Print this page
Saturday, 31 August 2019 13:42

አዲሱ ጠ/ሚ ሱዳንን ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ዝርዝር ለማስወጣት እየሰሩ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ሱዳን የተመድ ሰላም አስከባሪ ከዳርፉር እንዲወጣ ጠየቀች

          አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ፣ አሜሪካ፣ ሱዳንን ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድታስወጣ ጥረት ማድረግ መጀመራቸውን እንዳስታወቁ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ፤ ሱዳንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጀመረው ጥረት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሽብርተኝነትን የሚደግፉ አገራት በሚል በአሜሪካ ከተመዘገቡት አገራት ተርታ ማስወጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በመጠቆም፣ ይህንን እውን ለማድረግ፣ ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ማስታወቃቸውን  ዘገባው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1993 በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተችው ሱዳን፣ ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ መውጣቷ ለውጭ ኢንቨስትመንት በሯን እንድትከፍትና እጅግ ወሳኝ የሆነውን የገንዘብ አቅርቦት ከአለም ባንክና አይኤምኤፍ ለማግኘት እድል የሚሰጣት በመሆኑ፣ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ሱዳን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በዳርፉር የሚገኘውን የሰላም አስከባሪ ጦር በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲያስወጣ መጠየቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተመድ የሱዳን አምባሳደር ኦመር ሞሃመድ ሲዲግ፣ ባለፈው ሰኞ ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት አቤቱታ፣ የሰላም ማስከበር ተልዕኮው የሚያበቃበት ጊዜ ላይ መድረሱን በመጠቆም፣ ተመድ በዳርፉር አካባቢ መንግስት፣ የጦር መሳሪያዎችንና ወታደሮችን እንዳያንቀሳቅስ የጣለውን እገዳ ሊያነሳ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር ባደረገው ስብሰባ፣ ሱዳን በጸጥታ ችግር ውስጥ በመግባቷ በዳርፉር የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ጦር ከአካባቢው የሚወጣበት ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ እ.ኤ.አ በ2003 በዳርፉር የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ወደ አካባቢው የገቡ 5 ሺህ 600 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች አሁንም በዳርፉር እንደሚገኙና የአፍሪካ ህብረት ግን በዳርፉር ያለው ሁኔታ ገና ባለመረጋጋቱ የሰላም አስከባሪው እንዲወጣ የቀረበውን ጥያቄ ተገቢ አይደለም ሲል መተቸቱን አመልክቷል፡፡

Read 1391 times
Administrator

Latest from Administrator