Saturday, 14 September 2019 10:56

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች ዙሪያ ከጠ/ሚኒስትሩና ከክልል አመራሮች ጋር ውይይት ሲካሄድ ሰነበተ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከመንግስት ምላሽ በምትፈልግባቸው ጉዳዮች ላይ ከጠ/ሚኒስትሩና ከክልል አመራሮች ጋር ውይይት ሲካሄድ መሰንበቱን ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ ማህበራት አመራሮች ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱና አማኒያኑ እያጋጠሟቸው ባሉ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የአስተዳደር  አድሎአዊ መስተንግዶ፣ የአማኒያን መፈናቀልና ቤተ ክርስቲያናቱን የመከፋፈል ሴራ ጉዳይ ባለፈው ረቡዕ ላይ መወያየታቸው ታውቋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩም  ‹‹የት ቦታ ምን ተፈጠረ? እነማን ይመለከታቸዋል? የሚለውን መጀመሪያ ከክልል አመራሮች ጋር ውይይት አድርጉና ከዚያ በኋላ በደረሳችሁበት ጉዳይ ላይ በድጋሚ ውይይት እናደርጋለን›› ማለታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የማህበራት አመራሮቹም በትላንትናው ዕለት በቡድን በመከፋፈል ችግሮች ባጋጠሙ አካባቢዎች ካሉ አመራሮች ጋር በአካልና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ውይይት የጀመሩ ሲሆን ውይይቱ  ከድሬደዋ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ጋር እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በበኩሉ፤ የሲኖዶሱ አባላት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ከተወያዩ በኋላ ባወጣው ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ነው ያለውን አስተዳደራዊ አድሎና በደል አውግዞ አስተዳደራዊ በደል የሚፈጽሙ ባለሥልጣናት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያሳሰበ ሲሆን አለማቀፍ ማህበረሰብ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጎን ተሰልፎ ለመብቷ የምታደርገውን ትግል እንዲደግፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ መግለጫው፤ የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን ለመመስረት የሚንቀሳቀሱ አካላት ቤተ ክርስቲያኒቱን በመከፋፈል ሴራ በሕግ እንዲጠየቁ መወሰኑንም አስታውቋል፡፡

Read 8685 times