Print this page
Saturday, 14 September 2019 10:45

ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የተናጠል ውይይት አደረጉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ግድቡ በ7 አመት ጊዜ ውስጥ በውሃ እንዲሞላ ግብጽ ጠይቃለች

          አዲሱ የሱዳን የሽግግር መንግስትና የግብጽ መንግስት የመጀመሪያ ውይይታቸውን በኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ አድርገው የተናጠል ውይይት ማካሄዳቸውን የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል፡፡
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ማኒስትር ሣሜ ሹክሪ እና የሱዳኑ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላህ ሃምዶክ እንዲሁም የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አስማ መሃመድ አብዱላህ ባለፈው ማክሰኞ  በካርቱም የመጀመሪያ የተናጠል ውይይታቸውን አድርገዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የአባይ ግድብን አጀንዳቸው አድርገው መወያየታቸውን የዘገበው አናዶሉ፤ ስለ ውይይታቸው ፍሬ ሃሳብ ግን የታወቀ ነገር የለም ብሏል፡፡ ግብጽ በተደጋጋሚ በህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ላይ ቅሬታ እያቀረበች ሲሆን፤ ይህ ጉዳይ  የሱዳንና የግብጽ ባለስልጣናት የውይይት አጀንዳ ሳይሆን እንደማይቀርም ተጠቁሟል፡፡
ግብጽ ከሣምንት በፊት ለኢትዮጵያ ባቀረበችው ጥያቄ፣ ግድቡን በውሃ የመሙላት ሂደት በ7 አመት ጊዜ ውስጥ እንዲከናወን መጠየቋ የሚታወቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ግድቡን ከ5 እስከ 6 አመታት ጊዜ ውስጥ በውሃ የመሙላት እቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡
ግድቡን በውሃ የመሙላት ሂደቱ የግብጽን የአባይ ውሃ ድርሻ በሁለት በመቶ ይቀንሰዋል ያሉት የግብፁ የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትር፤ ይህም 2 መቶ ሺህ ሄክታር መሬትን ወደ በረሃማነት ይቀይርብናል ሲሉ አማረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም አለማቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ግፊት እንዲያደርግ ግብጽ እያግባባች ነው ተብሏል፡፡

Read 1490 times