Saturday, 21 September 2019 07:55

“የዘመን አዙሪት!”

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

 “ያገር ምድጃ ዘር ደም ጥዶ ሊታጠን አጥንት ሲማገድ…”
                       

          ከምንስማማበት የማንግባባበት ከሞላባት ዓለም
ደም ስርህ እስኪገተር ጉሮሮዬ እስኪደርቅ
ብንጮህ ብርቅ አይደለም፡፡
ተናግረህ እስክትጨርስ አውርቼ እስካበቃ
ላመል በጄ ብለን
ከተደማመጥን አዎ እንግባባለን፥
ካልተደማመጥንም አብረን ውለን አድረን
እየዘባረቅንም ኑሮን እንኖራለን…
        .   .   .
እስቲ እንደዋወል እንገናኝ ላፍታ
ነይ በሳቅ ግደይኝ ወይ ደረቴን ልምታ፥
በአንድ ማኪያቶ ካፌ ወንበር አሙቀን
የፍቅር ድርሣን ጦር መዝዘን ተጨቃጭቀን
እንደስኩር እስቲ…
ሃሳብ ስንተክል - ነገር ስንነቅል፥
ስደቢኝ  - ልውቀስሽ
ማዲያት አይሆንብሽ  ፊቴ ላይ አይብቅል፥
አንቺ ወዲያ ማዶ እኔ ወዲህ ማዶ
አስተዳደጋችን እንደ ዱባና ቅል፡፡
አይጨበጤ ጉም ዘመን  እንደየመልኩ
ባህርይው  እልፍ  ነው አዱኛው  ምስቅልቅል፥
በወል መኖር ተስፋ ጽልመቱን መንግለን
እንዝራ ፀዳል ዘር ብርሃን እሚያበቅል፡፡
እና አንዳንድ ሰሞን  . . .
ዘመን ልክፍተኛ ጤና አዳም ቢነሳን በሰላም
መዛመድ፥
ጥንትም እቅፍ ድግፍ አ´ርጎ በሚያዋዛን በእድሜ
በጎው ገመድ
ከስጋ ህቅታም ነጥሮ በመንፈስ ልዕልና ነፍስን
በማዛመድ፥
ያገር ምድጃ ዘር ደም ጥዶ ሊታጠን አጥንት
ሲማገድ
ትንፋሽ አሳጥቶ አፍኖ እማይገድለን ነፋሻማ
መንገድ፥
እንደ የፀሐይ ገበታ ማርና ወተት ማዕድ  ሳር
የአበባ ምንጣፍ
የተመራረቅነው የቡራኬ ድርሣን በብርሃን
እንዲጻፍ
ከፍ ብለን ስንበርር የማይረግፍ ላባ ቢሆንልን
አክናፍ፥
ከሌት መዐልት ሾልከን ከጽልመቱ የወህኒ አጥር
ቁም ከሚያባንነን፥
ለሀሳብ ባሪያ ያደርነው በቃተትናት መና ጠሉ
ካረጠበን፥
በጋራ የቃዠነው የቀበጣጠርነው ህልማችን
ቢያኖረን
በሀገራችን ሰማይ ስር፡ ከልካይ የሌለበት ገነት እንወርሳለን . . .
.   .   .
‹‹ብርቱ ጉዳይ!›› ብዬህ ምሽት ተቀጣጥረን
የፋመች ጨረቃ ሀሴት ተከናንበን
በከዋክብት ተከብበን
መለኪያ ጨብጠን ባልኮኒ ላይ ቆመን
ባለጌ ወንበር ቂጥ ባለጌ ሃሳብ ጥደን
ደም የሌለው ቡጢ ግብግብ ገጥመን
በቃላት ጦርነት ‹‹ድሉ የኔ!›› ብለን
ሺህ ጊዜ ስንጋጭ ሺህ ጊዜ ስንገጥም ብንኖርስ
ምናለ ?
ደሞ ዘመን አልፎ
ከርሞም ይኸ አብሮነት ጥሎን ካልተነነ…
.   .   .
ብንጤስስ  እንደ ጧፍ - ብንቀልጥ እንደ ሻማ -
ብንከስል ´ንደ ላምባ ዕቃ፥
ለምን ጭርጭር አንል  
በወል ተንቦግቡገን - ባገር የእሳት ላንቃ . . .
የዘመን አዙሪት ጨለማው ከሚውጠን
ለዓለሙ ሁሉ ያስጫርነው መቅረዛችን ወድቃ፥
በዝምታ ወህኒ የተዳፈነውን ረመጥ እፍ ብለን
ስንደነቃቀፍ ነፍስያችን ሞቃ፥  
ስንጦፍ በተስፋ ከሰመመን አዚም እስራት
እንድንነቃ
ሺህ ጊዜ ስንላተም መንፈሳችን ነጥቃ . . .
በግጭቱ ብርሃን የወገግታው ቅጽበት
ጥበብ ዘር ከታየ ለጥቅስ እሚበቃ
ሀሳብ ፍሙ ይንተርከክ
ብልጭታውን ጭረን አብረን እንሙቃ
እየተነታረክንም ልቅ እምነታችንን እንተዋወቃ?!
እስካልፈጀን ድረስ ረመጥ እስካልተወ
የውሎ አዳራችን የግጭት ሰበቃ፥
ብርሃን ፍንጣሪው ቦግ እልም ብሎ ሙት ነፍስ
ካነቃ
መለኮስ  ከቻልን  ነድደን እንድመቃ !  
በውብ ሩህ ደመራ ፀሐይዋን እንሁና በቃ!!!
(‹‹የፀሐይ ገበታ›› ተራኪ ሥነ -ግጥም 2005 ዓ.ም - ያልታተመ፡፡)

Read 1444 times