Saturday, 14 September 2019 10:52

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኦዴፓ ጋር የጀመሩት ውህደት መክሸፉን ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 ኦዴፓን ተጠያቂ አድርገው ከስሰዋል

          ከገዥው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጋር የጀመሩት የውህደት ድርድር መክሸፉን የገለፁት ሰባት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ‹‹ኦዴፓ የኦሮሞ ፓርቲዎች አንድ እንዳይሆኑ እያሴረ ነው›› ሲሉ ፓርቲውን ወንጅለዋል፡፡
የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ፣ የመላ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር፣ የኦሮሞ ብሄራዊ ነፃነት ፓርቲና የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ የተሰኙ ሰባት ፓርቲዎች ሰሞኑን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከኦዴፓ ጋር ለመዋሀድ ያደረጉት ድርድር መክሸፉን አስታውቀዋል፡፡ የውህደትና አብሮ የመስራት ድርድሩ ወቅት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰን ነበር ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ከሁለት ወራት ወዲህ ግን የኦዴፓ አመራሮች ከድርድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ጠቁመው፣ ኦዴፓ፣ የኦሮሞ ፓርቲዎች አንድ እንዲሆኑ እንደማይሻ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡
 አምስት ሺህ ወጣቶች የተሰውበት የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ያመጣው ለውጥ የኦሮሞን ሕዝብ ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም ያሉት ፓርቲዎቹ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ተመልሰው እየመጡ ነው ብለዋል -  በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች ሕገወጥ የመሬት ወረራ መንሰራፋቱንና ለሙስና በር ከፋች የሆኑ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑን በመጥቀስ፡፡
ከለውጡ እየተጠቀሙ ያሉት ገዥውን ፓርቲ የተጠጉ ካድሬዎች ብቻ ናቸው የሚሉት ፓርቲዎቹ፤ ‹‹ለውጡ በታቀደለት ደረጃ አልተጓዘም፣ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄም በአግባቡ እየተመለሰ አይደለም›› ሲሉም ትችት ሰንዝረዋል፡፡
ዛሬም በኦሮሚያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ አጥ መሆናቸውን በመጥቀስም መንግስት ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም ብለዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
ወለጋ፣ ባሌና ጉጂ ዞን በኮማንድ ፖስት ስር መሆናቸውንና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ስም አሁንም ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች መታሰራቸውን የጠቆሙት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ መንግስትን ጠይቀዋል።
ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የአፋን ኦሮሞ የፌዴራል የስራ ቋንቋ መሆንን ጨምሮ የአዲስ አበባ የወሰን ጉዳይ እልባት እንዲያገኝም ጥያቄ አቅርበዋል - ፓርቲዎቹ፡፡

Read 9363 times