Print this page
Monday, 09 September 2019 11:28

‹‹እንደራሴ›› - ዩኒቨርስቲ የሚገቡ የመንግስት ት/ቤት ተማሪዎች የመሸኛ ሥነ ሥርዓት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

በእውቋ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ የተቋቋመው ‹‹ላይድመንሽ መልቲ ሚዲያ›› ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር፣ የመንግሥት ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄድ የመዝናኛ ዝግጅት፣ ወደ የተመደቡበት ዩኒቨርሲቲዎች ለመሸኘት እየሰራ ይገኛል፡፡ ለመሆኑ የሽኝት ፕሮግራሙ እንዴት ታሰበ? ለምን አስፈለገ? ምንስ ፋይዳ አለው? “የላይድመንሽ መልቲ
ሚዲያ” ባለቤት ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ፣ በፕሮግራሙ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር እንደሚከተለው አውግታለች፡፡


             እስቲ መስከረም 11 ለማካሄድ ስላቀዳችሁት ዝግጅት አጫውቺኝ…?
ጥሩ! እኛ በፖየቲክ ጃዝ አማካኝነት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መልካም ዜጋ እንዲሆኑ፣ አገራቸውን እንዲወድዱ፣ እጅግ አስፈላጊ ዜጎች መሆናቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ በ45ቱም ዩኒቨርሲቲዎች እየዞርን በኪነ ጥበባዊ መንገድ ተማሪውን ለማነጽ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ እስካሁንም በአዲስ አበባና በወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ይህንን ተግባራዊ አድርገናል። በቀጣዩ ዓመት (2012 ዓ.ም) ደግሞ በ43ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጉዟችንን እንቀጥላለን፡፡
በላይድመንሽ መልቲ ሚዲያ የመጣው ሀሳብ ደግሞ በተለይ የመንግስት ት/ቤት ተማሪዎች ወደ የሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ከመሄዳቸውና አዲሱን ዓለም ከመቀላቀላቸው በፊት ለምን መርቀን አንሸኛቸውም የሚል ነው፡፡ እንደሚታወቀው፣ የግል ት/ቤት ተማሪዎች እጅግ ቅንጡ በሆነ መልኩ በቅንጡ ሆቴል፣ ብዙ ብር ወጥቶበት የ12ኛ ክፍል ፈተናን እንዳጠናቀቁ፣ ደግሰው ምርቃት ያዘጋጃሉ:: የመንግስት ት/ቤት ተማሪዎች ግን ይሄ ልምድ የላቸውም፣ ኖሯቸውም አያውቅም፡፡ አገር ግን ሁለቱንም ትፈልጋለች፡፡ ለሁለቱም እኩል ናት:: እንደውም ከተመረቁም በኋላ ከባድ ሀላፊነት ያለባቸው እነዚህ የመንግስት ት/ቤት ተማሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ለአገር እኩል ስለሆኑ ለምን አንመርቃቸውም፣ በሀገር ሽማግሌዎች በሀይማኖት አባቶች መርቀን ለምን አንልካቸውም፣ ወደ አዲስ አካባቢ ስለምንልካቸው ለምን ስንቅ አስታጥቀን አይሄዱም በሚል ነው የታሰበው፡፡ በዝግጅቱ ላይ ስለ አገራቸው በዲስኩር ይነገራቸዋል። በሚሄዱበት አዲስ አለም ስለሚጠብቃቸው ፈተናና ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ ይነገራቸዋል፡፡ “እናንተ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በድል አጠናቅቃችኋል፤ ጎበዞች ናችሁ፤ ለቀጣዩ ጉዟችሁ በርቱ” ብሎ የመላክ ሀሳብ ነው፡፡
እግረ መንገዳቸውን ደግሞ እስከ ዛሬ ትምህርትና ጥናት ላይ ነበሩ፤ ተዝናንተው ከጓደኞቻቸው ጋር ተደስተው፣ አዲሱን አመት በአዲስ መንፈስ ተቀብለው ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ለሚቀሩት ደግሞ የግል ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆችን አነጋግረንላቸዋል፡፡ የትምህርት ዕድል እንዲመቻችላቸው እየተሞከረ ነው፡፡ ጥሩ ውጤት ያመጡትን እንዲሁ ነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ እየጣርን ነው፤ ከተሳካልን ማለቴ ነው፡፡ በዚህ አይነት መንገድ ቀጣይነት ኖሮት፣ በየአመቱ የሚካሄድ የመሸኛ ፕሮግራም ይሆናል ማለት ነው፡፡
እንግዲህ በየመንግስት ት/ቤቱ የሚማሩ ያሉት በመላ አገሪቱ ነው፡፡ እናንተ ተደራሽ ግን  የአዲስ አበባዎቹ ብቻ ነው…?
ይሄ ነገር የግድ ከአንድ ቦታ መጀመር አለበት:: እኛም ለጊዜው አዲስ አበባ ላይ ነው ማዘጋጀት የምንችለው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ከዚህ የሚሸኙት እዚያ ተቀባይ አላቸው፡፡ ከሌላው አካባቢ የሚሸኙትን እዚህ ጥሩ ተቀባይ እንዲኖር ማስቻል ነው አላማው፡፡ እዚህ ተጀምሮ በሌላውም አካባቢ ተመሳሳይ ሽኝት እየተደረገላቸው፣ ወደየ ምድባቸው ቢሄዱ ጥሩ  ነው ባይ ነኝ፡፡ እኛ ግን ያው አዲስ አበባ ላይ ነው የምንጀምረው፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ሀሳቡን  በሙሉ ልብ ተቀብሎታል?
ስራውን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ነው የምንሰራው፡፡ እኛ ይህን ፕሮግራም ‹‹እንደራሴ›› ብለን ስንሰይመው፣ ተማሪዎቹ እንደራስ እንዲያስቡ ነው፡፡ ኢንጂነር ሲሆኑ በሙያቸው ለአገራቸው ለወገናቸው እንደራሳቸው እንዲሰሩ፣ ሀኪምም ሲሆኑ እንደራሳቸው እንዲያክሙ… እንደ ራስ ብለው እንዲሰሩ ነው፡፡ እንደራሴ ማለት አምባሳደር ማለት ነው፤ ተጠሪ ማለትም ነው፡፡ ስለዚህ ለአካባቢያቸው ለአገራቸው አምባሳደርም ተጠሪም እንዲሆኑ ነው:: መጠሪያውም በዚህ መልኩ የታሰበው፡፡ ከተማዋ እንደራሴ (ተጠሪ) አላት፡፡ ተጠሪዎቹ በየጊዜው ይቀያየራሉ፤ ነገር ግን ይህ ፕሮግራም በየጊዜው ይቀጥላል፡፡  ስለዚህ አሁን ያሉት የከተማዋ ተጠሪም የሚሸኙት ተማሪዎች ልጆቻቸው ናቸው:: መርቀው ይሸኟቸዋል፡፡ በዚህ አግባብ ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን አነጋግረናቸው፣ ፕሮግራሙን በቅንነት ተቀብለውን፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር እየሰራን ነው። ለተማሪዎቹ ብዙ ነገር አዘጋጅተውላቸዋል፡፡
ለምሳሌ ምን አዘጋጁላቸው?
ተማሪዎቹ ተዝናንተው ማታ ሲመለሱ እንዳይንገላቱ ትራንስፖርት አቅርበውላቸዋል:: ፕሮግራሙ ከ8፡00 እስከ 12፡00 ነው የሚቆየው፡፡ ጨርሰው ሲወጡ 40 መኪናዎች ተዘጋጅተውላቸዋል:: ያለምንም ችግር ወደ የቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ይሄ አንዱ ነው::  በፕሮግራሙ ላይ ስናክና ለስላሳ መጠጦች ተዘጋጅተዋል፡፡ እነ ቤቲ ጂ.፣ ልጅ ሚካኤል፣ መሃሪ ብራዘርስ ባንድና መሶብ ባንድ በሙዚቃ ያዝናኑዋቸዋል፡፡ ሽለላና ፉከራ ሁሉ ለመዝናኛነት ተሰናድቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆቹም እዚያው ስለሚኖሩ፣ እዚህ የሚቀሩት የትኛው ይሻለኛል ብለው የመምረጥ ሰፊ አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል:: ለዕድሜያቸው  የሚሆኑና የሚመጥናቸውና ሙዚቃዎች የሚያጫውትላቸው ዲጄም ይኖራል:: ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ይወዳደራሉ፡፡ አሸናፊዎች ስማርት ስልኮችን ይሸለማሉ፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ምን ያህል ተማሪዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል?
በአዲስ አበባ የ12ኛ ክፍል ፈተናን የወሰዱት 21 ሺህ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ለሁሉም ጥሪ እያደረግን ነው። የሞላላቸው የተመቻቸው ሁሉ ቢመጡ ደስ ይለናል፡፡
ይሄ ትልቅ ድግስ ይመስለኛልና ትልቅ በጀትም የሚጠይቅ ነው፡፡ እንዴት ነው ወጪውን የምትሸፍኑት?
መልካም! የዚህን ፕሮግራም አጠቃላይ ወጪ የሸፈነው ከተማ አስተዳደሩ ነው። ከዚያ በተረፈ የለስላሳ መጠጦችን ፔፕሲና ንጉስ ስፖንሰር አድርገውናል፡፡ በዚህ መልኩ ነው ወጪው የተሸፈነው፡፡
ይሄ ሀሳብ እንዴት መጣላችሁ?
አንድ ቦታ ለምረቃ በሄድኩበት ጊዜ ነው ያሰብኩት::  እኔ 12ኛ ክፍልን ስፈተን አልተመረቅኩም:: እኔም የመንግስት ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡ በኛም ጊዜ ምረቃ የለም፡፡ አሰብኩት፡፡ ለካ ብዙ የመንግስት ት/ቤት ተማሪ ይህ አልተደረገለትም፤ ግን ሊደረግለት ይገባል በሚል ነው ያሰብኩት። ከተማ አስተዳደሩ በበጎ ተቀብሎታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ፣ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ ደማቅ የመሸኛና የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ሁሉም የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንዲታደምና የማይረሳ ጊዜ እንዲያሳልፍ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
በጦቢያ ‹‹ግጥም በጃዝ›› ለተማሪው ኢትዮጵያዊነትን ለማስረጽና ሀላፊነት የሚሰማው ዜጋ ለመፍጠር በሁሉም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ኪነ ጥበባዊ ዝግጅት ለማቅረብ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ላይ ደርሳችሁ ነበር፡፡ እንዴት እየሄደ ነው?
መልካም፡፡ እንዳልሽው ነው፡፡ በአዲስ አበባና በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ተግባራዊ ካደረግን በኋላ ክረምቱም መጣ፡፡ አገሪቱም ላይ ተከስቶ የነበረው ችግር እንቅስቃሴያችንን ገታ አድርጎት ነበር፡፡ በአዲሱ አመት እንቀጥለዋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ እኛን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ዩኒቨርስቲ እንዲጠራንና የጀመርነውን እንድንቀጥል ለዩኒቨርሲቲዎቻችን ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡


Read 1871 times