Saturday, 07 September 2019 00:00

መንግስት አስቸኳይ ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ እንዲያመቻች ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ‹‹የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት›› - ኢሃን

             የአገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል አስቸኳይ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የውይይት መድረክ መንግስት እንዲያመቻች የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ጥሪ አቀረበ፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀል፣ ንብረትን መነጠቅና የጅምላ እስር በሰፊው እያጋጠማቸው መሆኑን የጠቆመው ኢሃን፤ በሌላ በኩል ታይቶ በማይታወቅ የኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ ነው ብሏል፡፡
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መደራረባቸውን ተከትሎም ሕዝብ በመንግስት ላይ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ በመሄድ ላይ ነው ብሏል ንቅናቄው በመግለጫው፡፡
በአገሪቱ ባሉ የፖለቲካ ቡድኖች መካከልም ያለው አለመተማመንና ጥርጣሬ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆመው ኢሃን፤ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከልም የተፈጠረው መከፋፈልና ተቃርኖ መንግስትን በጋራ ለመምራት ከማያስቻላቸው ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡
በእነዚህ ሁኔታዎች የተነሳም የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለመተንበይ አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሱን፣ እነዚህ ችግሮችም የቅርብ ጊዜ አመራሩ የፈጠራቸው ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የተከማቹና ስር የሰደዱ የአገሪቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች መገለጫ መሆኑን ንቅናቄው አመልክቷል፡፡
እነዚህን የአገሪቱን ህልውና በእጅግ እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮችን ኢሕአዴግ ብቻውን የመፍታት አቅም እንደሌለው የገለፀው ንቅናቄው፤ የአገሪቱን ተደራራቢ ችግሮች ስትራቴጂያዊ በሆነ መልኩ በየደረጃው ለመፍታት የሚቻልበትን መንገድ በጋራ ለመቀየስ መንግስት አስቸኳይ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የውይይት መድረክ እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡
አገሪቱን ካንዣበበው የህልውና አደጋ ታድጎ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገርም ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ቀዳሚ መፍትሄ ነው ብሎ እንደሚያምንም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ በቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አባላት የተቋቋመና በኢ/ር ይልቃል ጌትነት የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡

Read 886 times