Monday, 09 September 2019 11:19

ይድረስ ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን፤ “እስቲ እንረዳዳ!”

Written by  አክሊሉ ኪዳኑ ወልደ ጊዩርጊስ
Rate this item
(2 votes)

አሁን ሀገራችን ከገጠሟት በርካታ አንገብጋቢ ጉዳዮች አንዱ ህግን የማስከበር ችግር ነው፡፡ ከትናንሾቹ ጀምሮ እስከ ትላልቆቹ የሀገር ጉዳዮች ድረስ ይህ ችግር በተለያየ መልኩ ሲከሰት ይታያል:: በትንሹ የህግ ማስከበር ስራ ቢጀመርና ከተሳካ ልምዱን ይዞ ወደ ትላልቆቹ መሄድ ይቻላል፡፡
ስለዚህ በትንሹ እንጀምርና የአዲስ አበባን የእግር መንገዶች እንመልከት፡፡ በእርግጥ 90 በመቶ (ወይም 4 ሚሊዮን) የሚገመተው የአዲስ አበባ ነዋሪ እግረኛ ከመሆኑ አኳያ ሲታይ ይህ እምብዛም ትንሽ የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ለሁሉም ብቻ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ካሉበት ብዙ ሀላፊነት አንዱ፤ ለአደጋ ያልተጋለጠና አመቺ የእግር መንገድ ለሁሉም የከተማ ነዋሪዎች የማዳረስ ራእይ ነው፡፡ ይህ የሚደገፍና የሚበረታታ ቢሆንም፣ ይህን ራዕይ በስራ ላይ ለማዋል አንዳንድ ችግሮች እንዳሉበት ግን ይስተዋላል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት የህዝብ ገንዘብ በማውጣት የተቻለውን ያህል የእግር መንገዶችን ለመስራት እንደሚጣጣር ይታያል፡፡ ለምሳሌ አሁን በቅርቡ የተጠናቀቀው ከመስቀል አደባባይ እስከ ስድስት ኪሎ ያለው የእግር መንገድ በጥሩ ሁኔታ ተሰርቷል፡፡ የከተማው ነዋሪዎችም በስነስርአት ሲገለገሉበት ይታያሉ:: ሌሎችም በተመሳሳይ የተሰሩ አሉ፡፡ ለዚህም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መመስገን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የእግር መንገዶች ተገቢው ጥበቃና መከላከል እንዲኖራቸው የህግ ማስከበር ስራ እየተሰራ ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ የግድ ነው፡፡
እንደሚታየው ከሆነ፤ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ የእግር መንገዶች በቀላሉ በሚወላልቅ ሴራሚክስ ስለሚሰሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይወላልቃሉ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አንዴ እንጨት ሲፈለጥባቸው፤ አንዴ ጎሚስታ ሲቀየርባቸው፤ አንዴ ሲሚንቶና ጠጠር ሲራገፍባቸው፤ አንዴ መኪና ሲታጠብባቸው፤ አንዴ መብራት ሀይል ትላልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ ጥሎ ሲሄድ፤ ከፍተኛ የህዝብ ገንዘብ ባክኖ ይቀራል፡፡ እግረኞችም ወደ መኪና መንገድ በመሄድ ለአደጋ ይጋለጣሉ ማለት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ  ህግ የማስከበር ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ፤ እግረኞች እንዲጠቀሙባቸው ተብለው የሚሰሩ ሌሎች ስራዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን አውቶቡስ ለሚጠብቁ ሰዎች በሚል የተሰሩ መጠለያዎች በእግር መንገዶቹ ላይ እየታዩ ነው፡፡ በጣም ብዙ ገንዘብ እንደወጣባቸውም ያስታውቃሉ፡፡  ሀሳቡም የሚደገፍ ነው፡፡ ጠጋ ብላችሁ ብትመለከቷቸው ግን ለዘለቄታው እንዲቆዩ ሆነው የተሰሩ አይመስልም፡፡ መጠለያዎቹ ያረፉበት ቦታ ሴራሚክሱ ተፈነቃቅሎ እንደ ቁሻሻ ተከምሯል:: አንዳንድ መጠለያዎች ደግሞ ተገነጣጥለው የቁሻሻ ማጠራቀሚያና ራሳቸውም ቆሻሻ ሆነዋል፡፡  ከትንሽ ጊዜ በኋላም ወላልቀው እንደሚወድቁ ግልጥ ነው፡፡
ሌላ ምሳሌ፤ በየእግር መንገዱ ለቆሻሻ ማጠራቀሚያ ተብለው የተቀመጡ በእንጨት የተሰሩ ሳጥን የሚመሳስሉ ነገሮች ይታዩ ነበር፡፡  አሁን ግን ተሰባብረው ራሳቸው መነሳት ያለባቸው ቆሻሻ ሆነዋል፡፡ ብዙ የህዝብ ገንዘብ መውጣቱ አንሶ አሁን ደግሞ እነሱን አንስቶ መጣሉ ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ሊያስወጣ ነው ማለት ነው፡፡  አንድ ሰሞን ደግሞ የመንገድ ስምና ቁጥር የሚመስሉ በሰማያዊና በነጭ ቀለም የተጻፉ የብረት ምልከቶች በየመንደሩ በሰፊው ተተክለው ይገኙ ነበር፡፡ አሁን አብዛኞቹ ምልክቶች ተነቃቅለው ወድቀው መነሳት ያለባቸው ቆሻሻ ሆነዋል፡፡ የባከነው የህዝብ ሃብት ከፍተኛ መሆኑን መገመት ግን ለማንም አዳጋች አይሆንም፡፡
በአጭሩ፤ የእግር መንገዶችና ተጓዳኝ ስራዎች ብዙ የህዝብ ገንዘብ ወጥቶባቸው መሰራት ይጀምራሉ፡፡ በደንብ ተጠናቀው ሳያልቁ ስራ ላይ ይውሉና የመጠበቅና የመከላከል ስራ ስለማይኖር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወላልቀው ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ፡፡ እግረኞችም ወደ መኪና መንገድ ይገቡና ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ ገንዘብም ሕይወትም በከንቱ ይጠፋል፡፡  የከተማዋ ታክስ ከፋይም ለምን ታክስ እንደሚከፍል ግራ ይገባዋል፡፡ በእርግጥ በዋነኝነት ሀላፊነቱ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቢሆንም፤ ከአቅሙ በላይ ከሆነበት፤ እኛም ተጠቃሚ የሆንነው የከተማው ነዋሪዎች ሀላፊነታችንን መወጣት መረባረብ ይኖርብናል፡፡
እንግዲህ የመቆርቆር፤ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፤ ለወደፊት ተመሳሳይ ብክነት ከመድረሱ በፊት እስቲ እንረዳዳ! በኔ ግምት ቢያንስ በሶስት መንገድ መረዳዳት እንችላለን፡፡  
አንደኛ፤  መመካከር!  ስራዎቹ ከመሰራታቸው በፊት መመካከርና የሌሎች ሀገር ከተሞችን ተመክሮ መመልከት ነው፡፡ ለምሳሌ የእግር መንገዶቹ በሚፈራርስ ሴራሚክስ ከሚሰሩ በብዙ የውጭ ሀገር ከተሞች እንደሚታየው ሁሉ አንደኛውን ሊሾ ቢሆኑስ? ወጪው ከመቀነሱም በላይ ቶሎ ቶሎ አይበላሹም፤ ከተበላሹም ለጥገናም ይቀላል:: ነዋሪውም የእግር መንገዱን ይዞ በሰላም ይጓዛል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ነዋሪው ምን እንደሆኑ እንኳ የማያውቃቸው ምልክቶች በብዙ ወጭ ከመተከላቸው በፊት ስለ ጠቀሜታቸውም ሆነ ስለ አስፈላጊነታቸው መመካከሩ አይከፋም፡፡ በሌለ ገንዘብ ብክነትን ያድናልና፡፡
ሁለተኛ፤  መተጋገዝ!  የእግር መንገዶች ጥቅም ለእግረኞች ብቻ አይደለም፡፡ በአካባቢው ላሉ ሆቴሎች፤ ምግብ ቤቶች፤ ሱቆች፤ ባንኮችና  ለመሳሰሉ የንግድ ተቋማት ጥሩ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የከተማው ነዋሪዎችም ሆኑ ለስብሰባ ወይም ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ ሀገር ሰዎች በሰላምና በነጻነት ከአንድ የንግድ ተቋም ወደ ሌላው በመዘዋወር ገንዘባቸውን ለማጥፋት ያመቻቸዋል:: የከተማው አስተዳደርም ከታክስ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ይችላል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ከኤድናሞል አደባባይ እስከ ቦሌ መንገድ ያሉት የእግር መንገዶች በስነስርአት ተሰርተው  ቢያዙ ምን ያህል ለከተማዋ ውበትና ለንግድ ተቋሟቱ ጥቅም ማምጣት እንደሚችሉ መገመት አዳጋች አይደለም፡፡ ከትዝብትም ያድናል፡፡ ስለዚህ የንግድ ተቋሟቱ ባለቤቶችና የመንገድ ባለስልጣኑ መስሪያ ቤት  በመተጋገዝ መስራት አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ በከተማው ያሉ የእግር መንገዶች በጥሩ ሁኔታ ቢያዙ፣ ለሁሉም የገቢ ምንጭ ሊሆኑ  ይችላሉ ማለት ነው፡፡
ሶስተኛ፤  ህግን ማስከበር!  ከዚህ አኳያ ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ መቼስ ህጎች ይኖራሉ፡፡ በትምህርትም ሆነ በቅጣት እነዚህ ህጎች መከበር አለባቸው፡፡ እኔ እንደታዘብኩት ከሆነ፣ የከተማው ነዋሪ በመሰረቱ ህግ አክባሪ ነው፡፡ ግን መሪ ይፈልጋል፡፡ የተበላሸ ነገር ሲያይ የበለጠ ያበላሻል፡፡ የፀዳ ነገር ሲያይ ደግሞ  በፅዳት ይይዘዋል፡፡ ስለዚህ ዋናው የመሪነት ስራ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሆኖ፤ በከተማው ነዋሪዎች፤ በህግ አስከባሪዎችና በንግድ ተቋሟት ባለቤቶች ትብብር ሊከናወን ይችላል:: ለምሳሌ የአንድን አካባቢ የህግ ማስከበር ስራ በተሸከርካሪ እየተዘዋወሩ ቋሚ ክትትል የሚያደርጉና አስፈላጊ ከሆነም መቅጣት የሚችሉ ሰዎች ከበቂ ደሞዝ ጋር መመደብ ይቻላል፤እነሱንም  ቢሆን የሚቆጣጠር ሰው ያስፈልግ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ይህ ወጪ ያስወጣል፤ ጥቅሙ ግን ይበልጣል፡፡ በሌሎች ተመሳሳይ ከተሞች ይደረጋል፤  ውጤታማም ነው!
ስለዚህ አንፃራዊም ቢሆን፤ ማንኛውም  ነገር ከትንሹ ይጀምራል፡፡  የከተማ የእግር መንገዶችን ከብልሽት የመከላከልና የመጠበቅን ህግ በስራ ላይ የማዋል ባህልን ካዳበርን፤  ትላልቆቹ የሀገር ጉዳዮች ላይ ስናተኩር ሊቀለን ይችላል ማለት ነው፡፡ በትልቁ አስቡ፤ በትንሹ  ጀምሩ፤ ግን አሁኑኑ!! እንደሚባለው ነው፡፡
በመጨረሻ፤ በሌሎች ትላልቅ ከተሞች እንደሚደረገው ሁሉ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉትን ታሪካዊ ቦታዎችን፤ ቤተ መንግስቶችን፤ ሙዚየሞችን፤ አለም አቀፍ ድርጅቶችን፤ የሀይማኖትና የትምህርት ተቋማትንና የገበያ ቦታዎችን የሚያሳይ  የአውቶቡስ ጉብኝት ቢዘጋጅ፣ የኋላ ኋላ ጥቅሙ ለከተማችን ብዙ ነው፡፡ ይህ ከዚህ በፊት ተጀምሮ የተቋረጠ ቢሆንም፣ እንደገና በአዲስ መልክ ሊጀመር ይችላል:: በእርግጥ እቅድና ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ግን ይህንንም ቢሆን በትንሹ ጀምረን ልናሳድገው እንችላለን፡፡ እኔም አንዳንድ ሀሳቦች ስላሉኝ ጉዳዩ ይመለከተኛል ከሚል ሰው ወይም ተቋም ጋር ተገናኝቶ ለመመካከር ፍቃደኛ ነኝ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Read 1676 times