Print this page
Saturday, 07 September 2019 00:00

በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተፈጠረውን ችግር የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቋመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለጠ/ሚኒስትሩ ነው

            በ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ላይ የተፈጠረውን ችግር የሚያጣራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነ ኮሚቴ መቋቋሙ የተገለፀ ሲሆን ኮሚቴው በጥቂት ቀናት ውስጥ ችግሩን አጣርቶ ውጤቱን እንዲያሳውቅ መመሪያ ተላልፏል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ረቡዕ እለት በሰጠው መግለጫ፤ ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም የተሰጡ የአራት ፈተናዎች ውጤት ብቻ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ እንደ መመዘኛ እንደሚያገለግሉ ያስታወቀ ሲሆን ከሰኔ 10 እስከ 12 የተሰጡ ፈተናዎች የተማሪዎቹን ብቃት መለካት የሚያስችሉ አይደሉም ብሏል፡፡
በዚህ መሰረት ለዩኒቨርስቲ መግቢያነት መመዘኛ የሚያገለግሉት እንግሊዝኛ፣ ሂሳብ፣ ስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፊዚክስ፣ ለማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ የጂኦግራፊ ትምህርት ውጤት መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የመግቢያ ነጥቡም በቀጣይ ይገለጻል ተብሏል፡፡
ይህን መግለጫ ተከትሎ ምሁራንና ተማሪዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰማቸውን ቅሬታ እየገለጹ ሲሆን ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂ አካል ሊኖር ይገባል የሚሉ ድምፆችም በብዛት ተንፀባርቀዋል፡፡  
ችግሩ በማንና እንዴት ተፈጠረ? ማንስ ሃላፊነት ይወስዳል? የሚለውን የሚያጣራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የኮሚቴው ሰብሳቢም የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው መሆናቸው ታውቋል፡፡
በአገር አቀፍ ፈተና እንዲህ ያለው ስህተት ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው መሆኑ የተገለፀ  ሲሆን ለችግሩ መከሰት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት በሕግ እንዲጠየቁም ከሕብረተሰቡ ግፊት እየተደረገ ነው፡፡

Read 5405 times