Saturday, 14 September 2019 10:49

የኮትዲቯር ንጉስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን አባል ሆኑ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 ‹‹የአክሱም ታሪክ የኔም ታሪክ ነው››

        የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር አይቮሪኮስት ባህላዊ ንጉስ ቺፍ ዛዬ ጂያን፣ የኦርቶዶክስ እምነትን የተቀበሉ ሲሆን ከሰሞኑም በኢትዮጵያ ተገኝተው አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትን መጎብኘታቸው ተጠቁሟል፡፡
“በኢትዮጵያ መገኘታችን ትልቅ ፀጋ ነው” ብለዋል ንጉሱ - በጉብኝታቸው ወቅት፡፡ ከአመት በፊት በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን “ዴቪድ” ተብለው ክርስትና የተነሱት ንጉሡ፤ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ሥርዓትን ሲያከናውኑ የሰነበቱ ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኒቱም አባል ሆነዋል ተብሏል፡፡ ንጉሡና ልዑካናቸው በትግራይ ክልል የሚገኙ በርካታ ገዳማትን ጐብኝተው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውም ታውቋል፡፡
ንጉሡና ባለሟሎቻቸው ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፤ ለአፍሪካ ነፃነት አርማ የሆነች፣ የሰው ልጆችን ነፃነት የምታውጅ ቤተ ክርስቲያን ነች›› ሲሉም ምስክርነታቸውን ሰተጥዋል፡፡
ንጉሡ የአፍሪካ ባህላዊ ንጉሦች ህብረት መሪ ሲሆኑ ከሰሞኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትም  የኮንጐ፣ ቱኒዝያ፣ ናይጀሪያ፣ ኡጋንዳና ግብፅ ባህላዊ ነገስታትን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነገስታትን ይዘው እንደመጡ ታውቋል፡፡
በኮትዲቯር እስካሁን የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ እንደሌለ የጠቆመው የአለም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ህብረት በበኩሉ፤ ንጉሡና ባለሟሎቻቸው የመጀመሪያዎቹ ኮትዲቯራውያን ኦርቶዶክሶች ይሆናሉ ብሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን በስፋት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ እየሆኑ መምጣታቸውን ህብረቱ በድረ ገፁ ላይ ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ ጥቁር ህዝብ የነፃነት ተምሣሌትነት እንደምትቆጠርም ተገልጿል፡፡
ንጉሡና ልኡካናቸው አክሱም ከተማ ሲደርሱ የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገላቸው አቀባበል መደነቃቸውን በመግለጽም፤ “ኢትዮጵያ የተባረከች ሀገር ናት፣ በኢትዮጵያ መገኘታችን ትልቅ ፀጋ ነው” ብለዋል፡፡
“አክሱም የኢትዮጵያ ነገስታት መንበርና የንግስና መቀበያ ናት” ያሉት ንጉሡ፤ ‹‹የአክሱም ታሪክ የኔም ታሪክ ነው›› ብለዋል፡፡   

Read 9015 times