Saturday, 14 September 2019 10:27

እያንዳንዱ ሩዝ ላይ የሚበላው ሰው ስም ተጽፏል

Written by 
Rate this item
(12 votes)


            አንድ እጅግ ጉረኛ ሰው  ነበር፡፡ ድንገት ይመጣና ‹‹አሥራ ስድስት ቀበሮዎች አግኝቼ አንድ ላይ፣ በአንድ ጥይት ሰፋኋቸው! በጣም አስገራሚ ገድል ነው የፈፀምኩት›› አለ፡፡
‹‹እንዴት ሊሆን ቻለ?›› አሉት፡፡
‹‹እንዴ?! የዚያን ጊዜ ተዓምር በቃላት አይፈታም››
ማሰብ ይጠይቃል፡፡ እንደው ላይ ላዩን አይተን ብቻ በመሀይም ልቦና ጉዳዩ ውስጥ እንግባበት ብንል ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው፡፡
ምንም ማስረጃ ሳያስፈልግ ለአገር መመስከር እንችላለን፤ ሕዝቦች ነንና!!
ይኸው ጉረኛ መንገድ ላይ ሰው አገኘና፡-
‹‹ከየት ትምጣለህ?›› አለው
‹‹አሥራ ስድስት ቀበሮዎች ሰፍቼ››
‹‹የት?››
‹‹ጫካ››
‹‹ጀግና ነህ! አንበሳ ነህ!››
‹‹ጀግንነቴ አስደማሚ አይደለም?››
‹‹እኔን ያስደመመኝ ያንተ ጀግንነት አይደለም››
‹‹ሌላ ምኑ ነው ታዲያ ያስደመመህ?›› አለው፡፡
‹‹የአገርህ ቀበሮዎች አሰላለፍ!!››
 *  *   *
ለማንኛውም ከጥሩ ማስተዋል ጋር አሰላለፍን ማሳመር መታደል ነው!
ገጣሚውና ፀሐፌ - ተውኔቱ መንግሥቱ ለማ፡-
ቀማኛን መቀማት
  ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ
   የድሆችን ጭንቅ
በእኔ ቤት ፅድቅ ነው
አንድ ሰው ይሙት!!
አንድ መቶ ሺህ ሰው ሲኖር በምጽዋት!››… ብለዋል፡፡
ይህ ፍንትው ያለ ዕውነት ነው!!
‹‹ውሸት ዓለምን ዞሮ ሲጨርስ፣ ዕውነት ቦት ጫማውን አስሮ አይጨርስም›› ይላሉ አበው፡፡
‹‹ጓደኛሞች መጠጥ ቤት ይገናኙና፤
‹‹የት ጠፋህ›› አለ አንዱ አንደኛውን
‹‹እንደው ባንተያይ ነው እንጂ እኔ እንኳን አለሁ››
‹‹የደበቅኸኝ ነገር አለ እንጂ እዚሁ አዲሳባ እየኖርን ልንጠፋፋ አንችልም››
‹‹ምንም የደበቅሁህ ነገር አይኖርም፤ ግን ለአንድ ለስድስት ወር አሥረውኝ ነበር››
‹‹ምን አርገህ ብለው ነው?››
‹‹አንድ ኮርቻ ሰረቅህ ብለው ነው››
‹‹ለኮርቻ ስድስት ወር?››
‹‹ምን እባክህ ከኮርቻቸው ሥር አንዲት የማትረባ በቅሎ ነበረች››
ዋናውንና ምንዛሪውን ካልለየን አለመታመን የግድ ይመጣል፡፡ የግድ ተዓማኒ ለመሆን ማንነትን ማጥራት ዋና ጉዳይ ነው፡፡
ማንነት ደግሞ፤
የቀናነት
የሀቀኝነት
የፍቅር
የተስፈኝነት
የዕውቀት
ሁሉም የመልካም አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡
እነዚህን ሁሉ አንድ ሰው ሆድ ውስጥ ማጠራቀም ብርቱ ጥረት ይጠይቃል፤ ከልባችን እንታገል!!
ካመረርን፣ መንገዳችን ሩቅና መራራ መሆኑን ከልብ ካመንን የማናቸንፍበት አንዳችም ምክንያት የለም!!
መልካም የፍቅር ዓመት ያድርግልን!!

Read 9965 times