Saturday, 16 June 2012 09:34

ሁዳድ

Written by  ቦንቦሊኖ
Rate this item
(0 votes)

“ይሄማ የህፃን ልጅ ጨዋታ ማለት እኮ ነው! የጀግኖች ተግባር ግን በትክክለኛው ጦር ነው፤ ለዚህ ደግሞ የሚስተካከለኝ የለምና ከሃበሻ ውስጥ የሚሞክረኝ ካለ ዝግጁ ነኝ”በአካባቢው አየር ላይ ምላጭ ይነፍሳል፡፡ ገላ ላይ ስውር ሰንበር ጠሎ የሚያልፍ፡፡ የቀኑ ራስ የሚያስት ሃሩር ከማለፈ ወዲያው ቆዳ የሚያኮማትር ሃይለኛ ብርድ በቦታው ተተክቷል፡፡ ሰፊው አውራ ጐዳና ከውርጩ ለማምለጥ በሚጣደፉ ሰዎች ተሞልቲል፡፡ከአንድ ግሮሰሪ ደጃፍ ላይ ተቀምጫለሁ፡፡ ልቤ ላይ የሚነደውን የቁጣ እሳት በቀዝቃዛ ድራፍት ለማብረድ እየሞከርኩ አለም በአምባ-ገነኖች አለም በጨካኞች ስለመሞላቷ እያሰብኩ፡፡

አከራዬ ምን አንደሰቡ አላውቅም፤ ባልተዘጋጀሁበት ሁኔታ ቤታቸውን እንድለቅ አዘውኛል፡፡ ምክንያት መስጠትም ሆነ መስማት አልፈለጉም፡፡ ጌታ በባርያው ላይ ፈፅሞ እንደሆነው እንዲሁም አከራይም በተከራዩ ላይ ስዩም ነው፡፡ድህነት ማለት ከፍላጐት በታች መኖር ማለት ነው፡ ደሀ መሆን ከሰው ክብር በታች መውረድ ነው፡፡ ደሀ ስንኩል ነው፡፡ ደሀ ድንጉጥ ነው፡፡ አሁን ገና የሚከራይ ቤት ያያችሁ? ልል ነው…ደላላ፣ እቃ መጫን እቃ መጫን እቃ ማውረድ፤ አዲስ ንጉስ መልመድ… ትርምስ ነው….ሲኦል…“አስብ እንድታብብ” የሚል ንግግር ከገባሁበት ሃሳብ መለሰኝ፡፡ ወዳጄ አለማየሁ ሰፌድ የሚያህል መዳፉን ዘርግቶ ቆሟል፡፡ ጨበጥኩትና ከጐኔ ተቀመጠ፡፡ በአይኑ አስተናጋጅ እያደነ “ምነው የአለምን መከራ ለብቻህ የተሸከምክ ትመስላለህ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡በተቃውሞ እጄን እያወናጨፍኩ “መከራ የሚባል መንፈስ የለም፤ የአንዳችን መከራ የሚዘጋጀው በሌላኛችን ነው፤ ህይወትን በጋሬጣ የሞላትም መጠላላታችን ነው፤ እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ ሃበሻ ራሱን ላለመኮነን “ሰው ነው ለሰው መድሃኒቱ” ይላል የመረዘው እኮ ራሱ ነው!” አልኩ፡፡
የመጣለትን ድራፍት በአንድ ትንፋሽ ካጋመሰ በኋላ “በከፊል ልክ ነህ፤ ግን ምንድን ነው በትክክል የገጠመህ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡“አከራዬ ቤቱን በቶሎ እንድለቅ አዘውኛል፡፡ አሁን አሁን የመሰደድ የመጠቃት ስሜት እየተሰማኝ ነው፡፡ ሰው እንዴት በገዛ ሀገሩ መጠለያ ያጣል? በደም መስዋዕትነት ከባዕድ ወረራ የተጠበቀው መሬት እንዴት ለዜጐች አልብቃቃ አለ? እንዴ! እሱ ቢቀር በገዛ ሀገሬ ገንዘቤን ከፍዬ ለመኖር ለምን ባርያ መሆን ይጠበቅብኛል?” ጥፋተኛው እሱ ይመስል አፈጠጥኩበት፡፡ለረጅም ጊዜ ትክ ብሎ ከተመለከተኝ በኋላ “በእርግጥ በየዘመኑ የነበረው የአገዛዝ ስርዓት ህዝቡ ፍትሃዊ የመሬት ክፍፍል እንዳይኖረው አድርጐታል፡፡ ከንጉሱ ጀምሮ እስከ አሁን እንኳ ብትመለከት አገዛዞቹ ከሚቆምሩባቸው የሃገር ሃብቶች መሃል ዋነኛው መሬት ነው” የቀረችዋን ጨልጦ በአይኑ አስተናጋጅ መፈለግ ጀመረ፡፡(ይህን ጓደኛዬን ለምን እወደዋለሁ? አዎ ስለ ብዙ ነገር መጨዋወት ይችላል፤ የንባብ ቁራኛ ነው፡፡ ለዚህ ሰው ንባብ ከመሰረታዊ ነገሮች ውስጥ ይመደባል፡፡ እናማ ከሞላ ጐደል ሙሉ ሰው ነው፡፡)“ታዲያስ ልክ ነህ! ይሄ ሰውዬ ይሄን የሚያህል መሬት (ሰፈር ብለው ይቀላል) ከአፄ ሚኒልክ በስጦታ አይደል እንዴ ያገኘው!?” አልኩ፡፡“ልክ ነው፤ ግን አግባብ ያለው ስጦታ ነው፤ ስለ ሃገር ክብር ስለ ሃገር ስም መጠበቅ ለተከፈለ ጀግንነት የተደረገ ነውና ተገቢ ነው” አልኩ፡፡ግራ በመጋባት “እንዴት?” ስል ጠየቅሁት፡፡ “ጊዜው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ወቅቱም የጥምቀት በዓል የሚከበርበት፡፡ እናም ድፍን አዲስ አበቤ በጃን ሜዳ ተሰብስቧል፡፡ ንጉሠ ነገስት ዳግማዊ ምኒልክም በባለቤታቸውና በባለሟሎቻቸው ተከበው ተገቢውን ስፍራ ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ክብረ በዓሉ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት እየተካሄደ ነው፡፡ከተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች መሃከል አንዱ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ተራው ደረሰና በዚሀ ተስተካካይ የማይገኝላቸው የኦሮሞ ወጣቶች ቦታ ቦታቸውን ይዘው ጨዋታ ተጀመረ፡፡ በፈረስ ላይ ተሰይመው ጦር ወካይ ቀስታቸውን እየነቀነቁ ጋሻቸውን ለመከላከል ወደ ራሳቸው እያጠበቁ ፍልሚያው ቀጠለ፡፡ንጉሱ ንግስቲቱና መኳንንቶች በጨዋታው ተመስጠዋል፡ ዙሪያውን የከበበው ህዝብ የድጋፍና የማበረታቻ ጩኸት ያሰማል፡ በፈረሶች መራኮት አቧራው እየተጥመለመለ ወደ ሰማይ ይጠቀለላል፡፡በዚህ መሃል ያልተጠበቀ ንግግር ከንጉሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ከቆመ ሰው ተሰማ፡፡ ይሄ ሰው እንግሊዛዊው የታሪክ ተመራማሪ ፒተር ሃዋርድ ነው፡፡“ይሄማ የህፃን ልጅ ጨዋታ ማለት እኮ ነው! የጀግኖች ተግባር ግን በትክክለኛው ጦር ነው፤ ለዚህ ደግሞ የሚስተካከለኝ የለምና ከሃበሻ ውስጥ የሚሞክረኝ ካለ ዝግጁ ነኝ” ሲል ተናገረ፡፡ታላቅ ፀጥታ ሆነ፡፡ ፒተር እየተንጐራደደ በፌዝ ፈገግታ ይመለከታቸው ጀመር፡፡ የሀበሻ ጦረኝነት የሀበሻ ጀግንነት ለፈተና ቀረበ፡፡ በእርግጥም ዘለፋው ስለ አንድ ባህላዊ ጨዋታ ሳይሆን ከጀርባው ጨዋታውን ስለሚያካሂደው ልብ፣ ስለሚጫወተው ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ማንም ልብ ሳይላቸው ፈንጠር ብለው ከቆሙት ሰዎች መሃከል ማዕረግ አልባ የሆኑት አቶ ወርዶፋ ጨንገሬ የተባሉት በእርጋታ ወደ ፊት ተራምደው ከመጡ በኋላ ለንጉሰ ነገስቱ ለጥ ብለው እጅ በመንሳት፣ ፍልሚያውን ለማካሄድ ዝግጁ መሆናቸውንና የሚፈልጉትም ለሱባኤና ለዝግጅት የሚሆን የሳምንት ጊዜ እንደሆነ ተናገሩ፡፡ወሬው በፈጥነት ተሰራጨ፡፡ የከተማዋ ወሬ ይኸው ብቻ ሆነ፡ አቶ ወርዶፋ የሳምንቱን የዝግጅት ጊዜ ኮሶ በመጠጣትና በፀሎት አሳለፉት፡፡ ፒተር እንደወትሮው እየጠጣ እያነበበና አልፎ አልፎም እየጋለበ አሳለፈው፡፡ ነዋሪውም ስለ ሀገሪቱ ክብር፣ ስለተፋላሚው ህይወት፣ ስለ ንጉሰ ነገስቱ ክብር ተግቶ ፀለየ፡፡በተቆረጠው ቀን ከጥምቀቱ በዓል ያልተናነሰ ህዝብ ከየአቅጣጫው እየጐረፈ መጣ፡፡ ንጉሠ ነገስቱ ከባለቤታቸውና ከመኳንንቱ ጋር በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ተቀምጠዋል፡ ለሁለቱም ተፋላሚዎች የተዘጋጁት ፈረሶች ቀረቡ፡፡ ሁለት አሽከሮችም ጋሻና ጦር ለእያንዳንዳቸው አስረከቡ፡፡ሁለቱም ቀልጠፍ ብለው ፈረሶቻቸው ላይ ተሰየሙ፡፡ ቁንጥንጡ ፈረስ ላይ ጉብ ያሉት አቶ ወርዶፋ ጨንገሬ፤ ወደ ንጉሱ ነገስቱ መንበር ቀርበው ሰላምታ ከሰጡ በኋላ መፎከር ጀመሩ፡፡
ዘራፍ
ከጥንት እስከ ዛሬ
ጀግና ላልነጠፈባት ሀገሬ
ዛሬም ተሰይሟል
ወርዶፋ ጨንገሬ
ዘራፍ
የተነሸጡት መኳንንት ከግራ ከቀኝ በተኩስ አጀቧቸው፡፡ ህዝቡ በጩኸት ምድሪቷን አንቀጠቀጣት፡፡ ፈረሱ ላይ የተቀመጠው ፒተር ግር ያለው ይመስላል፡፡
ቁርጠኛዋ ሰዓት መጣች፡፡ እናም መልሶ ፀጥታ ሆነ፡፡ንጉሰ ነገስት ምኒልክም ቀዳሚነቱን ማን መውሰድ እንደሚፈልግ ጠየቁ፡፡ ከመቅፅበት የፒተር መልስ ተሰማ፡ በጨዋታው ህግ መሰረት አቶ ወርዶፋ በፈረሳቸው እየሸሹ ይመክታሉ፡፡ ፒተር እያሳደደ ያጠቃል፡፡ የቀዳሚነቱ ትሩፋት አጥቂ ሆኖ በመጀመር የማሸነፍ እድልን ማስፋት ነው፡፡ ማሸነፍ መኖር፤ መሸነፍ ደግሞ መሞት ነው፡፡አቶ ወርዶፋ መስማማታቸውን አሳወቁና ሁለቱም ተፋላሚዎች ወደ መሃል ሜዳ ጋለቡ፡፡ እንደ ስምምነታቸውም አቶ ወርዶፋ ቀድመው በፈረሳቸው መሸሽ ጀመሩ፡፡ ወዲያውም ፒተር ጦሩን በቀኝ እጁ ይዞ በግራው እየጋለበ ይከተላቸው ጀመር፡፡ታዳሚው ሁሉ ከንግግር ርቆ የሚሆነውን ይጠብቃል፡፡ ቀስ በቀስም በመሃላቸው ያለው ርቀት እየጠበበ መጣ፡፡ አቶ ወርዶፋ በፍጥነት እየጋለቡ ደግሞም ዘወር እያሉ ከባላጋራቸው ጋ ያላቸውን ርቀትና እንቅስቃሴውን ያረጋግጣሉ፡፡ ፒተርም ከትክክለኛው ርቀት ላይ ሲደርስ ተፋላሚውን በጦር ከፈረስ ለማውረድ ጓጉቷል፡፡በመጨረሻም ርቀታቸው በጦር መወርወሪያ ልክ ጠበበ፡፡ አቶ ወርዶፋ ለማረጋገጥ ዘወር ሲሉ ፒተርም አነጣጥሮ ለጀርባቸው ሲወረውር አንድ ሆነ፡፡በእርግጥም ተአምር ተከሰተ፡፡ አቶ ወርዶፋ ባልተጠበቀ ቅልጥፍና ከፈረሱ ጀርባ ተገልብጠው አንገቱ
ስር ተጠመጠሙ፡፡ በሁለት እግሮቻቸው የፈረሱን ጀርባ ቆልፈው በእጃቸው አንገቱን የሙጥኝ ብለው ወደ መሬት አስጐነበሱት፡፡የተወረወረችው ጦር በንፋሷ የፈረሱን ፀጉር ቀጥ እያደረገች በላያቸው አለፈች፡፡ ወዲያውም ቀልጠፍ ብለው ወደ ቦታቸው ተመልሰው መጋለብ ቀጠሉ፡፡ በምትሃቱ ግራጋቡት ንጉስ ነገስቱና መኳንንቱ እንዲሁም ህዝቡ ለትንሽ ጊዜ በዝምታ ከተዋጡ በኋላ ጭብጨባ ተኩስና ጩኸቱ ቀለጠ፡፡እነሆ በተራው ፒተር ሊሳደድ ሆነ፡፡ በቀይ ፊቱ ላይ ላብ ይንቆረቆራሉ፡፡ ድንጋጤው በግልፅ ይነበባል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ፒተር ከአቶ ወርዶፋ ፊት መሸሸ ጀመረ፡፡ ወዲያውም ጦራቸውን
ሰብቀው ተከተሉት፡፡ የሕዝቡ ጩኸት ሰማየ-ሰማያት የሚደርስ ይመስላል፡፡ርቀታቸው ጠበበ፡፡ ጦራቸውን ለመወርወር መዘጋጀታቸውን ያየውፒተር፤በደረቱ ፈረሱ ጀርባ ላይ ልጥፍ አለ፡፡ ግን ጦሯ ዘግይታ ነበር የተወረወረችው፡፡ አየሩን እየቀደደች ሄዳ ፈረሱ ጀርባ ላይ የተነጠፈውን ፒተርን ከፈረሱ ጋር አጣብቃ ሰፋችው፡፡ሁለቱም ዘግናኝ ጩኸት አሰምተው ከመሬት ተዘረገፉ፡፡ የፈረሱ ህይወት ከትንሽ መንፈራገጥና ጣር በኋላ አለፈች፡፡ የፒተር ፊት የተገረመ ይመስል ነበር፡፡ የሁለቱም ደም ተዋህዶ በዙሪያቸው አስፈሪ ኩሬ ሰርቷል፡፡ለዚህ የጀግንነት ተግባራቸው ንጉሠ-ነገስቱ ካመሰገኗቸው በኋላ የሚፈልጉትነ ቢጠይቁ እንደሚደረግላቸው ቃል ገቡላቸው፡ እናማ ይሄን የምታየውን ሰፈር ልባቸው የፈቀደውን ያህል በፈረሳቸው ጋልበው ጠየቁ፡፡ ተሰጣቸውም፡፡” ሲል ትረካውን አጠቃለለልኝ፡፡ሞቅ ብሎኛል፡፡ ትንሽ ብቆይ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን አይቻልም፡፡ የሰዓት እላፊ በደርግ አገዛዝ የተጣለና ያለፈበት ገደብ ቢሆንም ወታደራዊዋ አከራዬ ግን ዛሬም ይገለገሉበታል፡፡

 

 

Read 1674 times