Saturday, 14 September 2019 10:59

ትምህርት ሚኒስቴር ተጭበርብሮ አጭበረበረን!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)

 ባለፈው ዓመት (በ2011 ማለቴ ነው) በጽሁፎቼ ትኩረት ካደረግኩባቸው ጉዳዮች አንዱ የትምህርት ጉዳይ ነበር፡፡ እንደተፈራውም አልቀረ አሮጌውን ዓመት የሸኘነው በትምህርት ሚኒስቴር አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ውዝግብና በአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የስርቆት ዜና ነው፡፡ የዚህን ጽሁፌን ርዕስ “ትምህርት ሚኒስቴር ተጭበርብሮ አጭበረበረን” ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወደ ምክንያቶቼ ከመሄዴ በፊት አንዳንድ ጉዳዮችን ላንሳና በምክንያቱ ላይ እመለስበታለሁ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት 25 ዓመታት የነበረውን የትምህርት ሂደት ከገመገመ በኋላ “ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ (50%) አንዲት አጭር ዓረፍተ ነገር አንብበው ለመገንዘብ የሚያስችል እውቀት የላቸውም። ሩብ (25%) ያህሉ ደግሞ አንዲትም ቃል ማንበብና መጻፍ፣ መደመርና ማባዛት… አይችሉም” የሚል ዜና አምና በዚህ ወቅት በጥናት አረጋግጦ ነግሮን ነበር፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ትምህርት ለሁሉም፣ ለሀገሪቱ ህፃናት ተደራሽ ባለመሆኑና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ባለመቻሉ፣ አራት ክፍሎች ያሉት “የትምህርትና የስልጠና ችግሮችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን…” የያዘ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱንም የነገረን ያኔ ነው፡፡
በነባሩ የትምህርት ፖሊሲ ተምረው ከሚመረቁ ወጣቶች ብዙዎቹ “garbage in garbage out” ዓይነት የመከኑ፣ እውቀት አልባ፣ ስማቸውን እንኳ በትክክለኛ ፊደል አስተካክለው መጻፍ የተሳናቸው መሆናቸውን ያስተዋሉ ሰዎች፤ ገና ከጅምሩ “ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ ነው” በማለት ሲናገሩ፣ ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ አስተያየቱን እንደ “ሟርት”፣ ትችቱን እንደ “ጠላት ወሬ” ሲቆጥር የነበረው ትምህርት ሚኒስቴር፤ እንደ አዲስ ግኝት የፖሊሲውን የድክመት መርዶ መናገሩ ሲገርመን፤ ይህንን ለመቀየር በአዲሱ ፍኖተ ካርታ አማካኝነት “እውቀትን ማስጨበጥ ሳይሆን ሙያን ማስተማር አስፈላጊ ነው” የሚል አስቂኝ የትምህርት ዓላማ ይዞ ብቅ ማለቱን ስንሰማ፣ “ኧረ እየተስተዋለ! ይህ ማለት እኮ ‘ያለ እውቀት የህክምና ሙያ፣ ያለ እውቀት የምህንድስናም ሆነ የአናፂነት ሙያ…’ እንደሚኖር ማሰብ ነው…” በማለት በወቅቱ ተችተን ነበር - ሰሚ አላገኘንም እንጂ!
አበው “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” እንዲሉ፣ ጉድ ማሰማት የማይቸግረው የሀገራችን የትምህርት ሚኒስቴር፣ በዘንድሮው ክረምት ደግሞ በርካታ ነገሮችን ሲነግረን ከርሟል፡፡ የአነታራኪውን የትምህርት ፖሊሲና ፍኖተ ካርታ ጉዳይ ለጊዜው እንለፈውና በ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ላይ እናተኩር፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍልን የፈተና ውጤት በአዋጅ የነገረን በሐምሌ ወር አጋማሽ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ሀገር-አቀፍ የፈተና ውጤት ለህዝብ ይፋ ከመደረጉ በፊት ውጤቱ ምን ገጽታ እንዳለው በባለሙያዎች መታየት፣ መተንተንና መገምገም ሲገባው ከኮምፒዩተር የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) የተገኘን ውጤት እንዳለ ለህዝብ ይፋ መደረጉ መዘዝ አስከትሎ ነው የመጣው፡፡ በዚህም ምክንያት ውጤቱ በተገለጸ ማግስት የቅሬታ ዓይነት በየአቅጣጫው ይስተጋባ ጀመር፡፡ የጫጫታው ብዛት ትምህርት ሚኒስቴርን ካንቀላፋበት ያባነነው ነው የሚመስለው፡፡ ከእንቅልፉ ድንገት ባኖ የተነሳ ሰው ደግሞ መደናበር ማብዛቱ የታወቀ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴርም በተመሳሳይ ሁኔታ የተደናበሩ መግለጫዎችን በተከታታይ ማሰማቱን አስተውለናል…
በመጀመሪያው መግለጫ “ከፈተናዎቹ አንዱ በተሳሳተ የመልስ ቁልፍ የታረመ ስለሆነ እሱን እንደገና አርማለሁ” አለ፡፡ የአንድ ፈተና ውጤት የሚያመጣው ለውጥ ይኖር ይሆናል የሚል ተስፋ የሰነቁ ሰዎች፣ ውጤቱን በተስፋ ተጠባበቁ… ትምህርት ሚኒስቴር የ260 ሺህ ተፈታኞችን ፈተና በምን ዓይነት ፍጥነት እንዳረመው ባይታወቅም፣ “የአፕቲትዩድ” ፈተና “ታረመ” ተባለና ይህም ውጤት በይፋ ተገለጸ፡፡ ጫጫታው እንደገና አገረሸ:: ተማሪዎችም ወላጆችም ቅሬታ ያቀርቡ ጀመር፡፡ አክቲቪስቶች ቅሬታ ከማቅረብ አልፈው “ፈተናው ተሰርቋል” ማለት ጀመሩ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የተመዘገበው ውጤት፣ እንኳን ነገር ፈልፋይ አክቲቪስት እንደኔ ያለ ተራ ዜጋ፣ የፈተናውን ውጤት አይቶ የተሰረቀ መሆኑን ለመጠርጠር የሚያስቸግረው አይሆንም፡፡ ወከባና ጫጫታው የበዛባቸው የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ተረጋግተው መፍትሄ ማስቀመጥ ሲገባቸው፣ በድንጋጤ መዋከባቸውን በሚያሳይ መልኩ የፈተናውን ነገር ተወት አድርገው (አቅጣጫ ለማሳት በሚመስል መልኩ)፣ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ ዙሪያ መግለጫ መስጠት ጀመሩ፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ አበው፤ የፖሊሲው ጉዳይ እንኳን አቅጣጫ ሊያስቀይር ሌላ ጣጣ ይዞ መጣ፡፡ ይሄ ሁኔታ የበለጠ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎችን እንቅልፍ የነሳቸው መሰለ:: ጫጫታው ገፍቶ ሲመጣ፣ አሁንም ባልተረጋጋ ሁኔታ የክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችን በመሰብሰብ የፈተናውን ውጤት በተመለከተ መፍትሄ ለማስቀመጥ ሞከሩ፡፡ ፈተናው መሰረቁን ቢገነዘቡም ደፍረው “ፈተናው ተሰርቋል” አላሉንም:: ይልቁንም ፈተናው መጭበርበሩን እያወቁ፣ እኛን ወደ ማጨበርበር አመሩ፡፡ እናም “ከእረፍት በኋላ የተሰጡትን ፈተናዎች ውጤት ለዩንቨርስቲ መግቢያነት አንጠቀምባቸውም፡፡ የምንወስደው ከዚያ በፊት የተሰጡትን ፈተና ውጤቶች ነው” የሚል አዋጅ ነገሩን፡፡
እንደኔ እንደኔ፣ ይህም መፍትሄ ሆኖ አይታየኝም:: ምክንያቱም አንዳንድ የትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ፤ ከውጤቱ ተነስተን ፈተናው የት አካባቢ፣ በየትኛው ትምህርት ቤት ጭምር እንደተሰረቀ ማወቅ የሚያስቸግር አይደለም፡፡ ስለሆነም 260 ሺህ ተማሪዎችን በጅምላ ከመቅጣት ጥርጣሬ የታየባቸውን አካባቢዎች ተማሪዎች እንደገና መፈተን ይቻል ነበር፡፡ ይህንን ባለማድረጉ ትምህርት ሚኒስቴር ትልቅ ታሪካዊ ስህተት መሳሳቱን በታሪክ ፊት አስመዝግቧል ብዬ አምናለሁ፡፡
በመሰረቱ “ምርጥ” ፍኖተ ካርታና “ምርጥ” ፖሊሲ ማውጣት በቂ አይደለም፡፡ የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ “ጥራት ያለው ፖሊሲ” ማዘጋጀት አንዱ ግብዓት ይሆናል እንጂ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡ የትምህርት ጥራት የተለያዩ ችግሮች እንደሚጋረጡበት ይታመናል፡፡ ስለ ትምህርት ጥራት ስናወራ ቀዳሚውና ዋነኛው ግብዓት ደግሞ ጥራትና ብቃት ያለው መምህር ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የትምህርት ባለሙያ፤ አይረቤነቱ በተነገረለት ፖሊሲ ተምሮ ወደ ስራ የተሰማራ ነው፡፡ እናም እነዚህ “የመከነው ፖሊሲ” ውጤቶች የሆኑ መምህራን፤ “ፈተና በመስረቅ ተመርቀው ለተማሪዎቻቸው ፈተና መስረቅ ጀምረዋል” የሚሉ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡
በተሽመደመደ ፖሊሲ ተምረው፣ ስማቸውን አስተካክለው መጻፍ የማይችሉ ተማሪዎችን ሲያመርት የነበረ፣ ራሱ የመከነ የመምህራን ሰራዊትና የትምህርት ባለሙያ እንዲሁም እነዚህን ሁሉ አጣምሮ በበላይነት የሚመራ ፖለቲከኛ ጭምር፣ ሀገሪቱን ወደ 22ኛው ክፍለ ዘመን ማሸጋገር የሚችል ትውልድ ማፍራት ይችላል ብሎ ማሰብ ራሱ ከንቱነት ነው ይላሉ፤ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ እና ምን ይደረግ?
የመፍትሄ ሃሳብ
ፈተና መሰረቅ በኛ ሀገር የተጀመረ ጉዳይ አይደለም፡፡ የፈተና ስርቆት ዓለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ በተለይም ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር የፈተና ስርቆት ተባብሷል፡፡ በቅርብ ዓመታት በህንድና በግብጽ ብሔራዊ ፈተናዎች በመሰረቃቸው ውጤት መሰረዛቸውን እናስታውሳለን፡፡
በሀገራችን ለፈተና መጭበርበር ዋነኛ ምክንያት ከሚባሉት ችግሮች አንዱ የፈተናው ባህሪ ነው:: ፈተናው ምርጫ መሆኑ ፈተናውን ለመኮራረጅ አመቺ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ስለሆነም ከፈተናው ውስጥ ቢያንስ አስር በመቶ (10%) የሚሆነው በጽሁፍ የሚመለስ (essay) እንዲሆን ቢደረግ፣ ጎበዝ ተማሪዎችን ከኮራጆች ለመለየት የሚያስችል መሆኑን በጉዳዩ ላይ ያነጋገርኳቸው የትምህርት ባለሙያዎችና ጎምቱ መምህራን ነግረውኛል፡፡ በእኛም ሀገር በአጼ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት፣ የ12ኛ ክፍል ፈተና (ማትሪክ) በጽሁፍ መልስ ይሰጥ እንደነበር ቀደም ካሉ የፈተና ወረቀቶች ላይ ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡ ይሄ የቀረው በደርግ የአስተዳደር ዘመን ነው፡፡ ይህንን የፈተና ዓይነት አስቸጋሪ የሚያደርገው ለማረም አስቸጋሪ መሆኑ ነው፡፡ ለማረም ጊዜና ጉልበት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ወጪንም ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከአእምሯዊና ከስነ-ልቦናዊ ክስረት፣ የገንዘብ ክስረትን መሸከም ይሻላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሁለተኛው መታየት የሚገባው ነገር ብሔራዊ ፈተናን የሚሰርቅ ማን ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እኔም ተማሪ ነበርኩ፡፡ ትንሽ ጊዜም አስተምሬያለሁ፡፡ እናም የተማሪን ባህሪ አውቃለሁ፡፡ በበኩሌ ተማሪዎች ፈተናን ይኮራረጃሉ እንጂ ፈተናን ከመንግስት ቢሮ ሰርቀው፣ መልሱን ሰርተው ያሰራጫሉ ብዬ ለማመን ሳይሆን ለማሰብ ይከብደኛል፡፡ ታዲያ ፈተናን ከመንግስት እጅ ፈልቅቆ የሚሰርቅ ማን ነው? መምህራን ናቸው? ትምህርት ቤቶች ናቸው? ርዕሰ መምህራን ናቸው? የትምህርት ቢሮዎች/የትምህርት ቤት ባለንብረቶች ናቸው? ወይስ ፖለቲከኞች? ይሄ በአግባቡ ተለይቶ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል:: ችግሩ እየተባባሰ ሳይሄድ የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይል ጭምር ተሳትፎበት ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
አንዳንድ ሀገሮች ስርቆት ሲያጋጥም ፈተናን ሙሉ በሙሉ ይሰርዛሉ፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ በከፊል መሰረዝ በመፍትሄነት ይወሰዳል፡፡ በእኛም ሀገር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ዘመን (በ2009) ፈተና መሰረቁ ታውቆ ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል፡፡ አሁን የተወሰደው መፍትሄ ግን ያጠፋውንም ያላጠፋውንም በጅምላ መቅጣት ሆኖ ነው የታየኝ፡፡ የተመረጡት አራት የትምህርት ዓይነቶችም ቢሆኑ ተማሪዎችን በሙያ አንጻር ለመመደብ ያስችላሉ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ህክምና የሚያጠናን ተማሪ በፊዚክስ ውጤት ብቻ መመደብ ተገቢ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ለህክምና ትምህርት የባዮሎጂና የኬሚስትሪ ውጤቶች እንጂ የፊዚክስ ውጤት አመላካች ሊሆን እንደማይችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በመጨረሻ አንድ ነገር ልበል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ለሀገራቸው በጎ ነገር ለመስራት እየጣሩ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን በዚህ በእርሳቸው የስልጣን ዘመን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠሩ አሳዝኗቸው ስልጣናቸውን መልቀቅ ነበረባቸው፡፡ እኔ ብሆን ይህንን አደርግ ነበር!
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሐፊውን ሃሳብ ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2112 times