቅምት ላይ መደረጉ በርካታ የአትሌቲክስ ኤክስፐርቶችን አላስደሰተም፡፡ ባለፉት 16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዱ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍ 7.5 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ ያዘጋጀ ሲሆን በቲዲኬ TDK እና በኳታር ብሄራዊ ባንክ Qatar National Bank ልዩ ድጋፍ ደግሞ በሻምፒዮናው ለሚመዘገብ የዓለም ሪከርድ የ100ሺ ዶላር ቦነስ ተዘጋጅቷል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የስፖርት ዓለም የፈጠረችው ኳታርና መሰናዶዎቿ
በመካከለኛው ምስራቅ የዓለምን ታላላቅ የስፖርት መድረኮች ለማስተናገድ በቂ መሰረተልማቶችና የበጀት አቅም በመያዝ የስፖርት ዓለም የመሰረተችው ኳታር   በሚቀጥሉት 6 ወራት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን ጨምሮ 20 ትልልቅ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ታስተናግዳለች:: በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች የተሳካ መስተንግዶም በአካባቢው የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ተደማጭነቷን የሚጨምረው ሲሆን በቱሪስት ፍሰት እና በቱሪዝም መዳረሻነት በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርጋትና በዓለም ማህበረሰብ የሚያስመሰግናት ይሆናል፡፡ በ2022 እኤአ እስከምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ድረስ በስፖርት መሰረተልማቶች ግንባታ እና ሌሎች ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች እስከ 25 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ያደረገችው ኳታር ይህን ጉዟዋን የምትጀምረው በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ነው፡፡ 17ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም በዋና ከተማዋ ዶሃ በሚገኘው ዘመናዊው  የካሊፋ ኢንተርናሽናል ስታድዬም ይካሄዳል፡፡ 40000ሺ  ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው ይህ ሁለገብ ስታድዬም ለዓለም ሻምፒዮናው ለማዘጋጀት የ3 ዓመት ልዩ እድሳት እና ግንባታ የተካሄደ ሲሆን በተጨማሪ በዙርያው የተገነባው ልዩ ዓለም አትሌቲክስ መንደር ሻምፒዮናውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ምቹ ይሆናል ተብሏል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በካሊፋ  ኢንተርናሽናል ስታድዬም በተከታታይ ለ10 ቀናት ሲካሄድ 22 የዓለም ሻምፒዮኖች በሚታወቁባቸው ውድድሮች በርካታ አዳዲስ ነገሮችም ይኖራሉ፡፡ የመጀመርያው ውድድሮች በተስማሚ የአየር ሁኔታ ለማካሄድ በስታድዬም ዙርያ ገብ የሚገጠሙት  የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂዎች ናቸው:: ይህ ቴክኖሎጂ በሻምፒዮናው ስታድዬም ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮች በአማካይ 26 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ይሆናል፡፡ የማራቶን ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች በእኩለ ሌሊት መካሄዳቸውም በታሪክ የመጀመርያው ሲሆን፤ ልዩና አዲስ ድምቀት እንደሚፈጥር ተጠብቋል፡፡
ኳታር በ2010 እኤአ ላይ 22ኛውን የዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ከተመረጠች በኋላ ባለፉት 9 ዓመታት የዓለም ታላላቅ ስፖርት መድረኮች የማስተናገድ ብቃት እና የአየር ሁኔታ የላትም በሚል ውጥረት ውስጥ ቆይታለች፡፡ ለዓለም ዋንጫው አዘጋጅነት ስትመረጥ የፊፋን አሰራር በማበላሸት በጉቦ ልዩ እድል ማግኘቷን፤ የስፖርት መሰረተልማቶቿን የሚገነቡ ስደተኞችን ጉልበት መበዝበዟንና ሰብዓዊ ጉዳቶች ማድረሷን፤ የዓለም ዋንጫን የማስተናገድ ተገቢነት የላትም በሚሉት ትችቶች ስትብጠለጠል ነው የቆየችው፡፡ በሌላ በኩል በ2014 እኤአ 17ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድታስተናግድ በአይኤኤኤፍ ስትመረጥም ትችቶቹ አልተቋረጡም፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበርን በልዩ የገንዘብ ድጋፍ መደለሏን የሚጠቅሱ ዘገባዎች ነበሩ፡፡ ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ከ30 ሚሊዮን ዩሮ በላይ መለገሷን እንደመረጃ በማንሳት ነው፡፡ የኳታር ዋና ከተማ ዶሐ የዓለም ሻምፒዮናውን አዘጋጅነት ለማግኘት የበቃችው የስፔኗን ባርሴሎና እንዲሁም የአሜሪካዎቹን ዩጂንና ኦሬጎን ከተሞች በመብለጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ኳታር የዓለም ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ ውድድሩ አንድ ሰሞን እስኪቀረው ተፍ ተፍ ብላለች፡፡ በሻምፒዮናው በሚካሄዱ 49 የፍፃሜ ውድድሮች ላይ ለመሸለም ያዘጋጀቻቸውን የሽልማት ሜዳልያዎች ያስታወቀችው ሻምፒዮናው ሊጀመር ልክ አንድ ወር ሲቀረው ነበር፡፡ ሜዳልያዎቹን በዶሃ ተቀማጭነታቸውን ባደረጉ እና ሙሉለሙሉ ሴቶች በተደራጁበት ቡድን እንደተሰራ ሲታወቅ፤ የዶሃን ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎችና የካሊፋ ኢንተርናሽናል ስታድዬም በላያቸው የተቀረፀባቸው ሆነዋል፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ያሉ 13 የተለያዩ ምልክቶችም በሜዳልያዎቹ ላይ አርፈዋል:: በሌላ በኩል የውድድሩ ገድ ምልክት ‹‹ፋላህ›› የሚባልና የአትሌት ቁመና ያለው ፋልኮን ሲሆን በኳታር ባንዲራ መደበኛ እና ዋና ቀለም የታጠቀ ሆኗል፡፡ ይህን የገድ ምልክት ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴው ከ21 በላይ የዲዛይን ንድፎችን አወዳድሮ ሲሆን አሸናፊው 10ሺህ የኳታር ሪያል ወይም 2800 ዶላር ተሸልሟል:: ነበዓለም ሻምፒዮናው ከመላው ዓለም የተውጣጡ ከ4000 በላይ በጎፈቃደኞች የሚኖሩ ሲሆን የትኬት ዋጋዎች በአራት የተለያዩ የዋጋ ደረጃዎች 60፤ 120፤ 150 እና 300 የኳታር ሪያል እንደሆነ ሲታወቅ የትኬቶች ሽያጭ ፈጣን እንደነበር ተወስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡድንና የዝግጅት ሁኔታው
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ሻምፒዮናው የሚያደርገውን ዝግጅት የጀመረው በማራቶን ቡድን ምርጫ ከአምስት ወራት በፊት ነበር፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው 6 ሳምንታት ሲቀሩት ደግሞ ሙሉ ቡድኑን በይፋ አስታውቋል፡፡ ምርጫውን ለማከናወን  ከ2 ወር በፊት በሆላንድ ሄንግሎ በተከናወነው የረጅምና መካከለኛ ርቀት እንዲሁም የ3ሺ ሜትር መሰናክል የማጣርያ ውድድሮች፤ በዳይመንድ ሊግ ላይ በ5ሺ ሜትር፣ በመካከለኛ እና በ3ሺ ሜትር መሰናክል በነበሩ ተሳትፎዎችና ውጤቶች፤ ከ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎ በኋላ የተመዘገቡ ውጤቶች ከግምት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በእነዚህ ውድድሮች ጠንካራ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመምረጥ በሚያስችል አሰራር ላይ በፌደሬሽኑ በኩል ጥሩ ትኩረት መሰጠቱን ያመለክታል፡፡
ፌደሬሽኑ ከ5 ወራት ቀደም ብሎ የመጀመርያውን ምርጫ በሙሉ መተማመን ያደረገው  በማራቶን ሩጫ በሁለቱም ፆታዎች የሚሳተፉትን የማራቶኒስቶች ቡድን ነው፡፡  የማራቶን ቡድን ዋና ተወዳዳሪዎችን ከነተጠባባቂዎቻቸው የመረጠው፤ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የዋና እና የወርቅ ደረጃ በተሰጣቸው ማራቶኖች ከፈረንጆቹ መስከረም 2018 እስከ ሚያዝያ 2019 ድረስ ተወዳድረው ያስመዘገቡትን የተሻለ ሰዓት በማወዳደር ነበር፡፡ ከ2 ወር በፊት በሆላንዷ ከተማ ሄንግሎ ለዓለም ሻምፒዮና የተካሄደው ማጣርያ ደግሞ በረጅም ርቀት የሚወዳደሩትን ለመለየት አግዞታል፡፡ ሄንግሎ ላይ በተለያዩ የውድድር መደቦች በሁለቱም ፆታዎች የተደረጉ ውድድሮችን አስመልክቶ በወቅቱ ፍሎትራክ እንደዘገበው በማጣርያው  በሁለቱም ፆታዎች በ10ሺ ሜትር የተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች በታሪክ የተመዘገቡ ነበር፤ በማጣርያው በወንዶች ምድብ 6  አትሌቶች ከ27 ደቂቃ በታች መግባታቸው ከስምንት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ያጋጠመ ሲሆን፤ በሴቶች ምድብ ደግሞ ከ31 ደቂቃ በታች የገቡት 10 አትሌቶች መግባታቸው ከ14 ዓመታት በኋላ የተከሰተ ነው፡፡ በሄንግሎው ውድድር በ3 ሺህ ሜትር . መሠናክል ወንዶችና ሴቶች፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች እና በ800 ሜትር ወንዶችና ሴቶች ማጣሪያውን ያለፉ አትሌቶች በምርጫው ተካትተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በወንዶች በ1500 ሜትር፤ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል እና በማራቶን እንዲሁም  በሴቶች ደግሞ በ800 ሜትር፤ በ20 ኪሜትር እርምጃ፤ በ1500 ሜትር፤ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል እና በማራቶን የሚሳተፍ ይሆናል፡፡  37 አባላት ባሉበት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ሻምፒዮንነት ክብራቸውን ለማስጠበቅ ወደ ኳታር የሚጓዙት በ5ሺ የዓለም ሻምፒዮን የሆነው አትሌት ሙክታር እድሪስ እና የ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኗ አልማዝ አያና ናቸው፡፡ በ3ሺ ሜትር የዘንድሮ ዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ጌትነት ዋሌ የቡድኑ አባል ሲሆን በረጅም ርቀት የዓለም ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡት ሳሙኤል ተፈራ፤ ሰለሞን ባረጋ፤ ሃጎስ ገብረህይወትና ለተሰንበት ግደይ እንዲሁም የዓለም ሪከርድ ያለው ዮሚፍ ቀጀልቻ ይገኙበታል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በመጨረሻ ሰዓት ያጋጠመው ክፍተት በ1500 ሜትር የዓለም ሪከርድ ባለቤትና የቀድሞ የዓለም ሻምፒዮን አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በመጨረሻው ሳምንታት ባጋጠማት ጉዳት ከሻምፒዮናው ውጭ ለመሆን መገደዷ ነው:: አሁን 28 ዓመቷ ላይ የምተገኘው ገንዘቤ ጉዳቱ ያጋጠማት በነሐሴ ወር በዙሪክ የተሳተፈችበት የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ ነው፡፡ አትሌት ገንዘቤ በ2015 እኤአ ላይ በቤጂንግ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ካስመዘገበች በኋላ ከ2 ዓመታት በፊት ለንደን ላይ በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ ተወዳድራ በ12ኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኳታር ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የሜዳልያ ውጤት ያስመዘግበባቸዋል ተብለው የሚጠበቁት ውድድሮች በ10ሺ፤ በ5ሺ ሜትር፤ በማራቶን እንዲሁም 3ሺ ሜትር መሰናክል በሁለቱም ፆታዎች የሚደረጉ ውድድሮች ናቸው፡፡ በ10ሺ ሜትር 5 ጊዜ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሞ ፋራህ ከትራክ ውድድር መራቁ ኳታር ላይ በርቀቱ የሻምፒዮናነት ክብሩን ከሶስት የዓለም ሻምፒዮናዎች በኋላ ለመረከብ በኢትዮጵያ፤ በኬንያ እና በሌሎች አገራት አትሌቶች መካከከል ከባድ ፉክክር የሚጠበቅ ይሆናል:: የኢትዮጵያ ቡድን በዓለም ሻምፒዮናው ላይ በተለይ በረጅም ርቀት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች እንዲሁም በማራቶን ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደሚችል ግምት አለ፡፡ ቡድኑ ከውድድር ዘመኑ ውጤታማነት ጋር ተያይዞ ባለው መነቃቃት ከሚያደርገው ዝግጅት ባሻገር አስፈላጊውን የሜዳልያ ስኬቶች ለማስመዝገብ በመጨረሻ ሳምንት የሚስተዋሉ ዝግጅቶችና ሁኔታዎች ወሳኝነት አላቸው፡፡ የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች፤ የህክምና እና የስነልቦና ባለሙያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ክፍሉ በኳታር ከባድ የአየር ሙቀትና የውድድር ሰዓት ለውጥ፤ በተቀናቃኞች ወቅታዊ ደረጃ እና በቡድን ስራ ላይ በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራቱን የሚያሳውቅበት መድረክ ከዓለም ሻምፒዮናው በፊት እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡
በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ለኢትዮጵያ ከ10 ወራት በፊት በቀረበው ትንበያ
የአሜሪካ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በቅርበት የሚሰራው ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ Track & Field News በድረገፁ ከ10 ወራት በፊት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን የሜዳልያ ትንበያዎች አድርጎ ነበር፡፡ በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ውስጥ በዓለም አትሌቲክስ የውጤት እና የሰዓት ደረጃዎች ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በትንበያው የተሳተፉ ሲሆን፤ በትንበያቸው ቅድሚያ በሰጡት የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን በድምሩ 28  ሜዳልያዎች 14 በወንዶች 14 በሴቶች እንደሚመዘገቡና 11 የወርቅ ሜዳልያዎች እንደሚሆኑ ገምተዋል፡፡ በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ለኢትዮጵያ ከ10 ወራት በፊት በቀረበው ትንበያ በአጠቃላይ ሁለት የወርቅ፤ ሁለት የብርና 4 የነሃስ ሜዳልያዎች እንደምታገኝ ነው፡፡ በወንዶች ምድብ በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር እና በ3ሺ ሜትር መሰናክል የሜዳልያ ግምት አልተሰጠም፡፡ በአጠቃላይ ግን በ5ሺ ሜትር እና በማራቶን 1 የወርቅ፤ ሁለት የብርና ሁለት የነሐስ ሜዳያዎች ለኢትዮጵያ ተንበየዋል፡፡ በ5ሺ ሜትር  የተተነበየው አረንጓዴው ጎርፍ ሲሆን  ሰለሞን ባረጋ የወርቅ፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ የብር እና ሃጎስ ገብረህይወት የነሐስ ሜዳልያዎች ይወስዳሉ በሚል ነው:: በአንፃሩ በ10ሺ ሜትር ግን ሶስቱን ሜዳልያዎች ኬንያውያን አትሌቶች ይወስዱታል በሚል ገምተዋል፡፡ በማራቶን የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ለሆነው ኤሊውድ ኪፕቾጌ የወርቅ ሜዳልያው ተሰጥቶ ልዑል ገብረስላሴ እና ታምራት ቶላ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎቹ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሴቶች ምድብም  በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር እና በ3ሺ ሜትር መሰናክል ለኢትዮጵያውያን የሜዳልያ ግምት አልተሰጠም፡፡ በአጠቃላይ ግን በ5ሺ፤ በ10ሺ ሜትር እና በማራቶን 1 የወርቅና ሁለት የነሐስ ሜዳያዎች ለኢትዮጵያ ተንበየዋል፡፡ በ5ሺ ሜትር ገንዘቤ ዲባ የነሐስ ሜዳልያ፤ በ10ሺ ሜትር አልማዝ አያና የወርቅና ሰንበሬ ተፈሪ የነሐስ ሜዳልያዎች እንደሚወስዱ ሲገመት በማራቶን የነሐስ ሜዳልያው ለማትሳተው ጥሩነሽ ዲባባ ተገምቶላታል፡፡
በዓለም ሻምፒዮናው የኢትዮጵያ ታሪክ
ከ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት ኢትዮጵያ ባለፉት 16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 77 (27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳልያዎች) በመሰብሰብ፤ በውድድሩ ታሪክ አንድና ከዚያም በላይ ካገኙ 101 አገራት መካከል በ7ኛ ደረጃ ትቀመጣለች፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት 16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ከ1ኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ባስመዘገቡ አትሌቶች በሚወጣ ደረጃም በ808 ነጥብ ከዓለም ሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች:: የውጤቱ ዝርዝርም 27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳልያዎች እንዲሁም 20 ጊዜ 4ኛ ደረጃ፤ 18 ጊዜ 5ኛ ደረጃ፤ 14 ጊዜ  6ኛ ደረጃ፤ 19 ጊዜ 7ኛ ደረጃ እንዲሁም 15 ጊዜ 8ኛ ደረጃ በኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ አትሌቶች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ናቸው፡፡

Read 10309 times