Saturday, 07 September 2019 00:00

የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፤ የፓርቲዎችና የምርጫ ሕጉ በድጋሚ እንዲታይ ግፊት እያደረገ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ‹‹ሕጉ በድጋሚ የማይታይ ከሆነ ከቀጣዩ ምርጫ ራሳችንን ልናገልል እንችላለን››

       የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በቅርቡ በፓርላማ የፀደቀው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ሕጉን እንደማይቀበለው የገለፀ ሲሆን አንዳንድ የጋራ ም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ ሕጉ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከወዲሁ ከቀጣዩ ምርጫ ራሳቸውን እንደሚያገልሉ አስታውቀዋል፡፡
ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አዋጁ የፓርቲዎችን ሃሳብ ያላካተተ ነው ያለው የጋራ ም/ቤቱ፤ አዋጁ በድጋሚ ለውይይት ቀርቦና የፓርቲዎችን ቅሬታና ሃሳብ አገናዝቦ እንዲጸድቅ  ጠይቋል፡፡ ከ107 የጋራ ም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች መካከል 75 በመቶ ያህሉ በአዋጁ አለመስማማታቸውን የገለጹት የጋራ ም/ቤቱ ሰብሳቢዎች፤ አዋጁ በድጋሚ የሚስተካከልበት መንገድ መመቻቸት አለበት ብለዋል፡፡
7 ፓርቲዎች ተዋህደው የመሰረቱት “ሕብር ኢትዮጵያ” ፓርቲ ሊቀ መንበርና የጋራ ም/ቤቱ ም/ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል፤አዋጁ በድጋሚ የማይሻሻል ከሆነ ፓርቲያቸውን ጨምሮ በሕጉ ላይ ተቃውሞ ያላቸው ፓርቲዎች ከቀጣዩ ምርጫ ራሳቸውን ሊያገልሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡  
 ‹‹ሕጉ አንድም የኛን ሀሳብ  ሳያካትትና ሳያገናዝብ ነው የፀደቀው›› ያሉት ም/ሰብሳቢው፤ በዚህ አዋጅ መሰረት ቀጣዩ ምርጫ የሚከናወን ከሆነ፣ ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ያሸነፈበት የምርጫ አይነት ነው የሚደገመው ብለዋል፡፡
“ከእንግዲህ ኢሕአዴግ ብቻውን የሚያሸንፍበት የምርጫ ሂደት አካል መሆን አንፈልግም›› ሲሉ የተናገሩት  አቶ ግርማ፤ ፓርቲያቸው ከምርጫው ራሱን ሊያገልል እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ ኦፌኮ በበኩሉ በሰጠው መግለጫ፤ የአዋጁ በድጋሚ አለመስተካከል ቀጣዩን አገር አቀፍ ምርጫ ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ይሆናል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ምላሽ፤ፓርቲዎች ሕጉን በማርቀቅ ሂደት ሙሉ ተሳታፊ እንደነበሩ ጠቁሞ፣ በሕጉ ላይም የተደረጉ ውይይቶች በቂ ናቸው፤ ሕጉም አለማቀፍ መስፈርትን ያሟላ ነው ብሏል፡፡   

Read 5676 times