Saturday, 16 June 2012 09:23

ቤትሆቨን - የሙዚቃው ፀሐይ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

በልባችን ትልልቅ ስም፣ በመጽሐፍት ውብ ታሪክ የተፃፈላቸው የየዘርፉ ጠቢባን፣ እንደኛው እናት አምጣ የወለደቻቸው ሥጋ ለባሾች መሆናቸው፣ ነገ ለሁላችንም ተስፋ ሰጥቶ ያተጋናል፡፡ ስለዚህም ያንዱ ታላቅ ሰው ታሪክ በየልቦቻችን ተዘርቶ ሌሎችንም ይፈጥራልና ታሪክ መኖሩ ደግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያንዳንዱ ሰው ስም በሠፈሩ፣ የሌላው ስም በመስሪያ ቤቱ አጐበር ሥር ሊቀር ይችላል፡፡ እንግዲህ ከዚች አጥር ዘልሎ አጥናፍ የናኘው ነው ብዕር ነሽጦ ገጽ አስገልብጦ ዘመን የሚዘልለው፡፡ በተለይ በኪነጥበቡ ዘርፍ ያሉ ሰዎች የሰውን ልጅ ታሪክ ሁሉ ተጋርተው ስለሚኖሩ በብዙ አደባባዮች ስማቸው ይዘከራል! ከነዚህ ተዘካሪ ስሞች መካከል ሉድዊግ ቤትሆቨን አንዱ ስለሆነ ለዛሬው ይህንን የትውልድ ችቦ ከፍ አድርጌ ብርሃኑን በጥቂቱ ላሳይወድጄአለሁ፡፡ ይህ በየትውልዱ ልብ ዜማውን ያንቆረቆረና ሚሊዮንና ቢሊዮን ጆሮዎችን ዘልቆ፣ ነፍሶችን ያማለለ ሰው፣ የተወለደበት ቤተሰብ የተረጋጋና ተስፋ ያረበበበት አልነበረም፡፡

ወላጅ አባቱ የመጠጥ ሱሰኛ ስለነበር፣ ቤተሰቡን በወጉ ማስተዳደር ስለተሳነው ቤተሰቡ ሁሉ በምሥልቅልቅ ሕይወት የሚዳክሩ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት የታናናሾቹን ሕይወት ለመታደግ እንጀራ የማብላት ዕዳው የወደቀው በእርሱ ላይ ነው፡፡ ፒያኖ ለመጫወት መጀመሪያ ሲሄድም የሙዚቃ ፍቅር አንገብግቦት ሳይሆን ለቤተሰቦቹ ሕይወት እንደሚታረድ በግ ተነድቶ ነበር፡፡ በ1770 ዓ.ም ጀርመን ቦን ከተማ የተወለደው ቤትሆቨን፤ የወላጅ አባቱ ጉዳይ አከራካሪ ነበር፡፡ በሁለት ሰዎች አባትነት መካከል የሚዋዥቅ ወሬ ነበር፡፡ በትምህርቱም የሚሞገስ ወይም ሰነፍ ተማሪ ተብሎ የሚጣጣል አልነበረም፡፡ ማንበብና መፃፍ፤ አርቲሜቲክ በመጠኑ፤ እንዲሁም የላቲንን ቋንቋ ተምሯል፡፡ ወደ ሙዚቃው ዓለም በእንጀራ ግፊት ሲገባም ብዙ ሰዎች በአድናቆትና በሙገሳ አልተቀበሉትም፡፡ ይልቅስ ያጣጣሉት ነበሩ፡፡ ይሁንና ከቦን ከተማ ወደ ፍራንክፈርት ሄዶ ኒፌ የተባለው የሙዚቃ ሰው ሲተቸው፣ እርሱ ግን በ13 ዓመቱ አይሞከሩም የተባሉ የሙዚቃ ቀመሮችን ሠርቶ ማስደነቅ ችሎ ነበር፡፡ ሌላው የቤትሆቨን ግሩም ነገር ወደ ቪሮና ሲሄድ አጣጥሎ የተቸውን ተፌን በሚመለከት የፃፈው ነገር ነበር፡፡ በደብዳቤው ላይ “…በሙዚቃ ጥበብ እንዳድግና እንድቀጥል ስለመከርኸኝ አመሰግናለሁ፡፡ ለወደፊት ታላቅ ሰው ሆኜ ብገኝ ያንተ ታሪክ ከኔ የሚነጠል አይደለም” በማለት ቅን ልቡን አሳይቷል፡፡ ቤትሆቨን በእምነቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማኝ ስለነበር፣ በእግዚብሔር ፈጣሪነት ብቻ ሳይሆን፣ ሊመለክ የሚገባው እንደሆነም ያምን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ከሰዎች ጋር እንደማያወራ ይነገራል፡፡ ይህ ፀባዩ ደግሞ ከሳይንቲስቱና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዩ ሚካኤል ፋራዳይ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ፋራዳይ በቤተክርስቲያን የስብከት አገልግሎት እየሰጠ ብዙ ጊዜ ግን በሃይማኖት ጉዳይ ላይ አያወራም፡፡ ቤትሆቨን በሙዚቃ ፍቅር እየተመሰጠ መጥቶ ስቴርከል ከተባለው ድንቅ ፒያኖ ተጫዋች አጠገብ ቆሞ ቢያይም፣ ችሎታው ተአምር ስለሆነበት ደፍሮ መጫወትን ቶሎ አልደፈረም፡፡ ተጫወት ተብሎ ሲጋበዝ እንኳ እንደዚያ እጫወታለሁ የሚል ድፍረት በማጣቱ አንገራግሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቤትሆቨን ለላቀ የሙዚቃ ጨዋታ ጣቶቹን ከነቀነቀ በኋላ የሠራው ሥራ እጅግ አስገራሚ ሆኖ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ዌግለር የተባለው ሙዚቀኛ አላደነቀለትም፤ ይልቅስ አጣጣለበት፡፡ ይሁንና ቤትሆቨን የዛኛውን መሠላል ደረጃ በደረጃ እየረገጠ ወደ ከፍታው መጓዝ ቀጥሎ ነበር፡፡ ቤትሆቨን የሙዚቃ ትምህርት ለመማር ወደ ቪየና ሲሄድ መነሻው የጆሴፍ ሃይደን ጐትጓችነት ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ለስንቅና ለኑሮ የሚሆነው አንዳች ነገር አልነበረውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ማክስ ፍራንዝ የተባለው ሰው በቤተክርስቲያን (ቻፕል) ሙዚቃ እየተጫወተ ገንዘብ እንዲከፈለው አመቻቸለት፡፡ ያ ጊዜ ደግሞ የፈረንሳይ አብዮት ፍንዳታ በመሆኑ ፍርሃት በአካባቢው ሀገራት ሁሉ አንዣብቦ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ደቡብ ጀርመን ለጦርነት አሰፍስፎ ነበር፡፡ ካውንት ቮን ዋልደን - በቤትሆቨን የሙዚቃ ስኬት ውስጥ ትልቅ ሚና ያለውና ተሰጥኦውን አውቆ መንገዶችን ያመለከተው ሰው ነው፡፡ ዋልደን የሙዚቃ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን በሚገባ መጫወት የሚችል የጥበብ ሰውና በዘመኑ የንጉሱ ቤተመንግስት አስተዳደር ሠራተኛ የነበረ ነው፡፡ ታዲያ ለቤትሆቨን ኦርጋኒስትነትና የሥልጠና ትምህርት አቅጣጫ በማሳየትና የወደፊት ሁኔታውን በመተንበይ መንገዱን የደለደለለት ወዳጅ ነበር፡፡ ለሰዎች ሕይወት ስኬት ቀና ሰዎችን ማግኘት አንዱ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ይታወቃል፤ ቤትሆቨን በዚህ ዕድለኛ ነበር፡፡ ቤትሆቨን ነጭናጫና ብስጩ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከጓደኞቹና ከወዳጆቹ ጋር ይጋጫል፡፡ ይሁን እንጂ በኋላ በፃፈው ደብዳቤ ላይ እንደተገለፀው ፍፁም ሰው ወዳድና ለሰው ራሱን የሚሰጥ እንጂ ክፉ እንዳልነበረ በሚያሳዝን ሁኔታ አስታውቋል፡፡ እንዲያውም እንዲህ ይላል:- አንድ ቀን እነዚህን ቃላት ስታነብቡ በተሳሳተ መንገድ እንዳያችሁኝ ትረዳላችሁ፡፡ ለልጆቻችሁ ሠናይነትን ምከሩ፣ ደስታን የሚሰጠው ገንዘብ ብቻ አይደለምና መልካምነት ከጥበብ ቀጥሎ ለኔ ሕይወቴ ነው፤ እስከዛሬም የኖርኩት በርሱ ነው፡፡ ደግሞ ወደፊትም ሕይወቴ ራስን በማጥፋት አይጠናቀቅም፡፡

 

የሕይወት ታሪክ ፀሐፊው እንደሚሉት፤ ቤትሆቨን በጉባኤ ሙዚቃ ሲጫወት አንዳንዴ ይበሳጭ ነበር፡፡ ከጣቴ ላይ ደም እስኪቋጠር ድረስ ያሠሩኛል እያለ ሲበሳጭ ወዳጅ እየመከረው ሳለ ነው አስናደቂ ሜሎዲዎች የፈለቁለት፡፡ የብስጭቱን ምክንያት ግን ሲናገር የጆሮው ሕመም ነው፡፡ በተፈጥሮ ያዝናል፣ ይተክዛል፣ ይመረራል፡፡ ይሁንና በቤትሆቨን የ16 ዓመት ዕድሜ ሥራ ከተመሰጡት ሁለት ሰዎች አንዱ የነበረው ሞዛርትእንዲህ ብሏል - “ይህ ወጣት ልጅ ስሙ በመላው ዓለም ይናኛል” ይህን ሲል ብዙዎች ግን እንዴት ሆኖ ለዚያ ይበቃል የሚል ጥያቄ ነበራቸው፡ የገባቸው ገብቷቸዋል፡፡ ያልገባቸው አልገባቸውም ነበረና! ይሁንና እስከዛሬ ድረስ ነፍስ ውስጥ ገብተው የሚላወሱትን ሲምፎኒዎች የቀመረው ቤትሆቨን፤ “ወደፊት ትልቅ ሰው እሆናለሁ…ትልቅ ሥራ እሠራለሁ” ብሎ ተንብዮ ነበር፡፡ ቤትሆቨን መፃሕፍትን አጣጥሞ የሚያነብብና በርካታ መጽሐፍት የነበረው ሰው ነው፡፡ ግሪክና ሮማን ቢያነብብም ይበልጥ የሚመስጠው በሥነ ጥበባት ንባብ ነው፤ ውበት ላይ ያተኩራል፡፡ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ሲያሰኘው ደግሞ እንደ ፕሌቶ“ሪፐብሊክ” ያሉትን ያነብባል፡፡በኪን ጉዳይ ግን የሹቤርትን አጣጥሟል፡፡ መጽሐፉንም በክብር አስቀምጦታል፤ ይሁን እንጂ በሙዚቃ የላቀ ችሎታ ያላቸው ሰዎች በጥንቃቄ መርምረው እንዲያነብቡት ጠይቋል፡፡ ምክንያቱምየሚቀበላቸውና አሳሳች ብሎ የሚተቻቸው ነገሮች ስለነበሩት ነው፡፡ ቤትሆቨን ለሞዛርትም ትልቅ አድናቆት አለው፡፡ ይሁንና የማይወድለትም ነገር ነበረው፡፡ ሞዛርት መጽሐፍት አንባቢ ባለመሆኑ ብዙ ነገሮችን ማወቅ ሲገባው አላወቀም፡፡ መሻሻል ያለበትን ያህል አልተሻሻለም፤ ፒያኖ ጨዋታውን ብዙም አያደንቅም፡፡ ብዙ የሙዚቃ ቅንብሮችን የሠራው ቤትሆቨን፤ ከወጣት ሙዚቀኞች ጋር የነበረው ማህበራዊ ግንኙነት ጥሩ አልነበረም፡፡ ነጭናጫና ብስጩ፤ ቀና መልስ የማይመልስም ነበር፡፡ የሕይወት ታሪክ ፀሐፊዎቹ እንደሚሉት፤ መግባባት ዳገት ሲሆንበት የተፈጠረ ጠባይ ነው፡፡ ከ1816 -1818 ዓ.ም ባለው ጊዜ ጆሮው ላይ ለማዳመጥ የሚረዳ መሣሪያ ተገጥሞለት ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር የሚግባባው በወረቀት በመፃፃፍ ነበር፡፡ ሌላው ጉድ የሚያሰኘው የቤትሆቨን የማስታወስ ችሎታ ማነስ ነበር፡፡ አሁን የሠራውን የሙዚቃ ቅንብር በቅጽበት ይረሣዋል፤ ታዲያ ውስብስብና አስቸጋሪውን የኦርኬስትራ ቅንብር ብቻ አይደለም፤ ቀላል የሚባለውን “ሶሎ” ጭምር ነው፡፡ ንባብ ላይ ብርቱ ነው፤ ያነበበውን ግን አይረሳም፡ የሼክስፒር ሥራዎችን ሙሉ ጥራዝ፣ የጐተን ግጥሞችና ሌሎች ሥራዎች፣ የሆሜርን ኢልያድና ኦዲሴ እና የሌሎቹን አንብቧል፡፡ ይሁን እንጂ የሆሜርን ኦሊያድ ኦዲሴ እንደሚበልጠው ይናገራል፡፡ ኦሊያድ የሚያወራው ስለጦርነትና ጦር መሣሪያ ነው፤ ያኛው ግን ስለሠላማዊ ሕይወት ነው - የሚል አቋም አለው፡፡ ቤትሆቨን ነጭናጫ ነው የሚባለውን ያህል ቅን ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ የፒያኖ ተጫዋቹና ሙዚቃ አቀናባሪው ሁልዎ ሚስት፣ በቤትሆቨንን ዞማ ፀጉር ላይ የሚታዩትን ጥቁር የፀጉር ቀለበቶች ሠርቀው እንዲያመጡላት ጠይቃ፣ ከፀጉራም በግ ላይ ቆርጠው የቤትሆቨን ፀጉር ነው ተብሎ እንደተሰጣት ሲሠማ፤ ያደረገው ነገር የሚገርም ነው፡፡ “እንዴት የኔን ዞማ ፀጉር ለማስቆረጥ ተመኘች” ሳይል ራሱ በመቀስ ቆርጦ ላከላት፡፡ ይህ የቤትሆቨንን ገራም ልብ ያሳያል፡፡ ይህ የሆነው በ1826 ዓ.ም ነው፡፡ የቤትሆቨን የጓዳ ጉድም ብዙ የተለየ አይደለም፡ ሁልጊዜ ንጋት ላይ ተነስቶ የሚሄደው ወደመቀመጫው ነው፡፡ በእግሩ የሰዓት ያህል ጉዞ በመጓዝ የሚሠራውን ነገር ያሰላስልና ይመጣል፡፡ በአብዛኛው ከሰዓት በኋላውን የሚያሳልፈው የእግር ጉዞ በማድረግ ነው፡፡ አመሻሽ ላይ ደግሞ አንድ የለመደው ቡና ቤት ውስጥ በጓሮ በር ገብቶ ጋዜጦችን ያገላብጣል፡፡ በክረምት ደግሞ በተከታታይ የሥነ - ጽሑፍ ንባባት ላይ ያተኩራል፡፡ አመሻሽ ላይ የሙዚቃ ሥራ የሚሠራው አልፎ አልፎ ነበር፡፡ አመጋገቡን በተመለከተ ጧት ጧት ያለቡና ምግብ አይቀምስም፤ ከየትኛውም የምግብ አይነት ጋር ይሁን ቡና ከሌለ አይሆንለትም፡፡ ማካሮኒና አይብ (ቺዝ) ለርሱ በጣም የተመረጠ ምግብ ነው፡፡ ሌላ ምግብ ከሆነ ማጉረምረሙ ለብቻ ነው፤ ከሠራተኛው ጋር ንትርክ ውስጥ ይገባል፡፡ እንኳን ሰበብ አግኝቶ እንዲሁም ነጭናጫ ነው ቤትሆቨን፡፡ ሠራተኛውም ታውቃለች፡፡ ሁሉን ተጠንቅቃ ነው፡፡ አንዳንዴ ሾርባና ድንችም ለእራት ይመርጣል፡፡ ጨጓራውን ባያመው ወይን መጠጣት ይወድዳል፤ ግን ደሞ ጨጓራው ያቃጥለዋል፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ማምሻውን ቢራ እየጠጣ ጋዜጣውን እያገላበጠ ይዝናናል፡፡ በተለይ በስተርጅናው ጊዜ ቡና ቤቶችና ሬስቶራንቶችን መጐበኘት ያዘወትር ነበር፡ሰዎች እንዳያተኩሩበት እያለ በጓሮ በር ጓዳ ተቀምጦ ያሳልፋል፡፡ ከቤቱ ቅርብ የነበረችው ቡና ቤት ደግሞ ተመራጩ ነበረች፡፡ ይሁንና ሰዎች ሊተዋወቁት ስለሚፈልጉ ጥቂት አንብቦ በጓሮ በር ሹልክ ይላል፡፡

 

 

Read 2807 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 09:30