Saturday, 14 September 2019 11:08

የመርከቢቱ መናወጥ የሚያቆመው መቼ ነው?

Written by  ጤርጢዮስ ዘ-ቫቲካን
Rate this item
(1 Vote)

“ሁላችንም ከራስ ወዳድነት ስሜት ወጥተን፣ ለብሔራዊ እርቅና መግባባት ካልሠራን፣ ልክ እንደ ዮናስ በነፍስ ወከፍ “ለአገሬ ሰላም መደፍረስና ለአንድነቷ መናጋት ምክንያቱ እኔ ነኝ” ወደሚል ትሕትና ካልመጣን፣ መርከቢቱ በእምቢተኝነታችን ማዕበል መናጧ ይቀጥላል!--”
            
         ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ በሁላችንም ልብ ውስጥ የሚመጣ የአዲስ ሕይወት ተስፋ አለ፡፡ አሮጌውን ለአሮጌነቱ ትቶ ነገን በመልካም የመቀበል ስሜትም ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይህ ስሜት ግለሰባዊ ብቻ አይደለም፡፡ ቤተሰባዊም፣ ማህበረሰባዊም፣ አገራዊም ነው፡፡ ስሪታችን ውስጥ እነዚህ ሁሉ ቀለሞች አሉ:: አንዱ ያለ ሌላው የሚፈጥረው ነጠላ የደስታም ሆነ የተስፋ ስሜት የለም፡፡ አንዱ ያለ ሌላው ሕብር አይደምቅም፡፡ አብሮ ካልተገመደና፣ አብሮ ካልተሸመነ ረቂቅ ውበቱን ተመልክቶ ተፈጥሮን ማድነቅ አይቻልም፡፡
 የአዲስ ዘመንን በጐ ስሜቶች ለማጣጣም ደግሞ በቅድሚያ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ህልውና ብቻ ሳይሆን ህልውናችን እውን የሚሆንበት ሥፍራና ከባቢ ያሻናል፡፡ በደስታ ለመዝፈንም ሆነ በሀሴት ለመዘመር በቅድሚያ ቦታ ማግኘት ግድ ይለናል፡፡ ታላቁ መጽሐፍ “በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ” እንዲል ምህረቱ በዝቶልን፣ ወደ አዲስ ዘመን ለመሻገር በቃን እንጂ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት፣ እንደ አንድ አገር ሕዝቦች በጋራ ለመኖር በማያስችሉን ከባድ ፈተናዎች ውስጥ አልፈናል:: እነሆ በከፍታና በዝቅታ፣ በደስታና በሀዘን፣ በእምነትና በጥርጣሬ ማዕበል እየተናጥንም ቢሆን 2012 ዓ.ም ላይ ደርሰናል፡፡
ይሁንና እስካሁንም የቱን በጐ ነገር ይዘን፣ የቱን ክፉ ነገር ጥለን፣ ወደ አዲሱ ዘመን እንደተሻገርን አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ምክንያቱም የእኛ አገር ፖለቲካ ለትንታኔ ያስቸገረ፣ ከተገማችነት በላይ የረቀቀ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ አሁን ላይ በአገራችን ሃይማኖተኝነት ያልገራው፣ እውቀትና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላሸነፈው የራስ ወዳድነት ስሜት ነግሷል፡፡ ሁሉም በእኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ ፉክክር ተጠምዷል፡፡ ከዚህ ቀደም ያልተሞከረ፣ አንዱ ሌላውን ዝቅ ብሎ የማገልገል መርህ፣ በፊቱ ቀርቦለት ሳለ፣ ያንን ገንዘቡ ለማድረግ አልፈቀደም፡፡ ከመደመር ፍልስፍና ይልቅ፣ አንድ ሰው እንደተናገሩት፤ “እግዚአብሔር የለም፣ አይሆንም ብሎ እየከለከለን እንጂ እኛማ እንደ የመንና ሦርያ ካልፈራረስን፣ እንደ ሊቢያና ሶማሊያ ካልሆንን እያልን ነው” እናም “እኔ ያልኩት ብቻ ያጽና” የሚል ትምክህት፤ እምዬ አገራችንን ሊያፈራርሳት ዙሪያ ገባዋን እየዞራት ነው፡፡
የፖለቲካ ትንታኔውን ለፖለቲከኞቹ ትቼ፣ እኔ በእኔ የአመለካከት ዐውድ ውስጥ ሆኜ፣ አሁን ላይ ያለችውን አገሬን ነቢይ ዮናስ በተሳፈረባት መርከብ መስዬ አያታለሁ፡፡ በበርካታ የለውጥና የነውጥ ማዕበል ከዚህ ወደዚያ፣ ከዚያ ወደዚህ ስትላጋም ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ህዝቦቿም የቱ እንደሚሻላቸው፤ ማንኛው የአስተዳደር ሥርዓት እንደሚበጃቸው ለመምረጥ ሁልጊዜም የሚቆሙበት ቦታ እውነታውን አላሳይ እያላቸው ሲቸገሩ ሺዎች ዓመታትን ተሻግረዋል፤ ሆኖም የቱም ተመችቷቸው እፎይ ብለው አያውቁም፤ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጡን ለማጣፈጥ ቢደክሙም፣ ወጡን በቅጡ አጣጥመው ስለ ጥፍጥናው ሲመሰክሩ አይታዩም፡፡ የችግራቸውን ሥረ መሠረት ቆፍረው ለማግኘት ቢታገሉም፣ እስካሁንም ተገቢው ጥልቀት ላይ አልደረሱም፡፡
ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የነነዌን ሕዝብ የማዳን ተልዕኮ አሻፈረኝ ብሎ ወደ ተርሌስ ለመኮብለል መርከብ የተሳፈረው ዮናስ፤ በእርሱ እምቢታ ሊጠፋ ካለው ሕዝብ ይልቅ ግለሰባዊ ክብሩ በልጦበት በመርከቢቱ የታችኛው ክፍል ተኝቶ ሳለ፣ ብርቱ ማዕበል ተነስቶ ተሣፋሪውን ሁሉ እያናወጠ ነበር፤ የመርከቢቱ ካፒቴኖችም ይይዙት ይጨበጡት ጠፍቷቸው፣ የራሣቸውንም ሆነ የተሣፋሪውን ነፍስ ለማዳን ያላቸውን እውቀትና ብልሃት ሁሉ አሟጥጠው ቢጠቀሙም አልሆነም፡፡ ከማዕበሉ ኃይለኝነት የተነሳ ከወዲህና ከወዲያ የምትላጋዋን መርከብ ሚዛን ለመጠበቅ የተጫነባትን ጠቃሚ ዕቃ ሁሉ ወደ ባሕሩ እስከ መጣል ሁሉንም ሞከረዋል፡፡ ከመርከቢቱ ካፒቴኖች አንዱ፣ ወደ ታችኛው ክፍል ወርዶ ሳለ፣ ወዳገኘው ዮናስ ቀርቦ፡- “ሰው ሁሉ ተጨንቆ ወደ አምላኩ ለእርዳታ ሲጣራ አንተ ምነው ተኝተሃል?” ብሎ በግርምት እስኪጠይቀው ድረስ ዮናስ በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ሆኖ የራሱን ህልም እያለመ ነበር፡፡
ዮናስ የግድ ሰዓት መጥቶበት “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁት አውቃለሁና አንስታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ፀጥ ይልላችኋል” የሚል ኑዛዜ ከአንደበቱ እስኪያወጣ ድረስ የመርከቢቱ በማዕበል መናጥ አላቆመም፤ የሆነው ሁሉ የሆነው በእርሱ ራስ ወዳድነት እንደሆነ ለዮናስ ምሥጢሩ የታወቀውም ቆይቶ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በአገራችን ተከስቶ የነበረውን ሕዝባዊ ማዕበል፣ ያንን ተክትሎ የመጣውን ነውጥና ለውጥም የማመሳክረው ከዚሁ የነቢዩ ዮናስ ታሪክ ጋር ነው፡፡ ከመቶ ሚሊዮን ሰው በላይ አሳፍራ በታላቅ ማዕበል ስትናጥ የነበረችው ኢትዮጵያ የተሰኘች መርከብ ውስጥ እኔም ነበርኩና “በማዕበል” መናወጥ ምን እንደሚመስል አውቃለሁ፡፡ ማንም ባልገመተው ሁኔታ የማዕበሉን ፀጥ ማለት ያያዝኩትም፤ ከእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ጋር ነው፡፡ ለነገሩ ሃይማኖተኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ታላላቅ ፖለቲከኞችም ያሉት ይህንኑ ነው፡፡
በእርግጥም ደግሞ በወቅቱ ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ስለመሆኗ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገሮቹ የፖለቲካ ተንታኞች በጋራ የተስማሙበት ጉዳይ ነበር፡፡ ከሁለቱም ወገን የሚጻፉና የሚነገሩ ዘገባዎችንም አንብቤያለሁ፣ ሰምቻለሁ:: የዚህችኛይቱን መርከብ መሪ የጨበጡቱ ካፒቴኖችም በአደገኛ ማዕበል እየተናወጠች የነበረችውን መርከብ እንዴት ባለ ብልሃት ሾፍረው ወደ ዳርቻም ማስጠጋት እንዳለባቸው መላው ጠፍቷቸው ነበር፡፡ ለአሥራ ሰባት ቀናት በመርከቢቱ ዝግ ክፍል ውስጥ መሽገው ሲመክሩ በነበረበት ወቅትም የእኛ የተሣፋሪዎቹ ሥጋት ጣራ ነክቶ መዝሙረኛው ዳዊት “ለሞት አንድ እርምጃ ቀረኝ” እንዳለው ዓይነት ሆነን ነበር:: አንድዬ ጣልቃ ገብቶልን በስተመጨረሻው የሆነው ባይሆን ኖሮም፣ መርከባችን ወዲያውኑ ተሳብብራ፣ በርካቶቻችን የባህር አውሬ ይበላን ነበር፡፡
በዚያን ቀውጢ ወቅት ስለ መለኮታዊ ተዓምር መኖር ቢያውቅም እንኳ ፖለቲካ ውስጥ ግን የዘዋሪዎቹን አስተሳሰባዊ ብስለትና የአመራር ብልሃት እንጂ ተዓምር መጠበቅ ተላላነት የሚመስለው አንድ ወዳጄ ያለኝን በፍፁም አልረሳውም፡፡ ይህ የቅርቤ ሰው ከለውጡ በፊት ስለ ሰብዓዊ መብት ሲሟገት፣ አገሩ ነፃነትና እኩልነት የሰፈነባት እንድትሆን ሲታገል ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በተመሠረተ ሰሞን  በፓርቲው ሥራ ውስጥ የፊት ተሰላፊ ሆኖ በታላቅ ቅንዐት አገልግሏል፡፡ ይህን ብቻ ሳይሆን በጊዜው አይነኬ የነበረውን የፖለቲካ ድርጅት የሚተነኩስ ድራማ ጽፎ ለዕይታ አቅርቧል:: በፖለቲካ ሰበብ ደጋግሞ ሲታሰርም በየፖሊስ ጣቢያው እየሄድኩ ስጠይቀው ቆይቻለሁ፡፡ እጅግ ተጋፋጭነት የሞላበት የትግል ስልቱ ሁለት ህፃናት ልጆቹንና ባለቤቱን ለሰቀቀን የሚዳርግ መሆኑን ቢያውቅም፣ ያመነበትን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማይል ግትር ነበር፡፡
ይሁንና ከአንድ ዓመት በፊት የተሳፈርንባትን “መርከብ” ይሾፍሩ የነበሩ ካፒታኖች ከማዕበሉ የማምለጫችንን መላ ያፈላልጉ በነበረበት የአሥራ ሰባቱ ቀናት የምክክር መድረክ መገባደጃ ላይ ስልክ ደውሎልኝና ስሜን በቁልምጫ ጠርቶ፡- “ከዚህ በኋላ እንኳ ተስፋችን እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ ከልጆቼና ከሚስቴ ጋር ለመፀለይ ወደ ቤት እየሄድኩ ነው” ባለኝ ጊዜ አንድም ከልቤ መሳቄ፣ አንድም በወቅቱ የነበረው የአገራችን ሁኔታ አሳሳቢነት ገዝፎ እንዲታየኝ ያደረገ መሆኑ ትዝ ይለኛል፡፡
ከመርከቧ ካፒቴኖች ዋና የነበሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በአንድ የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ላይ ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ በአንፃራዊ መልኩም ቢሆን ወጀብና አውሎ ነፋሱ ፀጥ፣ እረጭ ብሎ መርከቢቱ ተረጋግታ መቆም የቻለችው በአንድዬ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ በዚህ ፀጥታ ውስጥ መስማት የጀመርነው የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የአንድነት ዜማም የመረጋጋት ስሜት ያጎናጸፈንና በአድናቆት እንድንሞላ ያደረገን ነበር፡፡ ዛሬም ዳግመኛ መርከቢቱ በሰላም እንዳትጓዝ ማዕበል የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች ከዚህም ከዚያም እየተነሱ ቢሆንም ማዕበሉን ፀጥ፣ ረጭ የማድረጊያው መላ ግን ተገኝቷል፡፡ መላው ቀድሞ የነበረውን የኢትዮጵያ የአንድነት መንፈስ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ነው፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታና በመደብ ያልተከፋፈለችን ጠንካራ አገር ለመገንባት መነሳት ነው፡፡
መላው “እኔ ያልኩት ብቻ ይጽና” ከሚል ራስ ወዳድነት ስሜት ወጥቶ፣ በምንወዳት አገራችን በፍቅር ለመኖር መሻት ነው፡፡ አንድ የቅርቤ የሆኑ ኦርቶዶክሳዊ አባት እንዳሉት፤ የእኛ አንድነት እንደ ምሥጢረ ሥላሴ “አንድ” ብሎ ጀምሮ ወደ አካላዊ ሦስትነት ትንታኔ የሚገባ ካልሆነ፣ እውነተኛ አንድነት መቼም ቢሆን ሊመጣ ስለማይችል፣ለዚያ ዓይነቱ አንድነት መፈጠር መትጋት የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ፈውሳችን ያለው በመደመር ፍልስፍና ውስጥ ነው፡፡ በድሮ በሬ ለማረስ ለሚሹትም እንኳ የተሻለው የበረከት መንገድ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የመቻቻል ጐዳና ነው፡፡
ይህ በእርግጥም የዘላለም ጥግ ነውና በዚህችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “የዘላለም ጥግ” ሳጥን ውስጥ ተሰድረው ካነበብኳቸው የታዋቂ ሰዎች አባባሎች ከፊሎቹን ከሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም  ብጠቅስ ደስ ይለኛል፡፡  
ሃይማኖትን በተመለከተ አብሂጂት ናስካር፡- “ሃይማኖት አንድነት ማምጣት ካልቻለ ሃይማኖት አይደለም” ሲል፣ ትምህርትን በተመለከተ ደግሞ ሄለን ኬለር፡- “የትምህርት የላቀው ውጤት መቻቻልን ማስፈን ነው” ብላለች፡፡
ሩብ ብሪጅስ፡- “መቻቻል፣ መከባበርና እኩልነት በተፃፈው ሕጋችን ውስጥ ተካትተዋል፤ ነገር ግን በተወሰኑ ሰዎቻችን ልብ ውስጥ አልሰረፀም” ሲል፣ ፍሬድሪክ ዱርማንት ደግሞ ፡- “መቻቻል ከሌለ ዓለማችን ወደ ሲኦልነት ትቀየራለች” በማለት ያስጠነቅቃል፡፡ ቴንዚን ግያለቶ፡- “መቻቻልና እሩህሩህነት የደከማነት ምልክት ዓይደለም፤ የጥንካሬ እንጂ” በማለት ልበ ኩሩነትን ሲገዳደር፣ የጥቁሮች መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ደግሞ በአሜሪካን አገር ተከስቶ የነበረውን የነጮችና የጥቁሮች መከፋፈል ለመዳኘት የተጠቀመበት ኃይለ ቃል፡- “እንደ ወንድማማቾች በአንድ ላይ አብረን መኖር መልመድ አለብን ወይም እንደ ጅሎች ተያይዘን ማለቅ” የሚል ነው፡፡
የእኛም ምርጫና እጣ ፈንታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ አዎን፣ በእግዚአብሔር ቸርነት የትናንቱን ጨለማ ሰንጥቀን አልፈን የብርሃን ጭላንጭል እያየን ወዳለንበት ብሩህ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ በተስፋና በስጋት መካከል እንድንዋልል የሚያደርጉ በርካታ መሰናክሎች እየተጋረጡብን ቢሆንም፣ የለውጡ ብርሃን ጨርሶ ሳይጠፋ ወደ አዲሱ ዓመት ተሸጋግረናል፡፡ ግን ደግሞ ፈጣሪ በሰጠን ዕድል መጠቀም ወይም አለመቀጠም የእኛ ፈንታ ነውና፣ አገራችንን ወደ ሲኦልነት የመቀየር አሊያም ለሕዝቦቿ የተመቸች ምድረ ገነት የማድረጉ ነፃ ፈቃድ በእጃችን ላይ ነው ያለው፡፡
በግሌ በአዲሱ የለውጥ መንፈስ ውስጥ ያለውን የአስተሳሰብ ሥርዓት መከተል የነገዋን ኢትዮጵያ ያማረችና የሰመረች ለማድረግ ቁልፍ ሚና እንዳለው ከሚያምኑት ወገን ነኝ፡፡ ለዘመኑ የሚመጥነው የሰለጠነ ፍልስፍናም “መደመር” እንደሆነ አስባለሁ፡፡ የተሳፈርንባት መርከብ አዲሶቹ ካፒቴኖች፣ አቅምና በጐ ፈቃድ ተጨምሮበት፣ መርከቢቱን ሥርዓት ባለው መንገድ ለመዘወር የላቀ ችሎታና መልካም ሥነ ምግባር የተቸረውን፣ የዋናውን ካፒቴን ህልሞች ለማሳካት ካልፈቀድን፣ በአንድነት ተደምሮ የመጓዝን ፈቃደኝነት ካላሳየን የሚመጣ ዘላቂ መፍትሔ የለም:: ከመለያየት በላይ አንድነት ካስፈራን፣ አለመኖር ከመኖር በላይ ከሆነብን ታመናልና ለዚህ ህመማችን ከፍቅር፣ ከይቅርታና ከአንድነት መንፈስ የተሻለ መድኃኒት አናገኝም፡፡ ሁላችንም ከራስ ወዳድነት ስሜት ወጥተን፣ ለብሔራዊ እርቅና መግባባት ካልሠራን፣ ልክ እንደ ዮናስ በነፍስ ወከፍ “ለአገሬ ሰላም መደፍረስና ለአንድነቷ መናጋት ምክንያቱ እኔ ነኝ” ወደሚል ትሕትና ካልመጣን፣ መርከቢቱ በእምቢተኝነታችን ማዕበል መናጧ ይቀጥላል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና  ሕዝቦቿን
ከመለያየት ጥፋት ያድን!

Read 1548 times