Saturday, 31 August 2019 13:35

ሥራ አጥነት፣ ብር በማተም የመጣ ዕድገትና የዶ/ር ዐቢይ ፈተና

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

ዓመቱ ሊጠቃለል እየተቃረበ ነው፡፡ ከአዲስ  አድማስ ጋዜጣ ጋር በነበረኝ የአንድ ዓመት ቆይታ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በኢኮኖሚው ጉዳይ ብዙም አልሄድኩበት፡፡ እናም የዛሬው መጣጥፌን ትኩረት በኢኮኖሚው ላይ አድርጌአለሁ፡፡    
በአዲስ አበባ ከተማ፣ ኮተቤ 02 ቀበሌ አካባቢ አንዲት አነስተኛ ባህላዊ ገበያ አለች፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ወደዚያች ገበያ ምርታቸውን ይዘው በመምጣት ከከተሜው ህብረተሰብ ጋር ይገበያያሉ፡፡ ባለፈው ሰሞን ባለቤቴ አስቤዛ ልትሸምት አብሬያት ሄጄ ነበር፡፡ እሷ እስከምትገዛ አካባቢውን ስቃኝ፣ አንዲት እናት በእጃቸው ዘንቢል አንጠልጥለው፣ በትከሻቸውም አዝለው ከገበያው ወጡ፡፡ እቃቸውን እኔ አጠገብ ያለ የመንገድ ጠርዝ ላይ አስቀምጠው የሚሸከምላቸው የቀን ሰራተኛ እያማተሩ፤ “ዘላለም ለማይሞላ ጉድጓድ!” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
“ምንድነው እሱ እናቴ?” አልኳቸው፡፡
“ምኑ?” አሉኝ፡፡
“ዘላለም ለማይሞላ ጉድጓድ ያሉት?”
“ሆዳችን ልጄ! ዘላለም የማይሞላ ጉድጓድ! እሱን ለመሙላት እድሜ ልክ መመናተል!...እዳ ነው እቴ!... ኤዳልኝ!”... አሉ ምርር ብለው፡፡ ቀጠልኩና “እንዴት ነው ገበያው ታዲያ?” በማለት ጠየቅኳቸው፡፡ “ምን እንዴት አለው ልጄ!...ዱሮ ሃያ ብር ይዘን መርካቶ ከሄድን ለወር የሚበቃ አስቤዛ ገዝተን እንመለስ ነበር---”ማሪኝ እናት መርካቶ!” ያስብላል፡፡ ዛሬ 20 ብር ባቶቢስ መርካቶ አድርሶ አይመልስህም፡፡ በዚያ ላይ ያልተወደደ ምን አለ? በመቶ ብር 3 ኪሎ ሽንኩርት ነው የምትገዛው፤ ቃሪያ በአቅሟ በመደብ በመደብ መሸጧ ቀርቶ እንደ ከረሜላ በቁጥር ሆኗል:: ያውም የሞተ ቃሪያ!...” ንግግራቸውን ቆም አድርገው አሻግረው ይመለከቱ ጀመር፡፡
ይህንን ሃሳብ የዚች መጣጥፌ መነሻ ያደረግሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በሀገሪቱ ያለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሰውን እያማረረ መሆኑን ለማመላከት ነው፡፡ መማረር ብቻ አይደለም:: በተለይ እዚህ አዲስ አበባ በሚያገኙት ገቢ መኖር ስላልቻሉ ሰዎች ለልመና እየተዳረጉ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ ሌብነትም ተስፋፍቷል፡፡ የቤት ኪራይ ያስመረረው አዲስ አበቤ፣ ወደ አጎራባች የኦሮሚያ ከተሞች እየተሰደደ ነው፡፡ በኮንዶሚንየም ቤቶች ተከራይተው የሚኖሩት የኤርትራ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኮንጎ፣ የኬንያ፣---- ስደተኞች ናቸው፡፡
በርግጥ ዱሮና ዘንድሮ አንድና ያው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምንም ነገር ዱሮ በነበረበት ሁኔታ፣ መጠን፣ ዋጋ፣----ዘንድሮ ሊገኝ አይችልም፡፡ በነፃ የምንተነፍሰው አየር እንኳ የዱሮውና የዘንድሮው አንድ አይደለም፡፡ የዘንድሮው አየር በፋብሪካ ጭስ የተበከለ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ እናም ዛሬ ዛሬ ከፊል አየር፣ ከፊል የፋብሪካ ጭስ ስለምንተነፍስ እንደ ሞተር የማጓራት ዓይነት ባህሪ ሊታይብን ይችላል ይላሉ፤አንዳንድ ፌዘኞች፡፡
በሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዋጋ ንሯል፡፡ ኑሮ ጣሪያ አልፎ ሰማይ ነክቷል:: በደመወዝ የሚኖረው ከተሜ፣ ደመወዙና ኑሮው አልተመጣጠኑም፡፡ በተለይ የቤት ኪራይ የሚቀመስ አልሆነም፡፡ ኢኮኖሚስቶች አንድ ሰው ከደመወዙ ላይ ለቤት ኪራይ እስከ 35% መመደብ እንደሚኖርበት ይናገራሉ፡፡ በእኛ ሀገር ግን በአሁኑ ወቅት የአንድ ሰው ደመወዝ ሙሉ ለሙሉ ለቤት ኪራይ ቢመደብም በቂ ሊሆን አልቻለም፡፡ የመንግስት ሠራተኛው “በአስማት ነው የሚኖረው” የሚለው አባባል ከቀልድነቱ በላይ ብዙ መልእክት የሚያስተላልፍ ይመስለኛል፡፡
ፓርላማ በነበርኩበት ወቅት “የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ” ይመራ የነበረው በኢዴፓ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ያገኘናቸውን መረጃዎች በመመልከትና ዓመታዊ የመንግስት የበጀት ምንጮችን ግምት ውስጥ አስገብተን በመገምገም፣ መንግስት ብር እንደሚያትም ጥርጣሬ አደረብንና ለአንድ በወቅቱ ትልቅ ባለስልጣን የነበሩ የኢህአዴግ ሰው “መንግስት ብር ያትማል እንዴ?” የሚል ጥያቄ ስናቀርብላቸው፣ ከመጠን በላይ ተናደዱ፡፡ ነገሩ ለምን ነቃችሁብን ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት የተገኘው ባለ ሁለት አኀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት የመጣው “ብር በማተም” እና “ሀገሪቱን እዳ ውስጥ በመዝፈቅ” መሆኑን በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ብር ማተምን ጋብ በማድረጉና ብድሩንም መጠኑን በመቀነሱ፣ የሀገሪቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት ተፈጥሯዊ ቁመናውን ይዞ መራመድ ጀምሯል የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት የነበረው የሀገሪቱ የግሽበት ምጣኔ 16.06 በመቶ ሲሆን ባለፈው ሐምሌ ወር የተመዘገበው አጠቃላይ የግሽበት ምጣኔ 15.5 በመቶ ነበር፡፡ በተናጠል ሲታይ የምግብ ዋጋ በሐምሌ ወር በ20.1 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ይህ የዋጋ ንረት በተናጠል በእያንዳንዱ የምግብ ዓይነት ቢታይ ደግሞ የተለየ ገጽታ አለው፡፡ ለምሳሌ የሽንኩርትን ዋጋ ብናይ፣ ከአምስት ብር ወደ 30 ብር አሻቅቧል:: ይህም የዋጋ ማሻቀብ በመቶኛ ሲሰላ ወደ 500% ማደጉን ያመለክታል፡፡ የጤፍ ዋጋ ከብር 1ሺ500 ወደ 3ሺ500 አሻቅቧል፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ ወደ 133% አቅንቷል ማለት ነው፡፡ የትራንስፖርት ዋጋ፣ የቤት ኪራይና የመሳሰሉት-- ዋጋዎች እያሻቀቡ መሆኑ ታይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱ የሥራ አጥነት ምጣኔ 20% ደርሷል፡፡
አሳሳቢው ነገር የምግብ ዋጋ መናሩ ብቻ አይመስለኝም፡፡ በሚመጣው ዓመት የሚጠበቀው የምርት መጠን በፀጥታ ሁኔታ፣ በዝናብ እጥረትና በዝናብ መብዛት አደጋ ሊደርስበት እንደሚችል አመላካች ሁኔታዎች እየተስተዋሉ በመሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በሌላ በኩል፤ አሁን የተገኘው “ለውጥ” ገፊ ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ የወጣቶች ሥራ አጥነት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በሥራ አጥነት የተማረረ ወጣት በፈጠረው ንቅናቄ፣ ኢህአዴግን ለሦስት ዓመታት በሰላማዊ ሰልፍ ሲያናውጥ ከርሞ፣ ከውስጡ የለውጥ ኃይል ፈንቅሎ እንዲወጣ አደረገው፡፡ በለውጡ እንቅስቃሴ ወቅት “ቤትና ሥራ ይሰጥሃል፣ የእከሌ ህንፃ ለአንተ ይሆናል፣ ያኛው የኢንቨስትመንት መሬት ከእንቶኔ ተቀምቶ ትከፋፈላለህ--” ተብሎ የተቀሰቀሰ ሥራ አጥ ወጣት፤ ቃል የተገባለትን ካላገኘ ለሌላ ነውጥ አይነሳሳም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡
ለወጣት ሥራ አጦች የሥራ ዕድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ የሥራ እድሉን የሚፈጥረው ግን መንግስት ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ባለ ሀብቶች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ፤ በፀጥታ ችግር ምክንያት በአሁኑ ወቅት ኢንቨስትመንቶች ተቀዛቅዘዋል፡፡ በተለይም የእርሻ ኢንቨስትመንት ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ ያለው አማራጭ ወይ እንደተለመደው ብር በማተም፣ የመንግስት ግንባታዎችን በማጧጧፍ፣ ወጣቶችን ወደ ሥራ ማሰማራት አሊያም ሌላ አማራጭ ማየት ነው፡፡ ብር ማተም ጊዜያዊ የስራ እድል ቢፈጥርም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ ስለሚያናጋ ተመራጭ አይሆንም፡፡ እኔ ሌላ አማራጭ ይታየኛል - ሰፈራና አዲስ የመሬት ድልድል ማድረግ! ወደ ሰፈራና አዲስ የመሬት ድልድል ጉዳይ ከመሄዴ በፊት ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ላንሳ፡፡
ባለፉት ዓመታት የኑሮ ውድነቱን እንዲህ ያናረው ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሲነሳ፤ ኢህአዴግ “የኢኮኖሚ እድገቱ ራሱ የፈጠረው ነው” የሚለውን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶችን ሲያቀርብልን ነበር:: በርግጥ “የኢኮኖሚ እድገት የኑሮ ውድነትም ሆነ የዋጋ ንረት አያመጣም” ብሎ መከራከር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ብቸኛም ባይሆን አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በመንግስት በኩል በተከፈቱ የኮብልስቶንም ይሁን፣ የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ አሊያም የመንገድና የባቡር ሐዲድ ዝርጋታ ስራዎች ምክንያት ዜጎች ስራም ገቢም ነበራቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የገቢ መጨመርን ያመጣል፡፡ ገቢ ሲጨምር የመግዛት ፍላጎት መጨመሩም ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከገቢ የሚነሳ ፍላጎት ሲጨምር አቅርቦት በቂ አለመሆኑም የሚጠበቅ ነው፡፡ የአቅርቦት በቂ አለመሆን ደግሞ ዋጋ ማናሩ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ያ ሁሉ ገቢ የለም፤ ሥራም የለም፡፡ የዋጋ ንረቱ ግን በተለይ በምግብ ምርቶች ላይ እንደቀጠለ ነው፡፡ ለምን ቢባል መልሱ፣ የህዝብ ቁጥር መጨመርና በቂ የምግብ እህል ምርት አቅርቦት ስለሌለ ነው፡፡ “አቅርቦት በቂ ያልሆነው ለምድነው?” የሚል ጥያቄ ስናነሳ ደግሞ “የተትረፈረፈ ምርት አለማምረት” የሚል መልስ እናገኛለን፡፡
የተትረፈረፈ የጤፍ ምርት፣ የተትረፈረፈ የማሽላ፣ የስንዴ፣ የገብስ፣ የበቆሎ፣ የሽንኩርት፣ የድንች፣ ወዘተረፈ ምርት ከተመረተ የተሟላ አቅርቦት ይኖራል፡፡ እናም ሸማቹ ዋጋ ተደራዳሪና ወሳኝ ኃይል መሆን ይችላል፡፡ አምራቹም የሚያዋጣው ሀቀኛ ዋጋ ላይ ይቆማል፡፡ ሌላው መነሳት የሚገባው ቀጣይ ጥያቄ “ታዲያ የተትረፈረፈ ምርት ለማምረት ችግሩ ምንድነው?” የሚል ይሆናል፡፡ ችግሩ ብዙ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ አጭርና ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ችግሩ መሬት ነው፡፡ አሁን ያለው የአርሶ አደሩ መሬት የበሬ ግንባር የምታህል ናት፡፡ እሷም ለዘመናት ስትታረስ የኖረች፣ የማምረት አቅሟ የነጠፈ ነው፡፡ እናም የነጠፈና የበሬ ግንባር የሚያህል መሬት በማረስ የተትረፈረፈ ምርት ሊገኝ አይችልም:: ይህም በመሆኑ ከሀገሪቱ ህዝብ 85 በመቶ የሆነው አርሶ አደር፣ የተትረፈረፈ ምርት አምርቶ፣ የገበያ ፍላጎትን ሊያሟላ ቀርቶ ራሱን መመገብ እያቃተው፣ ልጆቹን ወደ ዐረብ ሀገራት የመላክ አማራጭ ውስጥ መግባቱ ይስተዋላል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ወደ ዐረብ ሀገራት የሚደረገው ስደትም ቆሟል፡፡
ዛሬ ከተሜው በድለላ፤ ገጠሬው በቀን ስራ በትርፍ ጊዜው ሰርቶ በሚያገኘው ገቢ ኑሮውን እየደጎመ ሊሆን ይችላል፡፡ አነስተኛ የቤት ኪራይ ፍለጋ ወደ ከተሞች ጠርዝ ወጥቶ መኖር፣ አማራጭ የኑሮ መፍትሄ ተደርጎም ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላም ሌላም አማራጮች እየተሞከሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ሁላችንም የምንገነዘበው ይመስለኛል፡፡ እናስ መፍትሄው ምንድነው? ያልን እንደሆነ፤ በእኔ በኩል አንድ መፍትሄ ይታየኛል፡፡ ይኸውም፤ የተትረፈረፈ ምርት ለማምረት ብቸኛው መፍትሄ፣ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የእርሻ መሬት ማዘጋጀት ነው፡፡ “ተጨማሪ መሬት ከየት ይገኛል?” ለሚለው ቀጣይ ጥያቄ፣ በበኩሌ ሁለት አማራጮች ይታዩኛል፡፡ አንደኛ፤ በደርግ ስርዓት “የመንግስት እርሻ” ተብለው የተያዙና እስከ አሁን ድረስ በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ መሬቶች ሲሆኑ፤ ሁለተኛው አማራጭ፣ በየክልሉ ለኢንቨስትመንት ተብለው የተቀመጡ ማንም ያልያዛቸው መሬቶች ናቸው፡፡ እነዚህን መሬቶች በአካባቢው ላሉ ወጣት ሥራ አጥ አርሶ አደሮች አከፋፍሎ በግል እንዲያርሷቸው ማድረግ ወይም ወጣቶች በማህበር እየተደራጁ የህብረት እርሻ (union) እንዲመሰርቱ በማድረግ ማከፋፈል አስፈላጊ መሆኑ ይታየኛል፡፡
ሰፈራን በተመለከተ የደርግ ዓይነት ሰፈራ ማካሄድ በዚህ ወቅት የማይታሰብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ወረዳ ያልታረሱ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ወይም መንግስት በባለሀብቶች በኢንቨስትመንት እንዲለሙ የያዛቸው መሬቶች ካሉ፣ ከዚያ ላይ የተወሰነውን ቀንሶ በወረዳው ላሉ ወጣት የአርሶ አደር ልጆች በማህበር እንዲያርሱት ማድረግ እንደ አማራጭ ሊታይ ይገባዋል፡፡ ትርፍ መሬት የሌለው ወረዳ ሲያጋጥም፣ ወረዳው ባለበት ዞን ውስጥ ባሉ ሌሎች ወረዳዎች መሬት ላይ እንዲሰፍሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሁሉም ነገር ግን በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማማከር ሊከናወን ይገባዋል፡፡
መንግስት እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ የመፍትሄ ሃሳቦችን በጥናት ላይ ተመስርቶ የሚወስድ ካልሆነ በስተቀር ስራ አጥነቱ፣ የኑሮ ውድነቱም ሆነ የዋጋ ንረቱ የሚገታ አይሆንም፡፡ እንዲያውም በቀጣይ ጊዜያት አርሶ አደሩ ከራሱና ከቤተሰቡ ቀለብ ተርፎት ወደ ገበያ የሚያወጣው ትርፍ ምርት ስለማይኖረው፣ ገበያ ላይ በኪሎ ቀርቶ በስኒ የሚሸመት እህል ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ይህ ደግሞ ዶ/ር መረራ ጉዲና ደጋግመው እንደሚሉት፤ የተራበ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ መሪዎቹን “መብላቱ” የሚቀር አይመስለኝም፡፡
መሬትን በሕዝብ ስም መንግስት እንዲያስተዳድር ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች አንዱ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲገጥሙ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲችል እንጂ፤ መሬቶችን አጥሮ ማንም እንዳይነካቸውና በአጠገባቸው ዝር እንዳይል ለመጠበቅ አይመስለኝም፡፡ ሕዝባችንን በዚህ ወቅት ከገጠመው የባሰ ፈታኝ ሁኔታ ሊገጥመው እንደማይችልም አስባለሁ፡፡ ስለሆነም፤ መንግስት ለሕዝቡ ብቻ  ሳይሆን ለራሱም ህልውና ሲል አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል:: እንደኔ እንደኔ፣ በመጪው የምርት ዘመን፣ በርካታ ጠፍ መሬቶች ማረስ ለሚችሉ የአዲሱ ትውልድ አርሶ አደሮች ተከፋፍለው በግልም ይሁን በማህበር እንዲታረሱ ቢደረግ፤ ለመንግስትም፣ ለከተሜውም ሆነ ለገጠሩ ሕዝብ በነፍስ መድረስ ሆኖ ይታየኛል፡፡
የአደጋ ዝግጁነት ፈንድ አቋቁሞ ሰዎች እስከሚራቡና ቀያቸውን ለቀው እስከሚሰደዱ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ ያንን ፈንድ በማህበር የተደራጁ ዜጎች፣ በአነስተኛ ወለድ እንዲወስዱ ወይም እንደ ትራክተር ያሉ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችንና ምርጥ ዘር ጭምር በማቅረብ አስፈላጊውን ሀገራዊ ምርት እንዲያመርቱ ቢያደርግ፣ አደጋን መከላከል ብቻ ሳይሆን አደጋን ማስወገድ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2677 times