Print this page
Saturday, 07 September 2019 00:00

በቀጣይ አገራዊ ምርጫ 50 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በመራጭነት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 በቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ በመላ አገሪቱ 50 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን በመራጭነት ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የምርጫ ሥርዓቱም ከዚህ ቀደም በነበረው የአብላጫ ድምጽ ሥርዓት እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
በምርጫና በሲዳማ የሕዝበ ውሳኔ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ 3.7 ቢሊዮን ብር በጀት በተያዘለት ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ 50 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡  
ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች ባደረጓቸው ድርድሮች የምርጫ ሥርዓቱን ከአብላጫ ድምጽ ወደ ቅይጥ (አብላጫና ተመጣጣኝን ያማከለ) የምርጫ ሥርዓት ለመቀየር ተስማምተው እንደነበር ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ ከ‹‹ለውጡ በኋላ›› ግን በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ውይይት አልተደረገም ብለዋል፡፡
“ሁሉም ፓርቲዎች የምርጫ ሥርዓቱ እንዲቀየር እንደሚፈልጉ ቀደም ሲል ከተደረጉ ውይይቶች መገንዘብ ይቻላል” ያሉት ወ/ት ብርቱካን፤ በአሁኑ ወቅት ግን ጉዳዩን አጀንዳ ያደረገ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖሩን  አስታውቀዋል፡፡  
በመጪው ዓመት ግንቦት ወር ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አገራዊ  ምርጫ ቦርዱ በሙሉ አቅሙ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት ሰብሳቢዋ፤ ከምርጫው በኋላ ለሚፈጠሩ ቅሬታዎችና ክርክሮችም ቦርዱ የመፍቻ ስልቶችን ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡   
“ከምርጫው በኋላ ለሚፈጠሩ ክርክሮች አስፈላጊው የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፤በየምርጫ ጣቢያዎችም ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ የቅሬታ ፈቺ ኮሚቴ ይቋቋማል” ብለዋል፤ ወ/ት ብርቱካን፡፡
በቅሬታ አፈታት ዙሪያም አለማቀፍ ልምድና ተመክሮ መወሰዱን ሰብሳቢዋ አክለው ገልጸዋል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ሁሉን አካታች እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት ወ/ት ብርቱካን፤የተፈናቀሉ ዜጎች በያሉበት መጠለያ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘጋጅተውላቸው እንዲመርጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከ250 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በቀጣይ የሚመለምለው ቦርዱ፤ ለክልል የምርጫ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስፈጻሚነትም ሰዎችን አወዳድሮ ለመቅጠር የመመልመያ መስፈርቶችን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያዊ የሆኑና በየአካባቢያቸው ነባር ነዋሪ ሆነው መልካም ስም ያተረፉ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ገለልተኛ የሆኑና በፖለቲካ ሳይንስ፣ በሕግ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በማናጅመንት፣ በስታትስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የመሳሰሉ የትምህርት ዘርፎች ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል ብሏል፤ የቦርዱ መስፈርት፡፡
ቦርዱ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር መልካም ግንኙነት እንዳለው የገለፁት ሰብሳቢዋ፤ ገለልተኛነቱን ጠብቆ ከሁሉም ጋር  እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡     

Read 5831 times